February 21, 2024 – Konjit Sitotaw
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) “ኮንቬንሽን 189″፣ “190”፣ “97” እና”143″ የተባሉትን ዓለማቀፍ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ እንድታጸድቅ ዛሬ አገር ዓቀፍ ዘመቻ ጀምሯል።
አራቱ የቤት ሠራተኞችን፣ ፍልሰተኛ ሠራተኞችንና በሥራ ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች፣ የዓለም የሥራ ድርጅት ያወጣቸው ድንጋጌዎች ናቸው። “ኮንቬንሽን 189” የተሰኘው ድንጋጌ የቤት ሠራተኞችን መሠረታዊ መብቶች የሚመለከት ሲኾን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በ2011 ዓ፣ም ያወጣው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የቤት ሠራተኞችን ከወሰኑ ውጭ ያደረገና ያለ ሕግ ከለላ የተዋቸው መኾኑን ኢሠማኮ ገልጧል።
“ኮንቬንሽን 190” የተሰኘው ዓለማቀፍ ድንጋጌ በሥራ ቦታ ላይ የሚደርሱ የጾታና ጥቃቶችንና ትንኮሳዎችን የሚመለከት ሲኾን፣ “ኮንቬንሽን 97” እና “ኮንቬንሽን 143” ባንጻሩ በውጭ አገራት የተሠማሩ የቤት ውስጥ ሠራተኞችን መብቶች የሚመለከቱ ናቸው።