
ዜናበሸገር ከተማ የወንጀል ተጠርጣሪዎች አያያዝ በሕግ አግባብ ብቻ መሆን እንዳለበት ኢሰመኮ አሳሰበ
ቀን:
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሰላምና ደኅንነትን የማስከበር፣ ወንጀል የመከላከልና የመመርመር ሥራ በሕግ አግባብ ብቻ ሊሆን ይገባል ሲል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡ኢሰመኮ ከኅዳር 10 እስከ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሸገር ከተማ በፖሊስ ማቆያዎችና ማረሚያ ቤት በጥበቃ ሥር ያሉ የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ አካሄድኩት ያለውን ክትትልና ለባለድርሻ አካላት አቀርብኳቸው ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች ትናንት ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡በምክረ ሐሳቦቹ አብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት እንደማያቀርቡ፣ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎችን በዋስትና ከለቀቀ በኋላ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ፣ ተጠርጣሪዎች የራሳቸውን ወይም የሌላ ሰው ካርታ ወይም የመኪና ባለንብረትነት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ እንደሚጠየቁ መገንዘቡን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡
የተጠርጣሪዎች የምግብ በጀት አነስተኛ መሆኑና በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ወጥ ሆኖ አለመመደቡን፣ ነፃ የሕክምና አገልግሎት አለመኖር የሚሉ ጉዳዮችን በክትትሉ ማግኘቱን አመላክቷል፡፡የማረሚያ ቤቱ ሕጎችና መመርያዎች ለታራሚዎች በጽሑፍ አለመድረሳቸው፣ የተመደበው የምግብ በጀት አነስተኛ በመሆኑ በቂና ጥራቱን የጠበቀ ምግብ አለመቅረቡ፣ በከፍተኛ የሕክምና ተቋማት መታከም ያለባቸው ታራሚዎች በተሽከርካሪና በአጃቢ እጥረት፣ እንዲሁም ከሕክምና ተቋማቱ ጋር የነበረው ውል በመቋረጡ የሕክምና አገልግሎት ሲፈለግ ማግነኘት እንደማይቻል ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡የሸገር ከተማ ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን በገቢ ማስገኛ ሥራዎች በማሰማራትና አምራች ዜጎች ሆነው እንዲወጡ እንደሚሠራ፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሕፃናት ትምህርታቸውን ከማረሚያ ቤቱ ውጪ መቀጠል እንዲችሉ ዕገዛ መደረጉን፣ የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ንፅህናቸው የተጠበቀና በቂ መንቀሳቀሻ ሥፍራ ያላቸው መሆናቸው በጠንካራ ጎን የሚወሰዱ ዕርምጃዎች መሆናቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አመላክቷል፡፡