ሊዮኒድ ዛኩተንኮ የተባለው መርዝ ሻጭ
የምስሉ መግለጫ,ሊዮኒድ ዛኩተንኮ የተባለው መርዝ ሻጭ

ከ 1 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ኪንግደም ቢያንስ 130 ሰዎች ራሳቸውን አጥፍተውበታል የተባለውን መርዝ የሸጠውን ዩክሬናዊ ቢቢሲ ተከታትሎ ደርሶበታል።

ሊዮኒድ ዛኩተንኮ የተባለው ይህ ግለሰብ ራስ ማጥፋትን የሚያበረታታበት እንዲሁም አገልግሎቱን የሚያስተዋውቅበት ድረ ገጽ አለው።

ግለሰቡ ለቢቢሲም ምሥጢራዊ ዘጋቢ በየሳምንቱ አምስት እሽጎችን ወደ ዩናይትድ ኪንድም (ዩኬ) እንደሚልክ ተናግሯል።

ግለሰቡ ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር ከዋለው እና በ14 የግድያዎች ወንጀል ከተከሰሰው ካናዳዊ ኬኔት ሎው ጋር ተመሳሳይ ንጥረ ነገር ሲያቀርብ ቆይቷል።

ቢቢሲ ንጥረ ነገሮቹን በተመለከተ ያቀረበለትን ጥያቄ ሊዮኒድ ውድቅ አድርጎታል።

ቢቢሲ ግለሰቡ ወደሚኖርበት ዩክሬን መዲና ኪዬቭ መኖሪያ ቤቱ ድረስ አቅንቶም ገዳይ የሆነውን ኬሚካል ስለመሸጡ ቢጠይቀውም አላመነም። ቢቢሲ የዚህን ንጥረ ነገር (ኬሚካል) ስም አይጠቅስም።

ግለሰቡ ባያምንም ነገር ግን ቢቢሲ በምርመራው ይህንን ገዳይ ንጥረ ነገር ለዓመታት ሲያቀርብ እንደቆየ አረጋግጧል።

ኬሚካሉ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ሊሸጥ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው አሳማኝ ለሆኑ ግልጋሎቶች ብቻ ለሚጠቀሙ ኩባንያዎች ነው።

ንጥረ ነገሩን ለምን ተግባር እንደሚውል መሠረታዊ ምርመራ እና ፍተሻ ካላደረጉ በስተቀር አቅራቢዎች ለደንበኞች መሸጥ የለባቸውም።

ንጥረ ነገሩ በአነስተኛ መጠን ቢወሰድ እንኳን ለሞት ሊዳርግ ይችላል።

ሊዮኒድ ዛኩተንኮ የተባለው መርዝ ሻጭ
የምስሉ መግለጫ,ሊዮኒድ ዛኩተንኮ የተባለው መርዝ ሻጭ

“በጭካኔ የተሞላ”

ባለፈው ዓመት ይህ ግለሰብ በለንደን ነዋሪ ለሆኑት መንታ እህትማማቾች ሊንዳ እና ሳራ መርዝ ከሸጠላቸው በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

የሁለቱ እህትማማቾች ቤተሰቦችም ስለዚህ ግለሰብ ሲያወሩ “በጭካኔ የተሞላ እና ክፉ ሰው ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

ከእህትማማቾቹ አንዷ ሊንዳ ስለ መርዝ ሻጩ መረጃ ያገኘችው እውቅና ባለው ራስን የማጥፋት የውይይት መድረክ ላይ እንደሆነ እህቷ ሄለን ኪት ትናገራለች። እህቷ በጥቂት ፓውንድ የሞት ጽዋዋን እንደቀመሰች ተናግራለች።

ራሷን ስላጠፋችው የ54 ዓመት እህቷ ስትናገር “አሳቢ፣ አስተዋይ እና ጎበዝ ነበረች” ስትል ታስታውሳታለች።

እህቶቿም ሆነ ሌሎች በርካታ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ኬሚካሉን እንዳያገኙ ባለሥልጣናት የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩን በመተቸት “ብሔራዊ ቅሌት” ነው ስትል ሄለን ውቀሳለች።

ግለሰቡ የሚሸጠው ኬሚካል እነ ሊንዳ በሚጠቀሙበት የበይነ መረብ መድረክ ላይ በግልጽ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን፣ አባላቶቹም እንዴት እንደሚገዙ እና እንደሚጠቀሙበት ምክር ይለዋወጣሉ።

በለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርስቲ ሳይንቲስት የሆኑት ፕሮፌሰር አምሪታ አህሉዋሊያ በበኩላቸው ኬሚካሉ በዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ከተከሰቱት 130 ራስን ማጥፋቶች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ፕሮፌሰሯ በፖሊስ እና በላብራቶሪዎች የተላኩላቸውን ደም እና ሌሎች ናሙናዎችን በመመርመራቸው ነው እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የደረሱት።

ከመረመሯቸው 187 ናሙናዎች ውስጥ 71 በመቶው ገዳይ የሆነ ኬሚካል መኖሩን የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህን ቢያንስ 133 ሰዎች በዚህ ንጥረ ነገር እንደሞቱ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

“አንድ ነገር ሊደረግ ይገባዋል” ሲሉም ፕሮፌሰሯ ያሳስባሉ።

“ለምን ጥቅም ላይ እንደሚውል ሙሉ ምርመራ ሊደረግ ይገባል። አጠቃቀሙ ለታለመለት ዓላማ ይውል ዘንድም ቁጥጥር መደረግ አለበት” ይላሉ።

ካናዳዊው ኬኔት ሎው

የግድያ ክሶች

ምግብ አብሳይ የሆነው ካናዳዊው ኬኔት ሎው ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በ14 የግድያ ወንጀሎች እና ራስን ማጥፋትን በማገዝ ክስ ቀርቦበታል።

ግለሰቡ ኬሚካሉን በዓለም ዙሪያ ባሉ 40 አገራት ሸጧል። ከ1 ሺህ 200 በላይ ሽያጮችን አካሂዷል የተባለው ይህ ግለሰብ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ራሳቸውን ባጠፉ 93 ሰዎች ሞት ውስጥም እጁ አለበት ተብሏል።

ቢቢሲ ባደረገውም ምርመራ ሊዮኒድ ዛኩተንኮ የተባለው ግለሰብ ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ ተመሳሳይ ኬሚካል እየሸጠ መሆኑን አረጋግጧል።

በተጨማሪም በበይነ መረብ ላይ ራስን የማጥፋት መመሪያዎች ውስጥ የተካተቱ ሦስት የተለያዩ በህክምና ባለሙያ የሚታዘዙ መድኃኒቶችንም ያቀርባል።

ካናዳዊው ኬኔት ሎው ራስን ማጥፋት በሚያስተዋውቅበት የበይነ መረብ መድረክ ላይ ይህም ግለሰብ ለአጭር ጊዜ አገልግሎቱን ያስተዋውቅ ነበር።

ከዚያን ጊዜም ጀምሮ የመድረኩ ተጠቃሚዎች የእሱን አድራሻ በመልዕክቶች ይቀያየሩ ነበር።

ቢቢሲ ሊዮኒድ ዛኩተንኮንን ያገኘው በዩክሬን መዲና ኪዬቭ በሶቪዬት ኅብረት ዘመን በተሠራ ህንጻ ውስጥ በሚገኝ አነስተኛ የጋራ መኖሪያ ቤት ነው።

በርካታ እሽጎችንም ለመላክ በአካባቢው ፖስታ ቤት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው ቢቢሲ የተጋፈጠው።

ራሳቸውን ለማጥፋት ለሚፈልጉ ሰዎች ለምን መርዛማ ኬሚካል እንደሚልክም ተጠየቀ።

እጁን የቢቢሲ ካሜራን ለመሸፈን ከመሞከሩ በፊት “ይህ ውሸት ነው” በማለት ለማስተባበል ሞክሯል።

ቢቢሲም ዛኩተንኮንን በዚያች ቀን እሽግ እንዲልክለት መጠየቁን ተከትሎ ቢያንስ አንዱ እሽግ ኬሚካል እንደያዘ ለማረጋገጥ ችሏል።

ቤተሰቦቻቸውን በዚህ ኬሚካል ላጡ ሰዎች ምን ምላሽ አለህ? ተብሎ በቢቢሲ ሲጠየቅም “ስለምን እንደምታወሩ አልገባኝም” ሲል መልሷል።

ራሳቸውን ያጠፉት ቶም እና ጆ ኒሂል
የምስሉ መግለጫ,ራሳቸውን ያጠፉት ቶም እና ጆ ኒሂል

ጠንካራ እርምጃ

ዴቪድ ፓርፌት የተባለ ግለሰብ የ22 ዓመት ልጁ ቶም ተመሳሳይ ኬሚካል ከኬኔት ሎው ገዝቶ ከሦስት ዓመታት በፊት ሕይወቱን አጥፍቷል።

ፓርፌት በአሁኑ ወቅት ከራስ ማጥፋት ጋር የተያያዙ የውይይት መድረኮችን ለማዘጋት እና እንደ ዛኩቴንኮ ያሉ መርዝ ሻጮችን ለማስቆምም ዘመቻ እያደረገ ይገኛል።

ሌላኛው የ23 ዓመት ጆ ኒሂል የተባለ ወጣት ሞት መንስዔን የመረመረው ባለሙያ ማስጠንቀቂያ ለብሪታንያ ባለሥልጣናት መድረሱን ተከትሎ ስለ ኬሚካሉም ሆነ በበይነ መረብ ላይ ስለሚፈጸመው የመርዝ ንግድ ከአውሮፓውያኑ መስከረም 2020 ጀምሮ እንደሚያውቁ ይፋ ሆኗል።

መርማሪው ለፖሊስ፣ ለአስከሬን መርማሪ ዋና ኃላፊ እንዲሁም ለኬሚካል አቅራቢዎች ስለ አደገኛው ንጥረ ነገር ንግድ አስጠንቅቆ ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመላው ዩኬ የሚገኙ የአስከሬን መርማሪዎች ስለ ኬሚካሉ እና ራስን ስለ ማጥፋት እየተደረጉ ስላሉ የበይነ መረብ የውይይት መድረኮችን በተመለከተ አምስት ጊዜ ያህል ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ማስጠንቀቂያ ጽፈዋል።

ዴቪድ ፓርፌትም ባለሥልጣናቱ እሽጉን ያስቆሙት እንደሆነ ለማየት እና ሥርዓቱንም ለመፈተሽ ከዛኩተንኮ መርዛማውን ኬሚካል ገዝቷል።

እሽጉን ካዘዘ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፖሊስ ደኅንነቱን ለመጠበቅ ጎበኝቶት ነበር። ነገር ግን ኬሚካሉ በሳምንታት ውስጥ የደረሰው ሲሆን፣ ፖሊስም እንደገና አልጎበኘውም።

“ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እያወቅን አሁንም እንዲህ ዓይነት ነገር ይከናወናል ብሎ ማመን ከባድ ነው” ሲልም ተናግሯል።

ኬኔት ሎው በካናዳ ከታሰረ በኋላ በዩኬ ውስጥ ንጥረ ነገሩን በሚገዙ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ የደኅንነት ማረጋገጫ ጉብኝቶች ተካሂደዋል።

የዩኬ የብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ እንዳረጋገጠው ኬሚካሉን ከኬኔት ሎው ገዝተው ፖሊስ የደኅንነት ጥየቃ ካደረገ በኋላ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጧል።

“እንዲህ አይነት ጉዳዮች የሚስተናገዱት በፖሊስ አባላት አማካይነት ፖሊሲያቸውን እና ብሔራዊ መመሪያዎችን ተከትሎ ነው” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የሚወዷቸውን ሰዎች በኬሚካሉ የተነጠቁት ዴቪድ ፓርፌት እና ሄለን በእነዚህ የራስ ማጥፋት የውይይት መድረኮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ እየጠየቁ ይገኛሉ።

የዩኬ መንግሥት በበኩሉ ባለፈው ዓመት የጸደቀው አዲሱ የበይነ መረብ ደኅንነት ሕግ እንደነዚህ ዓይነት የውይይት መድረኮችን በመገደብ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግሯል።