ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ካሳ ተሻገር (ዶ/ር)፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ታዬ ደንደአ
የምስሉ መግለጫ,ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ካሳ ተሻገር (ዶ/ር)፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ታዬ ደንደአ

24 የካቲት 2024

በአማራ ክልል ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ለወራት በቁጥጥር ስር የሚገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት ካሣ ተሻገር (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት ተነሳ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ በጀመረው የ3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሚያካሂድበት ጊዜ ነው የከተማው ምክር ቤት የአባሉን ካሣ ተሻገርን (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት በአብላጫ ድምጽ ያነሳው።

ካሳ (ዶ/ር) የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ በመወዳደር ነበር ለከተማው ምክር ቤት እንደራሴነት የተመረጡት።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በክልሉ እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ ይሆናል በተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነበር ካሳ (ዶ/ር) በቁጥጥር ስር የዋሉ።

የከተማዋ ምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ለወራት በአዲስ አበባ እና በአዋሽ አርባ በእስር ላይ የቆዩ ሲሆን፣ ለስድስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጠናቀቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአራት ወራት እንዲራዘም ከወሰነ ከሳምንታት በኋላ ነው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ምክር ቤቱ የወሰነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የአባሉን ያለመከሰስ መብት ያነሳው የፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ፣ የምክር ቤቱ የሰላም፣ ፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ጥያቄ እንዲሁም ዝርዝር መረጃዎችን መርምሮ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ ካቀረበ በኋላ ነው።

ለወራት በእስር ላይ የሚገኙት እንደራሴው በተለያዩ ቦታዎች በቆዩበት ጊዜ የጤና እክል አጋጥሟቸው እንደነበረ ቤተሰቦቻቸው የተናገሩ ሲሆን፣ ባለፈው ጥር ለወራት ከቆዩበት የአዋሽ አርባ ወታደራዊ ማዕከል ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ጋር ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተው አለመረጋጋት ተከትሎ ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ቢያንስ አራት የተለያዩ ምክር ቤት አባልት ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለወራት በእስር ላይ ቆይተዋል።

እነሱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) እና የአማራ ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው።

በተጨማሪም ከተጠቀሱት የሕዝብ እንደራሴዎች በተለየ ሁኔታ እና ዘግይተው በቁጥጥር ስር የዋሉት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል እና የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአም ለሁለት ወራት ያህል ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በእስር ለይ ቆይተዋል።

በዚህ ሳምንት ውስጥም ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 16/2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳው ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) በተጨማሪ ሁለት ሌሎች የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታቸው ተገፏል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩትን የቀድሞው ሚኒስትር ዲኤታ እና የምክር ቤቱ አባልን ባለፈው ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ያለመከሰስ መብታቸውን አንስቷል።

በተጨማሪም የአማራ ክልል ምክር ቤት በእስር ላይ የሚገኙትን አባሉን የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት ባለፈው ሐሙስ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ማንሳቱን አሳውቋል።

ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 16/2016 ዓ.ም. ደግሞ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የካሳ ተሻገርን (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት በፍትህ ሚኒስቴር ጠያቂነት ማንሳቱን አሳውቋል።

በእረፍት ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላት የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) እስካሁን ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በእስር ላይ ይገኛሉ።

ምናልባትም ምክር ቤቱ ከእረፍት ሲመለስ በሚያደርገው ስብሰባ የቀሩትን ሁለት ታሳሪዎች ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ይችላል።