
March 3, 2024

ከፕላስቲክ መልሶ መጠቀም ሊገኙ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞችን ለማሳደግ የሚያስችሉ ረቂቅ ሕጎች፣ በፍጥነት ፀድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተጠየቀ፡፡ በየዓመቱ እስከ 380 ሺሕ ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ በምታመነጨው ኢትዮጵያ የፕላስቲክ ቆሻሻን በሁሉም ደረጃ መልሶ ለማስጠቀም የሚያስችሉ ሕጎች ባለመኖራቸው፣ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለው ጥቅም መታጣቱ ተገልጿል፡፡
የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና ፔትኮ ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት፣ ‹‹የፕላስቲክ መልሶ መጠቀም ፎቶ ኤግዚቢሽን›› የተገኙት የፔትኮ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ምሕረት ተክለማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ፕላስቲክ በከፊል ፕሮሰስ አድርገው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ጥቂት ድርጅቶች ቢኖሩም፣ አገሪቷ ከምታመነጨው የፕላስቲክ ቆሻሻ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ አጠቃቀም በየዓመቱ 13 በመቶ እየጨመረና 26 በመቶ የፕላስቲክ ቆሻሻ እየመነጨ መሆኑን በማስታወስም፣ በአደጉ አገሮች የተለመደውን ከመልሶ መጠቀም የተመረተ ፕላስቲክን ለምግብ ማሸጊያነት ማዋልን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ ያስችላሉ ተብለው የተዘጋጁ ሦስት ሕጎች በፍጥነት እንዲፀድቁና አገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን አሳስበዋል፡፡
እስካሁን ፕላስቲክን መልሶ ለምግብ ማሸጊያነት ለማዋል የሚያስችል ሕግ ባለመኖሩ ለውኃ፣ ለዘይትና ለተለያዩ ምግቦች ማሸጊያ የሚውሉ ፕላስቲኮች ከድንግል ላስቲክ ብቻ እንዲሠሩ ማስገደዱን፣ ይህም ኢትዮጵያ ፕላስቲክን በብዛት ከውጭ እንድታስገባና ከዚህ ባለፈም ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን አክለዋል፡፡
ለዚህ ‹‹ሪሳይክልድ ፕላስቲክ ፎር ፉድ ግሬድ›› ወይም ከመልሶ መጠቀም የተገኙ የፕላስቲክ ዕቃዎች ለምግብ ማሸጊያ እንዲወሉ መጠቀም የሚያስችል ሕግ፣ ማውጣት በጣም ጠቃሚ ነው የሚሉት ወ/ሮ ምሕረት፣ ረቂቅ ሕጉ በኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅት፣ በፔትኮ ኢትዮጵያና በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተረቆ ለፍትሕ ሚኒስቴር መቅረቡንና ግብረ መልስ ተካቶበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕጉ ከፀደቀ በኋላ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች ያሉት ወ/ሮ ምሕረት፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን እንደሚስብ፣ በሥራው ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኢንቨስተሮችን እንደሚያሳትፍና በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
‹‹ኤክስቴንድድ ፕሮዲዩሰርስ ሪስፖንስብሊቲ ሬጉሌሽን›› ወይም የተራዘመ የአምራቾች ኃላፊነት ሕግ፣ በየደረጃው ያሉ አምራቾችንና ፕላስቲክ ከውጭ የሚያስገቡ ድርጅቶችን ጨምሮ እስከ ታች ፕላስቲኮችን በገበያው ውስጥ የሚያሠራጩ፣ ፕላስቲኮቹ መልሰው ተሰብስበው፣ ተለይተውና ወደ መልሶ መጠቀም ተቀይረው ወደ ኢኮኖሚው እንዲገቡ ኃላፊቱን ወስደው እንዲሠሩ የሚያስገድድ ነው፡፡ ሕጉም ተረቆ ለፍትሕ ሚኒስቴር ቀርቦና አስተያየት ተሰጥቶበት በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካይነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ምሕረት ገለጻ፣ ኢትዮጵያ በፕላስቲክ መልሶ መጠቀምን በተመለተ ስትራቴጂካዊ የድርጊት መርሐ ግብር ዕቅድ የላትም፡፡ በመሆኑም ፔትኮ ኢትዮጵያ፣ የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅትና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በመተባበር ያዘጋጁት ዕቅድ እንዲፀድቅ እየተጠበ ነው፡፡
የፕላስቲክ ቆሻሻና ሌሎች የቆሻሻ ዓይነቶችን ወደ ሀብት ለመቀየር የሚያስችል ዕይታ አለመዳበሩን የገለጹት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የፖሊሲና ሕግ አማካሪ አየለ ኄጌና (ዶ/ር) በከኩላቸው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በቆሻሻ አወጋገድና አጠቃቀም ዙሪያ ሕጎችና ፖሊሲዎች ወጥተው በሥራ ላይ ቢውሉም ብዙ መሥራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ባለሥልጣኑን ጨምሮ የተረቀቁትንና የሚመለከታቸው አካላት ውይይት ያደረጉባቸውን ፕላስቲክን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችሉትን ሕጎች አስመልክተው እንዳሉት፣ ብሔራዊ የፕላስቲክ ቆሻሻ ስትራቴጂካዊ የድርጊት መርሐ ግብር ዕቅድ የተገመገመና ያለቀ በመሆኑ በቅርቡ ፀድቆ ከመጋቢት 2016 ዓ.ም. ማብቂያ ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት አስተዋውቀውት ወደ ሥራ ይገባል፡፡
የተራዘመ የአምራች ኃላፊነትና ከመልሶ መጠቀም የተገኙ የፕላስቲክ ዕቃዎችን ለምግብ ማሸጊያ እንዲውሉ የሚያስችሉት ሕጎች፣ በፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል፡፡ በቅርቡም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቀው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለዋል፡፡