EthiopianReporter.com 

ተመስገን ተጋፋው

March 3, 2024

ለውጭ ገበያ 60 በመቶ የአበባ ምርት የሚልኩ የሰባት ኩባንያዎች የአበባ እርሻ በከፍተኛ የ‹‹እሳት እራት›› በተሰኘ ተባይ መጠቃቱን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማኅበር ጋር በመተባበር፣ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ በተመለከተ፣ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአበባ አምራች ኩባንያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ‹‹Plant Health Unit of DG Santé›› ኢትዮጵያና ኬንያ የአበባ ምርቶችን ሲልኩ፣ የእሳት እራት የተባለው ተባይ ወደ አውሮፓ ኅብረት አገሮች ከገባ፣ በአየር ንብረት ምክንያት ባህሪውን በመቀየር የዕፅዋት ዝርያዎችን የሚያወድም መሆኑ ተገልጿል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ድሪባ ኩማ (አምባሳደር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ 50 የአበባ አልሚ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ሰባቱ በዝዋይ እንደሚገኙና በ‹‹እሳት እራት›› ወይም ‹‹ቢራቢሮ›› መሳይ በሆነ ተባይ በከፍተኛ ሁኔታ መጠቃታቸውን ገልጸዋል፡፡

የእሳት እራት የተሰኘው ተባይ በተለያዩ አካባቢዎችም ሆነ በቤት ውስጥ የሚገኝ እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህ ምክንያት ተባዩን በአገሪቱ ከሚገኙ አበባ አምራች እርሻዎች ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ አበባ አልሚዎች ወደ አውሮፓ ኅብረት አገሮች ምርቶቻቸውን ሲልኩ፣ ከተባይ የፀዳ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በሕግ መደንገጉን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከቡና ቀጥሎ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ዘርፍ በመሆኑ፣ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግ ባለሥልጣኑ የሚሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

ኢትዮጵያ በአበባ ምርት በየዓመቱ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ ጠቅሰው፣ ከዚህ በፊት አበባ አምራች ኩባንያዎች ራሳቸው አምርተው በመላክ የሚተዳደሩ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ሁሉም የግብርና ምርቶች ጥራታቸው ተፈትሾ እንደሚላኩ ጠቁመዋል፡፡

የእሳት እራት የተባለው ተባይ በምንም ዓይነት መንገድ የአውሮፓን ድንበር አልፎ መግባት እንደሌለበት፣ ከገባም ባህሪውን በመለወጥ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያም ወደ ተለያዩ አገሮች የአበባ ምርቶቿን ስትልክ 25 በመቶ ናሙና የሚወሰድ መሆኑንና ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ሌሎች አገሮች መቶ በመቶ ናሙና እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

ወደ ተለያዩ አገሮች የሚላኩ የግብርና ምርቶች ጥራታቸው የገዥ አገሮችን ደረጃ ያሟላ ነው የሚለው በባለሥልጣኑ የሚፈትሽ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የተወሰኑ የአበባ እርሻ ኩባንያዎች ወደ ተለያዩ አገሮች በሚልኩበት ወቅት ተባዩ መገኘቱን  አስረድተዋል፡፡

‹‹ሌሎች አገሮች የአበባ እርሻን ከተባይ እንዴት ነው የተቆጣጠሩት የሚለውን ለማወቅ ኬንያ ድረስ መሄዳቸውን፣ ኬንያም ‹‹ኬኤፍሲ›› የተሰኘ የአበባ እርሻን ብቻ የሚቆጣጠር ትልቅ ኢንስቲትዩት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

ኬንያዎች የአበባ ምርታቸው ከዚህ ተባይ የተከላከሉበትን መንገድ በማጥናትና ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት፣ የአበባ አምራች ኩባንያዎች ሥልጠናና በቂ የሆነ ክህሎት እንዲኖራቸው መደረጉን አስረድተዋል፡፡

እሳት እራት የተሰኘው ተባይ የአበባ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ፣ እንዲሁም ምርቶች ከኩባንያው ከወጡ በኋላ ከአገር ሳይወጡ በፊት በአውሮፕላን ማረፊያ በተገቢው መንገድ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ እርሻ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የአበባ እርሻ መሆኑን የገለጹት ድሪባ (አምባሳደር)፣ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ የእርሻ ኩባንያዎች በውጭ አገር ዜጎች ሥር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የእሳት እራት የተሰኘ ተባይ ወደ አውሮፓ ከገባ ባህሪውን በፍጥነት በመቀየር ከመቶ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎችን የሚያጠፋ መሆኑን የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንተርናሽናል ፕላን ፕሮቴክሽን ኮንቬንሸን (አይፒፒሲ)፣ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ አበባ ላኪ የሆኑ አገሮች የወጣውን ሕግ ተፈጸሚ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተለይም ሮዝ አበባ የሚልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ይህንን ሁኔታ ዜሮ ማድረግ እንደማይችሉ አክለዋል፡፡

እሳት እራት የተሰኘው ተባይ በቆሎ፣ ብርቱካን፣ መንደሪንና ሌሎች ዕፅዋቶች ላይ የሚገኝ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ለ180 አገሮች የግብርና ምርቶች እንደምትልክ ገልጸዋል፡፡

ለ‹‹አይፒሲሲ›› ፈራሚ አገሮች ኢትዮጵያ የምትልከው የግብርና ምርት ችግር ካለበት የላኪው ሰርተፊኬት ሊወሰድ እንደሚችል፣ ይህንንም የተለያዩ የአበባ ምርት የሚያመርቱ አገሮች ላይ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የሚልኩት የአበባ ምርት መቶ በመቶ ናሙናቸው እንዲታይ መወሰኑን፣ ይህ ማለትም አንድ አገር መቶ ሺሕ ቶን ለመላክ ቢፈልግ እያንዳንዱ ዘንግ የሚፈተሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚልኩ የአበባ እርሻ ኩባንያዎች በኬሚካልና በሌሎች ዘዴዎች ተባዩን እንዲያጠፉ የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፣ ባለሥልጣኑም ከእርሻ ጀምሮ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በማጣራት ውጤታማ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡