
February 21, 2024

የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2016 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እፈቅዳለሁ ብሎ ያቀደውን ከ23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ሙሉ በሙሉ ማሳካቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ የ2016 ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ካሠራጨው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ የሰጠው ብድር በዕቅዱ ልክ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ11.3 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡
ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ፈቅዶ ከነበረው የ12.3 ቢሊዮን ብር ብድር አንፃር ሲታይ፣ ዘንድሮ በግማሽ ዓመት የለቀቀው ብድር ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ በሊዝ ፋይናንስ የተሰጠው ብድር ከዕቅዱም በላይ አፈጻጸም የታየበት ነው፡፡
እንደ መረጃው በ2016 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት በሊዝ ፋይናንስ ለመፍቀድ ታቅዶ የነበረው የብድር መጠን 6.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የተፈቀደው ግን 10.5 ቢሊዮን ብር በመሆኑ የ151 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገብ ችሏል፡፡
የብድር አመላለስን በተመለከተም በስድስት ወራት ውስጥ ለማሰባሰብ አቅዶ የነበረው 7.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አፈጻጸሙ 6.6 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ ግማሽ ዓመት ባንኩ ከብድር ማስመለስ ጋር ተያይዞ ከሌላው ጊዜ በተለየ ተግዳሮት እንደገጠመው አመላክቷል፡፡ የተግዳሮቶቹ መነሻም ከዚህ ቀደም የተሰጡ ብድሮች ሲሰባሰቡ የነበሩት ማበረታቻ ጭምር በመስጠት ስለነበርና በዚህ ግማሽ ዓመት ግን ማበረታቻዎቹ በመቀነሳቸውና የብድር አሰባሰቡን በታቀደው መጠን ማሳካት አለማስቻሉን፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) የስድስት ወራት የባንኩን አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መግለጻቸው ታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም የብድር አሰባሰቡ ከፍተኛ አፈጻጸም ሲመዘገብበት የነበረው ለተበዳሪዎቹ የሚያስፈልገው የሥራ ማስኬጃ ካፒታል፣ ለጥሬ ዕቃና ለመለዋወጫ ዕቃዎች ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ባንኩ ያቀርብ ስለነበር፣ ተበዳሪዎቹም በዚህ ተበረታትተው ብድራቸውን በቶሎ መክፈል መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡
ባንኩ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ጠቃሚ የሆኑ በተለይም በውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተዋጽኦ ላላቸው ፕሮጀክቶች ለመደገፍና ፋይናንስ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነበት፣ ፕሬዚዳንቱ በሪፖርታቸው ሳያመላክቱ አላለፉም፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር ለመቅረፍ 150 ሚሊዮን ዶላር ቢገኝ ትልቅ ለውጥ ሊፈጥር ይችል እንደነበርና ይህ ባለመሆኑ፣ ተበዳሪዎቹ በቶሎ የሚከፍሉበትን ዕድል እያሳጣ ስለመሆኑ ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ብድር አሰባሰቡ በዕቅዱ ልክ ባይሆንም ከአፈጻጸሙ አንፃር ጥሩ የሚባል ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ በግማሽ የሒሳብ ዓመቱ እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት ቢሆንም፣ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ግን ከፍተኛ የሚባል ውጤት ማስመዝገብ ችሏል ተብሏል፡፡
ከአምስት ዓመታት በፊት ኪሳራ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሪፎርም በማድረግና አዲስ ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ አትራፊነት የተሻገረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከሪፎርሙ በፊት 40 በመቶ የተበላሸ ብድር የነበረበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በየዓመቱ የተበላሸ ብድር መጠኑን በመቀነስ በሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ የተበላሸ ብድር መጠኑን 7.3 በመቶ ማድረስ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡
አጠቃላይ የሀብት መጠኑንም ባለፉት አራት ዓመታት በአራት እጥፍ በማሳደግ፣ 170 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ታውቋል፡፡ ከትርፍ አንፃርም ከኪሳራ ወጥቶ በየዓመቱ ትርፉን በማሳደግ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 6.3 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ይታወሳል፡፡
የ2016 የግማሽ ዓመት የትርፍ መጠኑን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ግን የግማሽ ዓመቱ የትርፍ መጠን በተወሰነ ደረጃ ቅናሽ ማሳየቱ ታውቋል፡፡ የባንኩ ይፋዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በ2016 ግማሽ ዓመት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 1.47 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ 1.58 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት የተገኘው ትርፍ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ባንኩ በ2013 ግማሽ ዓመት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 130 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. ደግሞ 470 ሚሊዮን ብር ማትረፉ አይዘነጋም፡፡