February 27, 2024 – Mereja.com 

ከቀሲስ አስተርአየ ጽጌ የከንሳስ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ

የነነዌ ጾም የትንግርታችን የንግርታችንና የትርክታችን ጥንቅር ናት፡፡ በዓለት አጿማት የሚውሉበትን እለታት ሳምንታትና ወራት ለማግኘት ማፈላለጊያ እማሬያችን ማለትም ምልክታችን ናት፡፡ ከሶስት ሺ ዘመናት በፊት የተፈጸመው የነቢዩ ዮናስንና የነነዌን ሰዎች ታሪክ እንደሚያስታውሰን፦ ንስሀ ለሚገባ ህዝብ መውጫ መንገድ የምታሳይ ናት፡፡ ከ200 መቶ አመታት በኋል በነቢዩ ናሆምና በነነዌ ሰወች የተፈጸመው ታሪክ እንደሚያሳስበንም ያለፈውን ታሪኩን ለረሳ ሕዝብ ሊጠገን በማይችል ጥፋት ውስጥ መግባቱን  እያሳየች የምታስጠነቅቅ ናት። የሕግና የሥርአት ባለቤት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴወስ ወንጌል 12 ም ዕራፍ ከቁጥር 38 እስከ 41 ላይ እንደተናገረው የነነዌ ጾም ለሚጠፋ ትውልድ የተሰጠች ምልክት ስትሆን ከዘላለማዊ ሞት የዳንበት የክርስቶስን  ትንሳኤ የምታሳይ ናት፡፡ ዮናስ በከርሰ አንበሪ ሶስት ሌሊትና ሶስት ቀን እንደኖረ ክርስቶስም ሶስት ቀንና ሌሊት ቆይቶ ሞትን አሸንፎ ድል መንሳቱን ለምናስታውስበት ለታላቁ ዓቢይ ጾም መግቢያ ናት፡፡

አባ ሕርያቆስ የቅድስት ድንግልን ቅድስናን በብዙ ምሳሌወች  በገለጹበት ድርሰታቸው “ዕጸ ሕይወት ዘሲሎንዲስ ወፈዋሲተ ቁስሉ ለናሆም” ብለው የጠቀሱትን  “አልቦ ፈውስ ለቁስላ ለነነዌ ” ብሎ ነቢዩ ናሆም የተናገረውን ትንግርትና ንግርት አባቶቻችን በታላቁ ጉብያቸው ሀተታ ላይ ጠቅሰው በተረጎሙበት  አንድምታቸው  የነነዌ ጾም  በንስሀ ከመከራ መውጫ የማሳያነቷና ለትንሳኤም ምልክትነቷ እንዳለ ሆኖ፡ ከሁለት መቶ አመት በኋላ የተነሱት የነነዌ ሰወች  በዮናስ ዘመን የተፈጸመውን ታሪካቸውን ረስተው ወደ ባሰ መታረም ወደማይችል ጥፋት ገብተው እንደጠፉ፡ አባቶቻችን ብትርጓሚያቸው እንዳስተማሩኝ እኛ ኢትዮጵያውያን ጾመ ነነዌን የምንጾመው የቀደመ ታሪካችንንና ትንግርታችንን ንግርታችንን  እረስተን መመለሻ ወደ ሌለው ጥፋት እንዳንገባ ትልቅ እማሬ (ጠቋሚ ) እንደሆነችን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋራ ከመላከ ሕይወት ሐረገ ወይን የሰማሁትን ደምሬ ብጠቅሰው  የዚህን አመት ገጠመኙን የበለጠ አድርጎ የሚያብራራልን ይመስለኛል፡፡

መላከ  ሕይወት ሐረገው ወይን እንደነገሩኝ፡ በተወለዱቡት ደብር ዓለምን የረሱ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ባሉት መቃብር ቤቶች ባንዷ ይኖሩ የነበሩ አንድ አዕምሯቸው የተወስደባቸው የሚመስሉ ሰው ነበሩ፡ ባንድ ሰሞን ካካባቢው ጠፉ፡፡ ሕብረተ ሰቡ ወዴት ጠፉ እያለ በመጥፋታቸው ተጨንቆ ሲነጋገርበት ከሰነበተ በኋል ሰንብተው ብቅ አሉ፡፡ ተመልሰው መምጣታቸው ሕዝባዊ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ የት ጠፍተው ነበር? ብለው ሰወች ጠየቋቸው ፡፡ “ሰይጣን ልጁን ድሮ  መሽራዋንና ሙሽራውን አጅቦ የሚሄድ የሰይጣን ሠርገኛ ሆታ ሰምቼ ተክትየ ሄጄ አብሬ ሰጨፍር ሰንብቼ መጣሁ አሉ” ፡፡ ሰወችም “የሰይጣኑ ሠርገኛ ምን እያለ ይጨፍር  ነበር?  ብሎ ጠየቋቸው ፡፡ “እየበሰ እየባሰ እየባሰ ኄደ” የሚል ነበር” ብለው መለሱ፡፡

2016 ዓመተ ምህረትን የተርንተራሰች የነነዌ ጾም አዝላ ብቅ ያለችው እኒህ አዕምሯቸው የተወሰደባቸው ሰው “እየባሰ ሄደ” ያሉትን የሚያስታውስ መሰለኝ፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያና በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ መንግሥት የጀመረው መከራና እልቂት እየከፋና እየባሰ ቀጥሎ አምና ሻሸመኔ ላይ ብዙ ሰው ታረደ፡፡ መታረዱ አልበቃ ብሎ ሲኖዶሱ ጥቁር አስለብሶ የተረፈውን ሕዝብ አሰፈጄ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ እጅግ በከፋ ሁኔታ በጎጃም በወሎ በጎንደር በሸዋ ገዳማት አድባራት ተቃጠሉ፡፡ የዝቋል ገዳም መነኮሳት ታረዱ።

በዘንድሮዋ ጾመ ነነዌ ሌላም የሚዘገንን የከፋና የባሰ ያረመኔ ተግባር ተክስቶ አይተናል፡፡ ሰምተናል፡፡ የኔታ ዩቱብ ለህዝብ ቀርቦ አንድ ቆሞስ አንዲትን መነኩሲት ደፍሮ ካስወለደ በኋል ኃጢአቱን ለመሸፈን መነኩሲቱንም   የተወልደችውንም ሕጻን ለማጥፈት እያደረገ ያለውን የባሰና የከፋ  ያረመኔ ተግባር እየሰማን ነው፡፡ ይህች በቆሞስ የተደፈረችው መነኩሲት ልጅ ብትሆንም፡ ምንኩስናዋና ንጽህናዋ ሕሊናው በኃጢያት በጨቀየው ወምበዴ ተገዳ ብትደፈርም፡ ምንኩስናዋና ንጽሕናዋ አልተደፈረም አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ለምንኩስናዋ ይሰጣት የነበረው አንቱታ አሁንም እንዳለ ሊጠበቅላት ይገባልና አንቱ እያልኩ እናገራለሁ፡፡ እኒህ እሟሂቷ ወገናችን “ከኔ መደፈር ይልቅ እጅግ ያበሳጨኝና ያስቆጨኝ እኔን ከደፈረ በኋላ  ወደ ቤተ መቅደስ ደፍሮ በመግባት መባረኩንና ቀድሶ ማቁረቡን ማየቴ ነው”  ብለው በቁጭት የተናገሩት ከመደፈራቸው በፊት ከነበራቸው ሕሊናዊ ጽርየት ይልቅ ከተደፈሩ በኋላ ያንጸባረቁት የሕሊና ጽርየት በእሳት ከተፈተነ ወርቅ ይልቅ እጅግ የላቀ ያርባኛነት ባሕርይ ሆኖ አይቸዋለሁ፡፡ በሲኖዶሱ ዙሪያ የተሰበሰቡት ከደፈራቸው ካረመኔው ቆሞስ ጋራ በተመሳሳይ ባሕርይ ባይበከሉ ኖሮ ለኒህ ንጽሕት መነኩሲት ከትልቅ ሽልማት ጋራ ልዩ የመጠልያ ቦታ ባዘጋጀላቸው ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ፦ የ2016 ጾመ ነነዌ በኒህ ክብርትና ንጽሕት እሙሐይ የተከሰተው ጉድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰው መከራ እየባሰና እየከፋ መሄዱን አጠንክሮ አሳይቶኛል፡፡ ከመግቢያ ላይ እንዳልኩት የነነዌ ጾም የትንግርታችን የንግርታችንና የትርክታችን ጥንቅር ናት እንዳልኩት፡ በንጽሕት እሙሐይቷ እናታችን ወይም እኅታችን የተከሰተ ጉድ ከነነዌ ወቅት ጋራ ተጣምሮ ብቅ በማለቱ ላለማለፍ ጠቀስኩት እንጅ ብቻውን ተለይቶ በሰፊው የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡

ከ7 አመታት በፊት ኢትዮጵያ በነበረችበት ሁኔታ ላይ ሆኜ  በወቅቱ የተሰማኝን “ኢትዮጵያና ጾመ ነነዌ” በሚል ያቀረብኩትን  ቤተ ክርስቲያኑ በዩቱብ ቀርጾት ብዙ ሰው ተካፍሎት ነበር፡፡ ከዚያ በፊትና ከዚይም ወዲህ የሚተካካው ምንግሥት በመከራ አስቀጣይነት እየከፋ ቀጠለ።

በ2016 ዓመተ ምሕረት ላይ  ያለው የብልጽግና ምንግሥት ብግድያው እየባሰ ሄደ፡፡ በዚህ ዘመን ያለው ሲኖዶስም ግድያውን እያባሰ በማስቀጠል ላይ ካለው መንግሥት ጎን ተሰልፎ “እየባሰ ሄደ” የሚለውን በማጨብጨብ መከራው ይበል ይቀጥል የሚል  ይመስላል፡፡  ከ 7 አመታት በፊት የከንሳስ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቀርጾ ለህዝብ የለቀቀውን ዩቱብ የተመለከቱ ወገኖች ይዘቱ ገርሟቸው ከዚህ ቀደም  የተመለከተውን ወገን ለማሳሰብና ያልተመለከተው ወገንም ተመልክቶ የራሱን ግንዛቤና  ትዝብት እንዲወስድ እንደገና ይቅረብ የሚል ጥያቄ ስላቀረቡ  እነሆ ዩቱቡ በድጋሚ ቀረበላችሁ፡፡

ማሳሰቢያ ለቀሳውስት፦

ቤተ ክርስቲያናችን ላብነት (ላባትነት) ትምህርት ከምታዘጋጅበት ከቆሎው ትምህርት በኋላ፡ ባብነቱ (ላባትነት በሚያበቃው በጉባኤው ትምህርት) ሳታልፉ አባት በመሆን “ዕጸ ሕይወት ዘሲሎንዲስ ወፈዋሲተ ቁስሉ ለናሆም” (ቅ.ማ . ቁጥር 36 ) የሚለውን ያባ ሕርያቆስን ድርሰት የምትቀድሱ የዘመኑ ቀሳውስቶች ሆይ!  ደፈረን ብላችሁ ስሜን በማጥፈት በኔ ላይ ከመዝመት ይልቅ፡ የኢትዮጵያዊነትን ፍቅር በደም ውስጥ በሚከሰክሰው በሊቃውንት አባቶች ጉባኤ የማለፉ እድል ባይገጥማችሁም፦ በ4 ምዕራፎች የተወሰነውን የነቢዩ ዮናስን መይጽሐፍና በ3 ምዕራፎች የተወሰነውን የነቢዩ የናሆም መጽሐፍ በማነጻጸር አንብቡ ቪዲዮውንም ስሙት፦ እናነተን ለሚከተለው ሕዝብም አካፍሉት፡፡

https://youtube.com/watch?v=L0RxSLwRnZE%3Fversion%3D3%26rel%3D1%26fs%3D1%26autohide%3D2%26showsearch%3D0%26showinfo%3D1%26iv_load_policy%3D1%26start%3D1%26wmode%3Dtransparent