ሔኖክ ያሬድ

ቀን: February 21, 2024

‹አገር ተቃጠለ
እሳተ ጎመራ ወረደ ከሰለ።
ጭስ አመድ አዋራ ሰማዩን ሸፈነው
ጥቁር ሰማይ ጥቁር!
የቀን ጨለማ ሞት በእናት አገር ሰማይ
በጀግናው ሕዝብ ላይ የጠላት ግፍ ቀንበር።
ፋሺስት አስተጋባ ፋስ ተሰነዘረ
ባካፋ መዶሻ ሕዝብ ተወገረ።

አባቶች ታረዱ

እናቶች ታረዱ

ቤት ንብረት ፈረሰ ከብቶቹ ተነዱ።›

ይህ አንድ አንጓ የባለቅኔውና ሠዓሊው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ከጻፈውና መንገድ ስጡኝ ሰፊ ከተሰኘው መድበል የተገኘ ነው፡፡ ግጥሙ የሚያዘክረው ከ87 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ወርሮ የነበረው ፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በግፍ የገደላቸውን ሰማዕታተ ኢትዮጵያን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰማዕታት ሲዘከሩ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚገኘው የሰማዕታቱ
አፅም ያረፈበት ሐውልት

ከሰማንያ ሰባት ዓመታት በፊት ፋሺስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ከተማ የፈጃቸውና ሰማዕትነት የተቀበሉት ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሐውልት ተዘክሯል፡፡ የሰማዕታቱ ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም በጸሎተ ፍትሐት የታሰበው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) አማካይነት በ1934 ዓ.ም. በካቴድራሉ አፀድ ውስጥ በተተከለው የሰማዕታቱ አፅሞች ማረፊያ ነው፡፡

ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 14ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. ሲያከብሩ በተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ባበረከቱበት አዲሱ ሐውልት ግርጌ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ ዘመነ ፍዳውን የሚያስታውስ ነው፡፡

 ‹‹ዝንቱ ውእቱ ምዕራፈ አዕጽምቲሆሙ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን እለ ተቀትሉ በግፍዕ በእደዊሆሙ በሕዝበ ኢጣሊያ ፋሽስታውያን አመ ፲ወ፪ ለየካቲት በ፲ወ፱፻፳ወ፱ ዓ.ም …››

ይህ የአፅሞች  ማረፊያ በጣሊያን ፋሽስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን1929 ዓ.ም. የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው፤ በሚልየሚንደረደረው የሐውልቱ ጽሑፍ አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላበመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ)፣በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡ የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት ከእንግሊዝ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ስፍራም መታሰቢያውን አቆሙላቸው፡፡

በፋሺስት ጣሊያን ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት ሠላሳ ሺሕ ኢትዮጵያውያን በቆመው ሐውልት ግርጌ ላይ የተቀረፀው ግጥም የሚከተለው ነው፡፡

ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ

በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ

ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ

ማነው እንደ ፋሽስት በሰው ግፍ የዋለ?

ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ

በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ

እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡

ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ

ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ

አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን

ኢጣሊያ መሆኗን መርዛም ጠላታችን፡፡

እላንት አእጽምቶች ዕድለኞች ናችሁ

በኃይለ ሥላሴ ትንሣኤ አገኛችሁ፡፡

የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› በተሰኘውና በ1989 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሺስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡

‹‹የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡

የዓይን እማኙ ‹‹ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12›› የተሰኘ ጽሑፍ የጻፉት ተመስገን ገብሬም እንዲህ ጽፈዋል፡-

‹‹ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሽስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርአያን እግራቸውን ጠርቅመው አሰሯቸው፡፡ ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው ‹እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል፡፡ ኢየሱስንም በዚያ አየዋለሁ፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል!› የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ፡፡ ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ፡፡ ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርአያ ወደቁ፡፡ ካምዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው፡፡ እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው ኑረዋል፡፡ ከዚያም መሐል ጨመሩን፡፡

‹‹ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል፡፡ በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገለዋቸዋል፡፡ ሬሣቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ፡፡ እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ፡፡ ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን፡፡ አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ፡፡ የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ፡፡ ፋሺስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ መንግሥቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል፡፡ እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱሰ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምራቄ ደረቀ፡፡ በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን፡፡ ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር፡፡››

ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያኔው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ ለኔፕልስ ልዑል ልደት ክብር ተብሎ በተዘጋጀው መሰናዶ አጋጣሚ፣ በወቅቱ የተፈጠረውን የፋሺስት ጣሊያን ጭፍጨፋ የታዘበው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ዶ/ር ላዲስላስ ሳቫ ዓይኑ ያየውንና የታዘበውን በማስታወሻው መግለጹን በጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተመልክቷል፡- ‹‹…ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ፡፡ …በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም፡፡ ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ስውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር፡፡››

የካቲት አርበኞቹ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በተሽከርካሪው ወደ ፍቼ የወሰዳቸው ስምኦን አደፍርስ ነበር፡፡ የፋሺስቶች የግፍ ሰለባ ስለሆነው ስምዖን አደፍርስ በጴጥሮስ ጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር በሚገኘው ሐውልቱ ላይ ገድሉን እንዲህ ጽፎታል፡፡

‹‹ወጣቱ አርበኛ ስምዖን (1905-1929) የአብርሃና የሞገስ የልብ ጓደኛ ነበር፡፡ ከአደጋውም በኋላ ከአዲስ አበባ ያሸሻቸው በታክሲ መኪናው ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ተይዞ ደጃች ውቤ ሠፈር በግራዚያኒ ወህኒ ቤት ማቅቆ አካሉ ከሰውነቱ ውጭ ሆኖ በመርዝ ተገደለ፡፡ ዘመዶቹ በድብቅ ቀበሩት፡፡››

የየካቲት 12ቱን ጥቃት በማቀነባበርና በመምራት ረገድ ተጠቃሽ የሚሆኑት በጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ (በኋላ ደጃዝማች) መሆናቸው ይወሳል፡፡ ይህንንም ያቀናበሩት ጀኔቭ የነበሩት በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በግራዚያኒ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ አማካይነት ባስተላለፉላቸው ትዕዛዝ መሠረት መሆኑ በኢትዮጵያ ጥናት ጆርናል ላይ ተመዝግቧል።

ካምቤል በጻፈው ድርሳኑ እንደገለጸው፣ ለአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም እነሱን ከመመልመል ጀምሮ ለተልዕኮው አስተዋፅዖ ያደረጉ ስብሐት ጥሩነህና ስምኦን አደፍርስ እንዲሁም ባሻህ ውረድ ሀብተ ወልድ ናቸው፡፡

መታሰቢያዎቹ

በፋሺስት ጣሊያን ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት ሠላሳ ሺሕ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ እንዲሆን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎና በአራት ኪሎ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሐውልቶች ቆመዋል፡፡

እነዚህን ሰማዕታት ለመዘከር ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በብሔራዊ በዓልነት እስከ 1966 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ሥልጣን ከያዘበት 1967 ዓ.ም. ወዲህ ግን በመሠረዙ እስካሁን ታስቦ እየዋለ ነው፡፡

ባለፉት ሩብ ዘመናት መታሰቢያ በዓሉ ዓመት ካመት እየቀዘቀዘ ጉንጉን አበባ የሚያስቀምጡት ሹማምነት ደረጃም እንደቀደመው ዘመን አገራዊ ከፍተኛ ሹማምንት መሆናቸው ቀርቶ የከተማዋ ተወካዮች የሚገኙበት ሆኗል፡፡

የሰማዕታቱ መታሰቢያ ዓመት ታመት በስምረት እየተከናወነ እንዳልሆነ የሚናገሩት የባህል ባለሙያው አቶ መንክር ገብሩ፣ የጣሊያን መንግሥት በአምስቱ ዓመታት የወረራው ዘመን ለፈጸመው ፍጅትና ጥፋት ለሊቢያ እንዳደረገው ሁሉ ለኢትዮጵያ ተገቢውን ካሳ መክፈል አለበት ይላሉ፡፡

ከዓመታት በፊት የታንዛንያ ፓርላማ ከምታመት በፊት ከ1905 እስከ 1907 በተካሄደው የነፃነት ተጋድሎ በማጂ ማጂ ነገድ አመፅ ላይ ጀርመን ለፈጸመችው ፍጅት፣ ካሳ እንድትከፍል መንግሥት ግፊት እንዲያደርግ እንዳሳሰበው ሁሉ ‹‹እኛስ ለምን አንጠይቅም?›› ሲሉ ያክላሉ፡፡