February 21, 2024 – Konjit Sitotaw
እናት ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢሕአፓና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ያበረታታል የተባለውንና የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የተፈራረሙት የሳሞአ የንግድና ኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት እንዳያጸድቅ ዛሬ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ፣ ኢትዮጵያ የፈረመችውን ይሄንኑ ስምምነት “ትውልድ አምካኝ” እና “አገር እና ማንነትን አጥፊ” ብለውታል። ምክር ቤቱ የስምምነቱን መጽደቅ ማስቀረት ካልቻለ፣ ቢያንስ ከግብረ ሰዶም ጋር የተያያዙ አንቀጾች ከስምምነቱ “እንዲወገዱ” ወይም “እንዲታረሙ” እንዲያደርግ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
ስምምነቱ “ለግብረ ሰዶምና ግብረ ሰዶማዊነት በተዘዋዋሪ መልኩ ጥበቃ የሚያደርጉ፣ የሚደግፉና የሚያበረታቱ” አንቀጾችን አካቷል ያሉት ፓርቲዎቹ፣ ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንዳታጸድቅ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በጋራና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተናጥል ጭምር ያሰሙት ተቃውሞ በከንቱ ሊታለፍ እንደማይገባም አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ የሳሞአ ስምምነትን ካጸደቀ ግን፣ “የታሪክ ተጠያቂነት ይከተለዋል” በማለት ፓርቲዎቹ አስጠንቅቀዋል። የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የግብረ ሰዶማዊነት ተግባርን ወንጀል አድርጎ ደንግጓል።