
ቀን: March 3, 2024
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት ክልሎች ሊያካሂደው ላቀደው ምርጫ የሚያስፈልገውን 304 ሚሊዮን ብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀለት ቢሆንም እስካሁን እንዳላገኘ አስታወቀ፡፡
በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ በቦርዱ ውሳኔ ምርጫ ባልተካሄደባቸውና በድጋሚ ምርጫ በሚደረግባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች፣ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ምርጫው እንደሚከናወን ቦርዱ ዓርብ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በነበረው ውይይት አስታውቋል፡፡
በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ፣ ምርጫ ያልተካሄደባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 96 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ትግራይ 38፣ ኦሮሚያ 8፣ አማራ 19፣ አፋር 9፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 19፣ ደቡብ 2፣ እንዲሁም ሶማሌ 1 ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ምርጫዎች ያልተካሄዱት በፀጥታ ችግር እንደሆነ ባለፈው ዓመት ቦርዱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ
ይሁን እንጂ ቦርዱ በተያዘው 2016 የበጀት ዓመት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ይፋ ባደረገው ፕሮገራም ከአራቱ ክልሎች ውጪ ምርጫው ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ለማካሄድ የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑን የቦርዱ ምንጮች ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ በፓርላማ ሹመታቸው የፀደቀላቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በሰጡት ማብራሪያ ግን፣ በ1,146 የመደበኛ ምርጫ ጣቢያዎችና በ34 የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ጣቢያዎች በሚደረገው ምርጫ፣ ለዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለ26 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ውድድር ይደረጋል፡፡ ለዚህም 5,730 የምርጫ አስፈጻሚዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
ምርጫውን ለማካሄድ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች ተከናውነው መጠናቀቃቸውን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ከዚህ በኋላ የሚኖሩት ክንውኖች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ቢሆኑም በጀቱ እስካሁን አልተለቀቀም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ቦርዱ ለምርጫው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አቅርቦ እየተጠባበቀ መሆኑን፣ በጀቱ እንደተለቀቀ ወጪ ወደ የሚያስፈልጋቸው ተግባራት እንደሚገባ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ በጀቱ ባይለቀቅለትም ሥራ ጀምሮ ዝግጅት እያደረገ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በነበረው የቅድመ ዝግጅት ሒደት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ፣ ከዚህ ቀደም በምርጫ የተሳተፉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ፈቃደኝነት መጠየቅ፣ ለቀጣይ ምርጫ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ አባላቶቻቸው በቀጣዩ ምርጫ መካፈል አለመካፈላቸውን ማረጋገጥና በቦርዱ የውስጥ አሠራር መሠረት ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቦርዱ ሰብሳቢ እንደገለጹት የቀጣይ ሥራ ማከናወን የሚቻለው ቦርዱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የሚሆነው በጀት ሲለቀቅ በመሆኑ፣ ገንዘቡ እንደተለቀቀ በቀጥታ ወጪ ወደ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በመግባት ይሆናል ብለዋል፡፡
ለቀጣዩ ምርጫ ከተጀመሩ የዝግጂት ሒደቶች መካከል ከጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የምርጫ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ዘመቻ ከሚያዝያ 7 ቀን እስከ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ማድረግ፣ የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ የሚገለጸው በምርጫው ማግሥት ሰኔ 6 እና 7 እንደሚሆን፣ በቦርድ የተረጋገጠ ውጤት ደግሞ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ቦርዱ መጀመሪያ ምርጫውን ለማከናወን አቅዶ የነበረው በግንቦት 2016 ዓ.ም. አጋማሽ የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት በጀቱን በወቅቱ ባለመልቀቁ የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት ከአገር ውጪ የሚከናወን በመሆኑና የመንግሥትን የግዥ ሒደት መጠበቅ በማስፈለጉ ወደ ሰኔ 2016 ዓ.ም. እንዲሸጋገር መደረጉን ወ/ሮ ሜላተወርቅ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች መንግሥት በጀት ለምን ሊለቅ እንዳልቻለና አሁንስ የበጀቱ ጉዳይ ምን ተስፋ እንዳለው፣ ግጭትና የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫው አያደናቅፍም ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋ ገመቹ፣ ቦርዱ የምርጫ ቁሳቁሶችን ለማስተላለፍ አሁን ካለው የፀጥታ ችግር አኳያ እንዴት ሊያከናውነው አስቧል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹‹መንገዶች ምቹ ናቸው ወይ? ምርጫውን በተጠቀሰው ጊዜ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ወይ?›› በማለት ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹በእኛ ድርጀት ዕይታ ሁኔታውን ስንመለከት ምርጫው በአጭር ጊዜ ሊቋጭ ቢችል ምኞታችን ነው፡፡ ነገር ግን ሁኔታው እንደዚያ ዓይነት ነገር አያሳይም፣ በየቦታው ድንገት የሚፈነዱ ግጭቶች እየታዩ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የቦሮ ዴሞክራሲ ፓርቲ ተወካይ አቶ ዮሐንስ ተሰማ በበኩላቸው፣ ቦርዱ በጀቱን ከጠየቀ ወራት አልፎት መንግሥት ይህን ገንዘብ ለምን አለቀቀም? ምርጫ እንዳይካሄድ ይፈልጋል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ አክለውም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ያለው መንግሥት በኢሕአዴግ አስተዳደር ማለትም በ2007 ዓ.ም. በነበረው ምርጫ የተመረጠ ስለሆነ፣ አሁን ምርጫ ካልተካሄደ መቼ ሊደረግ ይችላል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ምርጫው እንዲካሄድ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምርጫው ሊካሄድ አለመቻሉ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ መንግሥት ገንዘብ ካለቀቀለት ምንስ አስቧል ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ የተገኙ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባል፣ ‹‹ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ መርሐ ግብር አዘጋጅተን እንድንቀሳቀስ ቦርዱ የሚያስፈልገው ገንዘብ ተለቆለት ወደ ሥራ ልንገባ ይገባል፡፡ በደመነፍስ በጀት ይፈቀዳል በሚል አላስፈላጊ ችግር ውስጥ መግባት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ የፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ በየጊዜው የፀጥታ ሁኔታ የዳሰሳ ሪፖርት እየቀረበ እንደሚታይ፣ በየጊዜው ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚኖር ውይይት እየተገመገመ በቀጣይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
የምርጫ ማስፈጸሚያ በጀትን በተመለከተ በተደጋጋሚ በጀት እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውንና እየጠየቁ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹በዚህ በተጣበበ የጊዜ ሰሌዳ ከተለቀቀ የቦርዱ ሠራተኞች ቅዳሜና የበዓል ቀን ጭምር በመሥራት ምርጫውን እናካሂዳለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በጀቱ መለቀቁ ግድ ነው፣ ሌላውን ዝግጅት አጠናቀናል፣ አለበለዚያ የሚያስኬደን አይደለም፡፡ በጀት ይለቀቃል የሚል ተስፋ አለኝ፣ ይለቀቅልናል፡፡ ከተለቀቀልን ቀጥታ ወደ ግዥ በመግባት ለሥልጠና የሚያስፈልጉ ግዥዎችን መግዛት፣ ምርጫ አስፈጻሚ መልምሎ ለሥልጠናና ሥምሪት ዝግጁ የማድረግ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡