ልናገርግራጫ ታሪክ ሲዘከር – የካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ

አንባቢ

ቀን:

በተስፋዬ ወልደ ዮሐንስ ኃይሌ“የቀረ ሰው አለ”“አምና የተነሳ መንገድ የጀመረ

ካሰበበት ሊደርስ ወገቡን ያሰረ

ትናንት የነበረ ዛሬ ግን የሌለ ሰው አለ የቀረእኛስ ተገኝተናል ዘመን ተሻግረናልበለቅሶ ሸለቆ ሰንጥቀን አልፈናልእንደ ሻማ ቀልጦ እዚህ ያደረሰን አለ ሰው የቀረአጥንቱ እንደ ጀልባ ደሙ ባህር ሆኖ እኛን ያሻገረ፡፡”                        ዳዲሞስሁነቱ ከተፈጸመ ዘንድሮ አምስት አሠርት ዓመታት ዘልቆ ሃምሳኛ ዓመቱን ያዘ፡፡ በርካቶች ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ያካሂዱት የነበረውን ተጋድሎ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥቂቶች ከታሪኮቻችን አንዱ አካል አድርገው ለቀሪው ትውልድ አስፍረውታል፡፡ የወታደሩ ስብስብ የሆነው ደርግ ጨምሮ መኢሶንና ኢሕአፓን በሚያስታውሰን የዚያን ዘመን ታሪክ ውስጥ በኢትየጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ምናልባትም አይቻልም የተባለለትን ዘውዳዊ ሥርዓት ለመጣል የተቆረጠለት የመጨረሻው ወር የካቲት ነበር፡፡ይሁን እንጂ በገዳይና በአስገዳይ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር አብዮታዊን ጎራ የተካሄደው  በጦር በመሣሪያ ጭምር የታጀበ የከተማና የገጠር ትንቅንቅ የጊዜን አስከፊነት የሚገልጽልን፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም መግቢያ በር ላይ “መቼም የትም እንዳይደገም” ከሚለው ሐውልት ጎን፣ “በአንድ ሌሊት የወለድኳቸው ይመስል በአንድ ሌሊት ጨረሷቸው” የሚለው አራት ልጆቻቸውን በአንድ ሌሊት ያጡት እናት ወ/ሮ ከበቡሽ አድማሱ ቃል ድርጊቱን፣ ስሜቱን፣ ብሶቱንና ሥቃዩን በብዙ ገላጭ ይመስለኛል፡፡የካቲት 1966 ዓ.ም. እና ተያይዝው የነጎዱት ዓመታት በሟቾች ቁጥር በማይስማሙበት ወገኖች መሀል የወደቁና ለአገራቸው የሞቱ፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነፃነታቸው ነፍሳቸውን ከሥጋቸው በኃይል እንደትለይ የተደረጉ ወገኖቻችን ከቁጥርነት ባሻገር ለሰውነት፣ ለከንቱ ሳይሆን ለአገራቸው የነበራቸውን ፍቅር ስለመሆኑ ለማሰብ ጊዜና ዕውቀት ጠይቆናል፡፡ እስካሁንም ሁሉም አካላት በአንድነት የሚስማሙበት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያሻል፡፡የኢትዮጵያም ዘመን ከሌላው ዓለም የተለየ ባይሆን በየካቲት 1966 ዓ.ም. በያ ትውልድ ለነፃነት የተለኮሰው ችቦ ዓመታትን አልፈው እንኳ፣ ዛሬም ድረስ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ተስፋ አድርገው ዘመንንና ትውልድን ለመፍትሔ ተሸጋግረው ውጤቱን አንጋጠው በተስፋ ይጠባበቃሉ፡፡ ውጤቱ የምክንያቱንና የቁስለቱን ጠባሳ ያህል እንኳ ባይሆንም ቅሉ፡፡አንዳንድ ትውልዶች አንዳንድ ዘመናት ለውጦቹ፣ ትግሎቹና መስዋዕትነቱ ለቀሪው ዘመናት በታሪክ እየተነሱ እየተወጉ ይሸጋገራሉ፡፡ ከዚህን መሰል ትውልዶች መካከል በታሪካችን ውስጥ በ1966 የነበረው ያ ትውልድ ትልቁን ስፋራ ይይዛል፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ወደ ኃላ አምስት አስርት ዓመታት ጊዜ ተጎዞ እንኳ ዛሬም ድረስ ተፅህኖ ያለው ፤ ዛሬም ድረስ ዋጋ ያለው ትውልድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡የ1966 ዓ.ም. የዚያ ትውልድ አባላት በመንፈስ፣ በአካልና በሕይወት የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አያሌ ጓዶች ለተበደሉና ፍትሕ ላጡ ወገኖቻቸው ተቆርቁረው በዓላማቸው ፀንተው ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ግፍ ለደረሰባቸው ሰዎች ሲሉ በትግሉ ነበልባል ጋይተዋል፡፡ ያም ሆኖ የትግል ጉዳይ ነውና አንዳንዶቻችን ደግሞ  በሒደት፣ በአጋጣሚ ወይም በዕጣ ፈንታ ከእዚያ እሳት ተርፈው ኑሯቸውን ቀጥለዋል።  ተፅዕኖው ምንም እንኳ ይህንንም ዘመን ተሻግሮ የመጣ ቢሆን ቅሉ ሰንሰለቱ በተነሳበትና ለተነሳለት ዓላማ ሆኖ አይደለም ትውስታው፡፡ በተለያዩ ወገኖች በተደረገውና በርካቶችን ለአካላዊ ጉዳት፣ ለሕይወት መስዋዕትነት በዳረገው የየካቲት አብዮት ዓላማ የነበረን ጥንካሬ፣ ለዜጎች ድምፅነት የነበረን መከታነትና ለመስዋዕትነት የነበረን እሽቅድምድም ፍንትው አድርጎ ያሰየ ተዕይንት ነበር፡፡ መነሻውም መድረሻውም ያው ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋም፣ ፍትሕና እኩልነት ማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን ነበረ፡፡ችቦ  ይለኮስ እንጂ መያያዙን፣ መብራት ይጀምር እንጂ መቀጣጠል ተስፋ አላደረገም፡፡ ጥያቄዎቹ ይነሱ እንጂ ሁነኛ አመራርና ስትራቴጂ ከወዲህ ነው ብሎ አላላቸውም፣ መንገድም አላመላከታቸውም፡፡  ከዓመታት ጉዞ በኃላ እንኳ ዛሬም ጥያቄዎች እንደ አዲስ የሚጎመሩ፣ ማጀቢያቸው የተጎነጎነላቸውን ግን ተመልሰው በመፍትሔ ያልታጀቡ ሆነው ይስተዋላሉ፡፡እኔ ግራጫ የምለው ታሪክ በአግባቡ የተሰነደ፣ ለታሪክ የተቀመጠና በዚህኛው ትውልድ ይታወቅ ዘንድ የተፈቀደለት ከመሆን ይልቅ ትርክት ተበጅቶለት ያ ትውልድ፣ ያ ዘመን እየተባለ በተዛባ አነጋገር ውስጥ አጥፊ፣ አውዳሚ፣ በ‹‹ቸ›› እና በ‹‹ሸ›› ፊደላት ትርጓሜ የተጨፋጨፈ፣ ያ ትውልድ ካላለቀ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም የሚል አፅንኦት ይበዛበታል፡፡ማስታወሻቸው የነፃነት፣ የእኩልነት የዴሞክራሲ መስፈን የነበረው ዜጎቻችን ዋናው ሐውልታቸው መቆሙን የሚያውቁት በዘመኑ የተነሱለት ችቦ ከመለኮስ ወደ መንደድ፣ ከፍላጎት ወደ ድርጊት ተለውጦ ሲመለከቱ ይመሰለኛል፡፡ ለዚህም የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ትውልድ አባላት ከማለፋችሁ በፊት ታሪካችሁ ከገጠመው የተሳሳተ ትርክት አውጡት፡፡ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው tesfayewoldeyohanes.h@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡