የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ የሥራ ሁኔታች ቁጥጥርና የኢንዱስትሪ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ተካልኝ አያሌው (ዶ/ር)

ዜና በአፍሪካ ተመሳሳይ የፍልሰት ሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በአሠራር ላይ ክፍተት መፍጠሩ ተነገረ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: February 28, 2024

የአፍሪካ አገሮች አንድ ዓይነት የፍልሰት አስተደደር ቅኝት ውስጥ ባለመሆናቸውና ተመሳሳይ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ስለሌላቸው፣ በአሠራር ላይ ክፍተት መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጋር በመተባበር፣ አምስተኛውን የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ አገሮች ሚኒስትሮች ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች ፎረም ሲያካሂድ ነው፡፡

ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም.  ለአራት ቀናት በሚቆየው የምሥራቅ አፍሪካ የሚኒስትሮች የፍልሰት ጉዳዮች ፎረም ኢትዮጵያን ጨምሮ አሥራ አንድ የቀጣናው አባል አገሮች፣ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮች መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ የሥራ ሁኔታዎች ቁጥጥርና የኢንዱስትሪ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ተካልኝ አያሌው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የሚኒስትሮች የፍልሰት ጉዳዮች ፎረም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ለውጦች ቢኖሩም፣ አባል አገሮች የሚጠቀሙበት የአሠራር የተለያየ ስለሆነ ክፍተቱ የጎላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በቀጣናው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሰዎች ፍልሰት ለመቆጣጠር አገሮች የየራሳቸው የፍልሰት አስተዳደር ፖሊሲ እንዳላቸው ገልጸው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ነፃ የሰዎች ዝውውር እንዲኖር የሕግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖር የፍልሰተኞችና የስደተኞች መብት ከማስበር ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ፎረሙ የተቋቋመበት ዋነኛ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ የፍልሰት አስተዳደር ሒደቱን ለማሻሻል እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከምልመላ፣ ከሥልጠና፣ ከሥምሪት፣ እንዲሁም ዜጎች ተመልሰው አገራቸው እስኪገቡ ድረስ ያለውን እንቅስቃሴ የተሻለ ለማድረግ የአሠራር ንድፈ ሐሳብ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚፈልሱ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነሱ በትክክለኛ መንገድ ሥራ እንዲያገኙና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የተሻለ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለአራት ቀናት በሚቆየው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ፎረም ላይ እያንዳንዱ አገሮች የየራሳቸውን ተሞክሮ እንደሚቀያቀርቡ ገልጸው፣ ይህንን አሠራር በሚያቀርብበት ጊዜ አንዱ ከአንዱ አገር ልምድ የሚወስድበት አጋጣሚ የሚፈጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት በቀጣይ በምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወጥ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓትና የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር አገሮቹ በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውሰዋል፡፡

የፍልሰተኞች ጉዳይ ለቀጣናው ከፍተኛ ሥጋት እየሆነ መምጣቱንና ችግሩም የሁሉም አገሮች በመሆኑ፣ አስፈላጊውን አሠራር መከተል እንደሚገባ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አቢባቶው ዋኔ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዘርፉ ከቀጣናው የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን ገልጸው በፎረሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኡጋንዳ፣ የሩዋንዳ፣ የታንዛኒያ የብሩንዲ፣ የኤርትራና የጂቡቲ ተወካዮች መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡