ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

ዜና በትግራይ ክልል ያለበቂ ሥልጠና ፖሊስን የተቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ለእስረኞች ሥጋት መሆናቸው ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: February 21, 2024

በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች መደበኛ ፖሊስንና የማረሚያ ቤት ተቋማትን ሲቀላቀሉ ያለ በቂ ሥልጠና በመሆኑ፣ በእስር ላይ ባሉ ዜጎች ላይ አደጋ መደቀኑን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል አምስት ዞኖች አስተዳደሮች ውሰጥ ሰብዓዊ መብትና ሰብዓዊ ቀውስን በተመለከተ አካሄድኩት ያለውን የምርመራ ሪፖርት ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በሪፖርቱ በክልሉ የሚካሄደው የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባር በፍጥነት መካሄድ አለበት ብሏል፡፡

የኢሰመኮ ሪፖርት በትግራይ ክልል የሚገኙ የፍትሕ ተቋማት በተለይም ፍርድ ቤቶች፣ የፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስና የማረሚያ ቤት አስተዳዳር ተቋማት የሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አስታውቋል፡፡                               

የቀድሞ ተዋጊዎች በመልሶ ማቋቋም ሒደቱ ወደ መደበኛ ፖሊስና ማረሚያ ቤት ፖሊስ የሚቀላቀሉ አባላት ተገቢውን ሥልጠና ባለማግኘታቸው፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ላይ የሚደርስ ድብደባ፣ ያልተገባ ቅጣት፣ እጃቸው ታስሮ እንዲቀመጡ ማድረግ፣ ከማሰቃየት ወንጀል ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ቅጣቶች፣ ሰብዓዊ መብትን ያልጠበቁ አያያዞችና ከሕግ ውጪ የሚደረጉ እስሮችን እየፈጸሙ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

መንግሥት ያቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከስምንት ክልሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ማጣራት 371,971 የቀድሞ ተዋጊዎች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ ትልቁን ቁጥር የትግራይ ክልል ይይዛል፡፡

ኢሰመኮ በሪፖርቱ የፍትሕና የፀጥታ ተቋማቱ ላይ አፋጣኝ የአቅም ግንባታ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ መሠረት ያደረገ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች በመብዛታቸው የአቅርቦቱ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን፣ በሰላም የመኖር መብት አደጋ ውስጥ መውደቁን፣ የክልሉ የጤና ተቋማት መልሰው አገልግሎት ለመስጠት ከደረሰባቸው ውድመት ሙሉ በሙሉ አለመጠገናቸውን፣ የሕፃናትና የእናቶች ሞት ከሰብዓዊ ቀውስ ጋር መባባሱንና አፋጣኝ ዕርምጃ የሚያስፈልገው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት የደረሰባቸው ውድመትና ዝርፊያ ትምህርትን መልሶ ለማስጀመር አዳጋች መሆኑን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ ሁሉም ወገን የተቻለውን ጥረት በማድረግ ሕፃናት ሙሉ በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አለባቸው ብሏል፡፡

ሪፖርቱ በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በየካቲት 2024 ብቻ 12,000 አዳዲስ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን፣ ከክልሉ ባለሥልጣናት መረጃ ማግኘቱን አመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች የሥነ ልቦና አገልግሎት፣ የሕግና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም ብሏል፡፡

በክልሉ አብዛኞቹ የፆታ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ መሆኑን፣ ጥቃቱ የተፈጸመው በኤርትራና በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ባሉ አካባቢዎች እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የተለያዩ ጥቃቶች የተፈጸሙባቸው ዜጎች እየደረሰባቸው ባለው መገለል የተነሳ ከማኅበረሰቡ እየራቁ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ መጠነ ሰፊ የሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ቀውስ አፋጣኝ ዕርምጃ ይፈልጋል ያለው ኮሚሽኑ ለዚህም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተፋጠነ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲኖር እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ከክልሉ አደጋ ሥጋት ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ 6.5 ሚሊዮን ወይም 84 በመቶ የሚሆኑ ወገኖች ዕርዳታ ጠባቂ ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችም ሆኑ ባሉበት ሆነው ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን የሚጠብቁ ዜጎች የሚያገኙት ድጋፍ በጣም ውስን ስለመሆኑ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አገኘሁት ባለው መረጃ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በረሃብና ተያያዥ ሕመሞች ምክንያት አንድ ሺሕ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ አስታውቋል፡፡

 በመጠለያዎቹ በረሃብና በተያያዥ ሕመሞች ሕፃናትና እናቶች እንደሚሞቱ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የዕርዳታ አስተባባሪዎች መረጃ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ  በረሃብና ተያያዥ በሽታዎች መሞታቸውን ባያረጋግጥም፣ የተባለው ሞት ሊከሰት እንደሚችል ግን አሳማኝ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡ በርካታ ተፈናቃዮች የሚገኙት በትምህርት ቤቶች በመሆኑ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን ተጠቅሞ ወደ ትምህርት ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ እንደሆነበትም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ምልከታ አደረግኩበት ያለው የማይጨው ማረሚያ ቤት በቂ የሰው ኃይል የሌለው በመሆኑ፣ በአንድ መታሰሪያ ክፍል ውስጥ 90 ሰዎች እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አስር ቤት የሚገኙ ታራሚዎች በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ ያገኛሉ ብሏል፡፡ በሽሬ ማረሚያ ቤት የምግብና የውኃ አቅርቦቱ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑን፣ አቅርቦቱ በማኅበረሰቡና በድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች የመስጠት ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው ተብሏል፡፡

ኮሚሽኑ በኃይል እንዲፈናቀሉ በተደረጉ፣ ከሕግ ውጪ በተገደሉ፣ ፆታዊ ጥቃት በደረሰባቸው ዜጎችና ከሕግ ውጪ ተደረጉ በተባሉ የእስር ወንጀሎች ፈጣንና ሁሉን አቀፍ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡