ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

February 21, 2024

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ ብዙ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ተጠብቆ ነበር፡፡ እንደተጠበቀውም በአኅጉሩ ስለጨመረው የመፈንቅለ መንግሥት፣ የምርጫ ወቅት ግጭት፣ የሰብዓዊ ቀውስ፣ ጦርነት፣ እንዲሁም ስለአሳሳቢው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ አጀንዳዎች ላይ መክሯል፡፡ ከእነዚህ አጀንዳዎች በተጨማሪም መላው ዓለምን እየተፈታተኑ ያሉ ከጂኦ ፖለቲካ ፍጥጫ፣ ከግጭትና ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችም የተነሱበት ጉባዔ ነበር፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ይህን በመሰለ አኅጉራዊ መድረክ ላይ የተገኙት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ግን የጉባዔውን የትኩረት አቅጣጫ ለመሳብ ሞክረው ነበር፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የአዲስ አበባው ጉባዔ መሪ ተዋናይ ሆነው ለመቅረብ መሞከራቸው አስገራሚው ክስተት ነበር፡፡

በብዙ ቁልፍ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ይተላለፍበታል የተባለው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት በፈጠሩት አምባጓሮ ትኩረት ሊያጣ ይችል ይሆን ወይ ተብሎ ታስቦም ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደ ኅብረቱ የስብሰባ አዳራሽ እንዳልገባ የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ከለከሉኝ ማለታቸው ውዝግብ ቢፈጥርም ያን ያህል ትኩረት አላገኘም፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ንግግር ሲያደርጉ

ወደ ኅብረቱ አዳራሽ እንዳልገባ ብቻ ሳይሆን ከሆቴልም እንዳልንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊያኑ አድርገውኛል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ከሰዋል፡፡ የኅብረቱ መቀመጫ የሆነችው የስብሰባው አስተናጋጅ አገር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት የማትመጥን አገር እንደሆነች በመጥቀስ፣ መቀመጫው ወደ ሌላ አገር እንዲዛወር እስከመጠየቅ ድረስ ሄደዋል፡፡

ወደ 30 የአፍሪካ መሪዎች በታደሙበት የኅብረቱ ስብሰባ ላይ በጋራ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ንግግር ያሰማሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ግን ኢትዮጵያን መወንጀል ላይ ያተኮረ ንግግር ነበር ያቀረቡት፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ መላው ትኩረቱ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በገባችበት ፍጥጫ ላይ እንዲያተኩር የፈለጉ መስለው ታይተዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት አውግዞ የጋራ አቋም እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡  

ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም እንደደጋገሙት ሁሉ ኢትዮጵያ የሶማሊያ አካል ከሆነችው ከሶማሌላንድ ጋር ስምምነት በመፈረም፣ ሉዓላዊ ግዛታችንን ለመንጠቅ እየሞከረች ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት የአፍሪካን ሰላምና መረጋጋት የሚያናጋ ዕርምጃ ነው፡፡ ሶማሊያ የዓለም አቀፍ ችግር ምንጭ የሆኑ ሽብርተኞችን በመዋጋት ስኬታማ እየሆነች በመጣችበት በዚህ ወቅት ስምምነቱ ጥረታችንን የሚያደናቅፍ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በዚህ የተነሳ በጋራ ጠንካራ አቋም ሊይዝ ይገባል፡፡ ከጎረቤቶቻችን ጋር አላስፈላጊ ፀብ እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ አገሬ በኢትዮጵያ ለመወረርና ግዛት ለመነጠቅ መጋለጧ የአፍሪካ ኅብረት መርሆዎችን የሚጥስ ድርጊት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት የቅኝ ግዛት ድንበሮች ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚያደርገውን ስምምነት እንዲጣስ የሚያደርግ ነው፡፡ ሶማሊያ በጊዜው ባትደግፈውም የአፍሪካ ኅብረት አባላት ድንበር በቅኝ ግዛት ወቅት እንደነበረው ተጠብቆ ይቆያል የሚለውን መርህ ካፀደቀ ቆይቷል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነትም የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚደፈር ብቻ ሳይሆን ድንበራችንንም የሚቀይር ነው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ከስብሰባው ጎን ለጎን በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተመሳሳይ ውንጀላን በኢትዮጵያ ላይ አሰምተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል ሕግን ጥሳ በስብሰባው እንዳይሳተፉ እንቅፋት ለመፍጠር መሞከሯንም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ላይ፣ ‹‹ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት የመዝጊያ ጉባዔን ለመካፈል ከሆቴሌ ልወጣ ስል የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ከለከሉኝ፡፡ ለረጅም ሰዓታት በሆቴሉ ለመቀመጥ ከተገደድኩ በኋላ በጂቡቲው ፕሬዚዳንት መኪና ነበር ወደ ኅብረቱ ጽሕፈት ቤት የሄድኩት፡፡ በጽሕፈት ቤቱም መግቢያ ግን የጂቡቲው ፕሬዚዳንትና እኔ እንዳንገባ በድጋሚ ተከለከልን፡፡ የታጠቁ ወታደሮች ነበሩ እንዳንገባ የከለከሉን፡፡ የሌሎች አገሮች መንግሥታት መሪዎችም ይኼው እንቅፋት ገጥሟቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የሚናገሩት አዎንታዊ ንግግር ምንም ትርጉም የለውም፡፡ በተግባር ያየነው ነገር ብዙ ይገልጻል፡፡ ኢትዮጵያ የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛትን ለመጠቅለል እንዳሰበች የዛሬው ድርጊት በግልጽ ያሳያል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ተሳታፊ የሆንን የአገር መሪዎችን ኢትዮጵያ በአደባባይ አዋርዳናለች፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ሆኖ ይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ ቢያስብበትና ውሳኔ ቢሰጥበት፤›› በማለት ነበር ወቀሳ በኢትዮጵያ ላይ ያቀረቡት፡፡

የሶማሊያ መሪ በአዲስ አበባ የፈጠሩት አምባጓሮ በኅብረቱ ጉባዔ ላይ ጥላ ለማጥላት ያለመ ነበር፡፡ ኒቲሽ ቨርማ ‹‹African Union Summit Overshadowed by Somalia – Ethiopia Dispute›› በሚል ርዕስ ያስነበበው ዘገባ ይህንኑ በሰፊው አትቶታል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ቀውስ ጭምር መክሮና ዘክሮ አቋም ይይዛል ተብሎ የኅብረቱ ጉባዔ ሲጠበቅ፣ የሶማሊያው መሪ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር የፈጠሩት ግብግብ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ እንደተገኘ ዘገባው ይገልጻል፡፡ ትልቅ ቦታ በተሰጠውና ብዙ በተጠበቀው የኅብረቱ ስብስባ ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ የገቡበት ወቅታዊው ፖለቲካ ውጥረት ጎልቶ ሲስተጋባ መታየቱን በዘገባው ተመልክቷል፡፡

በስብሰባው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሶማሊያ ባለሥልጣን የሚያስታግስ ንግግር አሰምተው ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ሶማሊያን እንደ ወዳጅ አገር ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድን ደግሞ እንደ ወዳጅ ነው የምትመለከተው፡፡ ሶማሊያን ለመጉዳት አንዳችም ፍላጎት የለንም፣ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈረምን በኋላ ለጎረቤቶቻችን እንደ ወዳጅ አገር ሐሳብ ለመለዋወጥ ጥረት አድርገናል፡፡ በታላቅ ወንድማችን እስማኤል ኦማር ጊሌ አማካይነት ጂቡቲ ላይ ተቀምጠን ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ጋር ለመምከር ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡ በኡጋንዳም ፊት ለፊት ከፕሬዚዳንት ሀሰን ጋር ንግግር ለማድረግ በፕሬዚዳንት ሙሴቬኒና በፕሬዚዳንት ሩቶ በኩል ጥሪ አቅርበናል፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡ አሁንም ቢሆን ለኅብረቱ ግልጽ የምናደርገው ሶማሊያዊያን ያላቸውን ሥጋት በሙሉ በግልጽ ለመነጋገር ዝግጁ ነን፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

ለሶማሊያው መሪ ሀሰን ሼክ ግን ይህ ሁሉ ትርጉም የሌለው የጣፈጠ ቃል ብቻ ሆኖ ነበር የታያቸው፡፡ ኢትዮጵያን ማመን ያልፈለጉ የሚመስሉት ፕሬዚዳንቱ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ካልተሰረዘ በስተቀር ከኢትዮጵያ ጋር ንግግር የሚባል አይኖርም በሚለው አቋማቸው የፀኑ ነው የሚመስለው፡፡ ይህ ሳያንስ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እንዳልካፈል እንቅፋት ፈጠረች የሚል ትኩሳት ነበር የቀሰቀሱት፡፡

በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማትነት ለበርካታ ዓመታት የሠሩት፣ እንዲሁም በፖለቲካ ሳይንስ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በማስ ሚዲያ መምህርነት ለረጅም ዓመት የሠሩት ብሩክ ኃይሌ (ፕሮፌሰር)፣ የሶማሊያው መሪ የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮሎችን ባልተከተለ መንገድ ኢትዮጵያን መወንጀላቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዲፕሎማትነት በአሜሪካ ባሳለፉበት ወቅት ካዩት፣ እንዲሁም ለረጅም ዓመታት ባገለገሉበት የውጭ ግንኙነት ከሚያውቁት ልምድ ተነስተው የአፍሪካ ኅብረትን በመሰሉ መድረኮች የሚጠበቀውን የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል በሰፊው አስረድተዋል፡፡

‹‹በቬና ኮንቬንሽንም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ስምምነቶች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለመዱ አሠራሮች ከአኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆኑ አገሮች የሚከተሉት ራሱን የቻለ የፕሮቶኮል አሠራር አለ፡፡ የተለያዩ አገሮች መሪዎችን ሲያስተናግዱ የመሪዎቹን አካላዊ ደኅንነት፣ እንዳይገደሉ፣ እንዳይጎዱ ብቻ ሳይሆን እንዳይሰደቡ፣ ድንጋይ እንዳይወረወርባቸው ብቻ በብዙ መንገዶች ሕይወታቸውን ለመጠበቅ ስምምነት አለ፡፡ ይህ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ባለበት ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለበት ኒውዮርክም የሚተገበር ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካ የነበራቸውን የዲፕሎማሲ ቆይታ ሲያስረዱም፣ በእንግድነት የሚመጡ መሪዎች ወደ አስተናጋጁ አገር አየር ክልል ሲገቡ ጀምሮ ጥበቃው በአስተናጋጁ  አገር እጅ ላይ እንደሚወድቅ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ዋሽንግተን በነበርን ጊዜ አሠራሩን በደንብ አይቻለሁ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ እዚያ ሲመጡ የሚደረገው የፕሮቶኮል ዝግጅት ቀላል አይደለም፡፡ መለስ ከአዲስ አበባ ሳይነሱ ስንት ጠባቂ እንደሚመጣ፣ ምን ዓይነት መሣሪያ እንደሚይዙም ይጠየቃል፡፡ ይህን ያህል መትረየስ፣ ሽጉጥ ተብሎ የሚይዙት መሣሪያ ከእነ መለያ ቁጥሩ (ሲሪያል ነምበር) እስከሚይዙት ጥይት ብዛት ድረስ ተመዝግቦ ወደ ዋሽንግተን ይላካል፡፡ ይህን መረጃ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እናቀርባለን፡፡ አቶ መለስ አጃቢዎቻቸውን አስከትለው ሲመጡ ደግሞ የአሜሪካ ፀጥታ አስከባሪዎች ሁሉንም የፀጥታ ጥበቃ ሥራ ይረከቡታል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ የውጭ ዲፕሎማቶች በሥውርም በግልጽም የደኅንነት ጥበቃ ይደረግላቸዋል የሚሉት ብሩክ (ፕሮፌሰር)፣ የዋሽንግተን ግዛትም የፌዴራል መንግሥቱም ይህ ኃላፊነት በቀጥታ ይመለከታቸዋል ብለዋል፡፡ ይህ የአፍሪካ ኅብረት ባለበት አዲስ አበባም ተመሳሳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን አኅጉራዊ ጉባዔ በማስተናገድ 60 ዓመታት ልምድ አላት፡፡ ዘንድሮ ወደ 40 አገሮች መሪዎቻቸውን መላካቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ወደ ኅብረቱ የስብሰባ አዳራሽ መሪዎች፣ ውጭ ጉዳዮቻቸውና አማካሪዎቻቸው ብቻ ካልሆኑ ለመግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ ይህ ለረጅም ጊዜ ሲተገበር የኖረ ፕሮቶኮል ነው፡፡ ወደ አዳራሹ የጦር ሥልጠና ያለውና የታጠቀ አጃቢ የማይገባው፣ የተለያየ አደጋ እንዳይፈጠርና ለደኅንነት ሲባል ነው፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከአጃቢዎቼ ጋር ካልገባሁ ማለቱን ነው የሰማሁት፡፡ ይህ አለመፈቀዱ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ አልጄሪያና ሞሮኮ ዓይጥና ድመት ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ አገሮች መሪዎችን ከእነ አጃቢዎቻቸው ማስገባት አደጋ አለው፡፡ የአንዱን መሪ አጃቢ አስገብተህ ደግሞ የሌላውን ልትፈቅድ አትችልም፡፡ የዚምባብዌም፣ የኤርትራም የሌላውም ቢገባ አዳራሹ ውስጥ ድንገት ፀብና ግጭት ቢፈጠር የመሪዎቹን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥልና ለጦርነት የሚጋብዝ ችግር ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

መሪዎች እንዲህ ባለው አዳራሽ ለብቻቸው የሚገቡት በመካከላቸው ሊኖር የሚችል መጯጯህና አለመግባባትን በጓዳ ለብቻቸው እንዲፈቱ በማሰብ ጭምር መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ጠንቅቃ የምታውቅ እንጂ ለአኅጉራዊ ዲፕሎማሲ አማተር እንዳልሆነች ብሩክ (ፕሮፌሰር) ያስረዳሉ፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከዚህ አንፃር አዲስ አበባ የመጡት በቁጭት ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለመዝለፍ ተዘጋጅተው እንደሆነ በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ፕሮቶኮሉን አጓድላ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፍራካ ኅብረት ጉባዔውን መስተንግዶ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱ ሚኒስትር ደኤታዎች ብርቱካን አያኖ (አምባሳደር) እና ምሥጋናው አረጋ (አምባሳደር) ስለጉባዔው ሒደት ትናንት ሰፊ መግለጫ ለጋዜጠኞች ሰጥተው ነበር፡፡ ከሶማሊያው መሪ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን የፕሮቶኮል ግጭት አምባሳደሮቹ በዚሁ ጊዜ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡

የአፍሪካ መሪዎችን መቀበልና የማስተናገዱን ሥራ ከኅብረቱ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ እንደምትሠራ ተናግረዋል፡፡ ብርቱካን (አምባሳደር) ‹‹ከማለዳው እስከ እኩለ ለሊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካቢኔ ሚኒስትሮች በፈረቃ ሲቀበል ቆይቷል፡፡ በተቻለ አቅም በወታደራዊ የሙዚቃ ባንድና የክብር ዘብ በማጀብ ተቀብሏል፡፡ ፕሮቶኮሉ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ 12፡00 ሰዓት የሚያዝ ቢሆንም እኛ ግን ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሚኒስትሮቻችንን ኤርፖርት አሳድረን ጭምር ነው አቀባበል ስናደርግ የቆየ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሶማሊያ መሪ ሲመጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ተዘመረ ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠራጭቷል፡፡ ይህ ፍፁም ሐሰት ሲሆን በአፍሪከ ኅብረት ጉባዔ ጊዜ የኢትዮጵያ ሳይሆን የኅብረቱ መዝሙር ነው የሚዘመረው፡፡ ባንዲራውም ቢሆን የኢትዮጵያና የኅብረቱ ባንዲራ ነው የሚሰቀለው፤›› በማለት ዝርዝር ፕሮቶኮሉን አብራርተዋል፡፡

የደኅንነት ጥበቃን በተመለከተ የኅብረቱ ዋና ፕሮቶኮል ባለበት ለተስተናጋጅ አገሮች በቂ የፕሮቶኮል መረጃ መስጠቱን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመረጃ ክፍተት የተፈጠረ ሳይሆን መደበኛውንና የተለመደውን አሠራር ለማደናቀፍ በሚደረግ ጥረት ነው ችግሩ የተፈጠረው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም በኅብረቱ ስብሰባ ወቅት ሆነ ተብሎ አምባጓሮ የመፍጠር ችግር በተስተናጋጅ አገር መሪዎች እንደገጠማት በርካቶች ይናገራሉ፡፡ በ1974 ዓ.ም. በተስተናገደው 19ኛው የመሪዎች ጉባዔ የሊቢያው የያኔው መሪ ሙአመር ጋዳፊ አምባጓሮ ፈጥረው እንደነበር አንዳንዶች ያስታውሳሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴና በጊዜው የነበሩ የፕሮቶኮል ሰዎች ማስታገሻ በመስጠት ጋዳፊን ከእነ አጃቢዎቻቸው እንደሸኟቸውም ያወሳሉ፡፡

የቀድሞ ዲፕሎማት ፍሰሐ አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከዚያ አጋጣሚ አስቀድሞም የሊቢያው መሪ ኢትዮጵያ መጥተው ተመሳሳይ የፕሮቶኮል ጥሰት  መፈጸማቸውን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ጋዳፊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ተሳደቡ፡፡ ይህን ጊዜ ግን የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች እነ ጋሽ ከተማ፣ እነ ምናሴ፣ እነ ገብረግዚ (ዶ/ር) የመሳሰሉ ባለሥልጣናት በቂ ምላሽ በዚያ መድረክ ላይ ሰጡት፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በጭብጨባ እስኪደግፉ ድረስ ምላሽ ተሰጠው፤›› የሚሉት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ በዚህም ኢትዮጵያ ችግሩን እንደተወጣች ገልጸዋል፡፡

የዲፕሎማሲ መቀመጫ በሆኑ አገሮች አስተናጋጅ አገር ከራሱ ከተቋሙ ጋር ስምምነት እንደሚያደርግ ዲፕሎማቱ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ይኼው ስምምነት ያላት ሲሆን፣ ጉባዔ በሚካሄድበት ወቅት ይህንኑ ስምምነት ተከትሎ የፕሮቶኮል ደንበኞች ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስረድተዋል፡፡