
21 የካቲት 2024, 15:56 EAT
የሶማሊያ ፓርላማ ከሳምንት በፊት ከቱርክ ጋር የተፈረመውን የመከላከያ እና የምጣኔ ሃብት ስምምነትን አጽድቋል። የዚህ ስምምነት ሙሉው ዝርዝር ይፋ ባይደረግም በተለይ በመከላከያ ዘርፍ ቱርክ የሶማሊያን ባሕር ኃይልን ለማጠናከር እና የአገሪቱን የባሕር ጠረፍ በጋራ ለመጠበቅ ከስምምነት መደረሱ ተነግሯል።
ቱርክ አንካራ ውስጥ የሁለቱ አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ስምምነቱን የተፈራረሙት ኢትዮጵያ ነጻነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ከተቀሰቀሰ ከአንድ ወር በኋላ ነው።
በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል የተደረሰው ስምምነት ለአስር ዓመታት የሚቆይ ነው። ቱርክ የሶማሊያን የባሕር ኃይል በማሠልጠን የምታስታጥቅ ሲሆን፣ የሶማሊያን የባሕር ጠረፍን ለመጠበቅም የራሷን የባሕር ኃይል በአካባቢው እንደምታሰማራ ተነግሯል።
ቢቢሲ ሶማሊኛ ባገኘው ሪፖርት መሠረት የቱርክ ወታደራዊ መርከቦች በቅርቡ ወደ ሶማሊያ የባሕር ግዛት በመድረስ የሚሰማሩ ይሆናል።
ለአስርታት በእርስ በርስ ጦርነት እና ባለመረጋጋት ውስጥ የቆየችው ሶማሊያ ከቱርክ ጋር በደረሰችው ወታደራዊ ስምምነት ሽብርተኝነትን፣ የባሕር ላይ ውንብድናን፣ ሕገወጥ አሳ ማስገርን እና በአካባቢው በቅርቡ የተከሰቱ ስጋቶችን ለመከላከል አቅም ይፈጥርላታል ተብሏል።
- ሶማሊያ እና ቱርክ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ9 የካቲት 2024
- የተፈረመው ስምምነት ጦርነት ከማወጅ ጋር የሚስተካከል ነው፡ በተመድ የሶማሊያ አምባሳደር20 የካቲት 2024
- ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች ከሶማሊያ ጎን እንደምትሰለፍ አል ሲሲ ተናገሩ22 ጥር 2024
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ከቱርክ ጋር የተፈረመው ስምምነት “የትኛውንም የሽብር ስጋት እና በባሕር ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶችን ጨምሮ ከውጭ አገራት የሚፈጸምን ጥሰት እንዲሁም ስጋትን” ለመከላከል ይጠቅማል ብለዋል።
ከተጠቀሰው ጥቅል የስምምነቱ አካል ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው ሰነድ አስካሁን ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም።
ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ አወዛጋቢውን ስምምነት ሲፈራረሙ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ ለወደብ እና ለባሕር ኃይሏ አገልግሎት የሚውል የባሕር ጠረፍን እንደምትሰጥ፣ በምላሹም ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን እንደአገር ለማወቅ እንደተስማሙ ተገልጾ ነበር።
ይህም ሶማሊያን አስቆጥቶ ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ ያደረገች ሲሆን፣ ጉዳዩን ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አቅርባ እንዲወገዝ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ ሶማሊያ ከተለያዩ አገራት ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ከቱርክ ጋርም ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረመችውም በዚህ ወቅት ነው።
ቢቢሲ ሶማሊኛ ከምንጮቹ እንደተረዳው ረቡዕ የካቲት 13/2016 ዓ.ም. በአገሪቱ ምክር ቤት የፀደቀው ከቱርክ ጋር የተደረሰው ስምምነት ለፓርላማውም ሆነ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ዝርዝርሩ በይፋ አልቀረበም።
ስምምነቱ ከሶማሊያ ምክር ቤት አባላት ድጋፍን ያገኘ ሲሆን፣ በሞቃዲሾ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር የሆኑት ሙርሳል ሳኒ ስምምነቱ የሶማሊያን ጥቅም ለማስከበር ጠቃሚ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ከአውሮፓውያ 2012 ጀምሮ የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ በአውሮፓ ኅብረት እየተጠበቀ ሲሆን፣ አሁን ከቱርክ ጋር የተደረሰው ስምምነት ተጨማሪ ኃይል ወደ አካባቢው እንዲሰማራ የሚፈቅድ ነው።
በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ቁጥራቸው በውል ያልተገለጹ የቱርክ የባሕር ኃይል መርከቦች እና ወታደሮች በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ውስጥ ሆነው ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ የሶማሊያን ባሕር ኃይል መልሶ እንዲደራጅ ያደርጋሉ ተብሏል።
ቱርክ ወታደሮቿን ወደ አፍሪካ ቀንዷ አገር ስታሰማራ የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከስድስት ዓመታት በፊት ከግዛቷ ውጪ ትልቁ ነው የተባለውን ወታደራዊ ሰፈርን በ50 ሚሊዮን ዶላር መገንባቷ ይታወሳል።