የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ታይገር ቻጉታህ

ዜና በአማራ ክልል ከፍርድ ውጪ ግድያ የፈጸሙ የመንግሥት አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል…

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: February 28, 2024

በአብርሃም ተክሌ

በአማራ ክልል ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች እንዲቆሙና በግድያ የተሳተፉ የመንግሥት አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥያቄ አቀረበ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይላት ከፍርድ ውጭ የሚፈጸሙ ግድያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን፣ በተለይም ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ስድስት ሰላማዊ ሰዎች ከፍርድ ውጪ በግፍ መገደላቸውን አመልክቷል።

ሪፖርቱ ሰላማዊ ሰዎቹ የተገደሉት በከተማዋ ቀበሌ 14 ውስጥ በሚገኙ አቡነ ሃራና ልደታ በተባሉ ሥፍራዎች እንደሆነ ገልጾ፣ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ ሰባታሚት በተባለው የከተማዋ አካባቢ አምስት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ያለ ፍርድ በመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደተገደሉ ገልጿል። በወቅቱ ከተገደሉት መካከል ጤና ጣቢያ ውስጥ ሕክምና ላይ የነበሩ አንድ ታካሚና በአካባቢው የነበሩ ሦስት ወንድማማቾች ይገኙበታል ብሏል።

በአቡነ ሃራና ልደታ በተባሉ ሥፍራዎች ከተፈጸሙ ግድያዎች በኋላ የሰብዓዊ መብት ተቋሙ ከዓይን እማኞችና የቤተሰብ አባላት ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ሰላማዊ ሰዎቹ የተገደሉት በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት መሆኑን ገልጿል።ከፍርድ ውጪ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ ወ/ሮ ይታጠቁ አያሌው መሆናቸውን፣ ልደታ አካባቢ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ በመንግሥት ወታደሮች በጥይት ተመትተው መሞታቸውን የተመለከቱ በርካታ ምስክሮችን ጨምሮ የ17 ዓመት ዕድሜ ያለው የቅርብ ዘመዳቸው መናገሩን፣ ነሐሴ 2 ቀን ጧት ይታጠቁ እንጀራ እየጋገሩ የተኩስ ድምፅ መሰማት እንደጀመረ መግለጹ ተመልክቷል፡፡አምነስቲ በአንዳንድ ሁኔታዎች ቤተሰቦች የሟቾችን አስክሬን እንዳይቀብሩ እንደተከለከሉም በሪፖርቱ ላይ ሲያመላክት፣ መንግሥት በባህር ዳርና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ በአስቸኳይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲጀምር ጠይቋል።‹‹ግንኙነት ተቋርጧል፣ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ጫናዎች ተፈጥረዋል፣ ትክክለኛ መረጃዎች ማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል፤›› ያለው አምነስቲ፣ የተፈጸሙትን ግድያዎች የተመለከተው ሪፖርት ከረዥም ጊዜ በኋላ ያወጣውም በእነዚህ ጫናዎች ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን (IHL) በመተላለፍ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ከባድ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ከጦር ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክቷል። በማከለም ያለ ፍርድ ግድያ መፈጸም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ መሠረት በሕይወት የመኖር መብትን መጣስ መሆኑን ገልጿል።‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ወንጀል ፈጻሚዎች ተዓማኒ በሆነ የፍርድ ሥርዓት ተጠያቂ ባለመሆናቸው ወንጀሎች ተደጋግመው እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል፤›› ያሉት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ታይገር ቻጉታህ፣ ‹‹በመላ አገሪቱ የሚታየው የፍርድ መጓደል እንዲያበቃና የዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት ባደረገ መንገድ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጊዜው አሁን ነው፤›› ብለዋል፡፡የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባወጣቸው ሁለት ሪፖርቶች የችግሩን አሳሳቢነት የገለጸ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 2021 እስከ ጥር 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በታጠቁ ኃይሎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያለ ፍርድ ግድያ፣ የአካል ጉዳትና አፈና መፈጸሙን ጨምሮ ገልጿል፡፡ እንደ ሪፖርቶቹ ከሆነ ሲቪሎች ዒላማ የተደረጉት እነሱ ወይም የቤተሰብ አባላት በግጭቱ ውስጥ የፈጻሚዎቹ ተቃዋሚዎች ስለሆኑ ወይም ስለሚደግፉ ነው ብሏል።  በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመከሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ሞሊ ፊ እና የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው ነበር። ሞሊ ፊ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ሰላምን እንዲሰፍንና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና መነጋገራቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ማይክ ሐመር በበኩላቸው በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየታየ ነው ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመጥቀስ፣ መንግሥት ለዜጎች ከለላ እንዲያደርግና ወንጀለኞችን ተጠያቂ እንዲያደርግ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡መንግሥት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየቀረበበት የሚገኘውን ተደጋጋሚ ክስ በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም።