
ልናገር በጣት መፈረም ሲያበቃ የአገር ዕድገት ይፋጠናል
ቀን: March 6, 2024
በዳዊት አባተ (ዶ/ር)
የትምህርት ዕድል ማግኘት በዓለም አቀፍ የተደነገገ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ስለአገራችን የትምህርት ሥርዓት በአብዛኛው የሚነገረውና የምንሰማው ስለመደበኛ ትምህርት ነው፡፡ ከዚህም በጠበበ መልኩ ለከፍተኛ ትምህርትና ለድህረ ምረቃ ፕሮግራም ትኩረት የሚሰጥ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ስለ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ዝቅተኛ ውጤት ማስመዘገብ ጉዳይ እና ስለዩኒቨርስቲ መግቢያና መውጫ ፈተናዎች ሆኗል፡፡ ስለጎልማሶች ትምህርት ጉዳይ ጭራሽ የተረሳ የትምህረት ዘርፍ ሆኗል ማለት ይቻላል፣ ይህ ግን ሊሆን አይገባም፡፡
በኢትዮጵያ ማንበብና መጻፍ የሚችሉት ዜጎች 39 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ 61 በመቶ የሚሆኑ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ዜጎች (ማይማን) የሚኖሩባት አገር ናት ማለት ነው፡፡ በዩኔስኮ መሠረት የጎልማሶች ትምህርት የመደበኛ ትምህርት ዕድል ላላገኙ ዕድሜአቸው ከ15 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የሚዘጋጅና የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ የአገሪቱ የማይምነት ችግር የበለጠ ተስፋፍቶ የሚገኘው በገጠር ኗሪው መካከል ሲሆን፣ በሴቶች ላይ ደግሞ ጭራሽ የከፋ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሳይሻሻል የአገር ዕድገት ማምጣትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች እኩል እንሆናለን የሚለው ተስፋ ዕውን ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ለአንድ አገር ሕዝብ የኑሮ ደረጃ መሻሻልን ለመለካትና ለማነፀፀር በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት አንዱ መሥፈርት ትምህርት ሲሆን፣ የማይማን ቁጥር ማነስ/መብዛት ዋናው ነው፡፡ በዚህ መሥፈርት ድርጅቱ ኢትዮጵያን በጣም ዝቅተኛ ከሚባሉ አገሮች መካከል አንዷ ያደርጋታል፡፡ ከ184 አገሮች መካከል 175ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአጠቃላይ የተማረ የሰው ኃይል ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት መፋጠንና የዜጎች ኑሮ መሻሻል መሠረታዊ ግብዓት መሆኑን የመስኩ ባለሙያዎችና የዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንበብ መጻፍ ደረጃ በዓለም ካለው ሁኔታ ጋር ማነፃፀር ይገባል፡፡ የበለፀጉ አገሮች የማይማን ቁጥር ከአምስት መቶ በታች ነው፡፡ ከዚህም በላይ የተወሰኑ አገሮች ለምሳሌ ሩሲያና ፊንላንድ ማንበብና መጻፍ የማይችል ዜጋ ጭራሽ የለባቸውም፣ ማይምነት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት ነው፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁኔታው የተለየ ነው፡፡ በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ማንበብ መጻፍ ከሚችሉት ይልቅ የማይችሉት ዜጎች በቁጥር ይበልጣሉ፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ድህነትን መቀነስ፣ የዜጎች ነፍስ ወከፍ ገቢ መጨመርና በአጠቃላይ የሕዝብ ኑሮ ደረጃ መሻሻል ማይምነት ከማጥፋት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
የትምህርት ታሪካችን እንደሚያሳየው የጎልማሶች ትምህርት በኢትዮጵያ የተጀመረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ማንበብና መጻፍ የሚችሉት ዜጎች 39 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረው 93 በመቶ የማይማን ቁጥር በአጭር ጊዜ ዝቅተኛ ደረጃ የደረሰው በደርግ ዘመን ነበር፡፡ ይኸውም ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ያህል ማይምነትን ለማጥፋት በማቀድ “ማይምነት የጨለማ ጉዞ ነው” በሚል መፈክር በተካሄደ ጠንካራ ጥረት የአገራችንን የማይማን ቁጥር ወደ 24 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለዚህ ጥረትና ለተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ሽልማት በጊዜው አግኝታለች፡፡ ይህ ጥረትና ሒደት በሕውሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ባለመቀጠሉ የማይማን ቁጥር በደርግ ጊዜ ከነበረው በከፋ ሁኔታ በመጨመር ዛሬ 61 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጥረቱ ቢቀጥል ኖሮ በጣት ከመፈረም የተሻለ ለመላቀቅ ይቻል ነበር፡፡
የጎልማሶች ትምህርት በዩኔስኮ ትርጉም ከ15 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ማለትም ለአደጉ (አዋቂ) ሰዎች የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ ማንኛውም ያደገ ሰው ደግሞ ዕውቀት አለው፡፡ ይህ ዕውቀት ከወላጆች፣ ከጎረቤት፣ ከማኅበረሰቡና ከአካባቢ የሚገኝ ባህላዊ ዕውቀት ሲሆን የግለሰቦች ዕድሜ በገፋ ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ ዕውቀት ነው፡፡ ከትምህርት ቤት፣ ከማሠልጠኛ ተቋም ወይም ከዩኒቨርሲቲ የሚገኝ ዕውቀት ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ (ከወላጆች ወደ ልጆች) በአብዛኛው ከአፍ ወደ አፍ በሆነ መንገድ ሲተላለፍ የመጣ ዕውቀት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በረጅም የሥልጣኔ ታሪካችንና ከባህልና ከተፈጥሮ ብዝኃነት የመነጨ ጥልቅ ባህላዊ ዕውቀት ባለቤቶች ነን፡፡ ይህ ባህላዊ (አገር በቀል) ዕውቀት ከሕዝቡ ብዙ ዘመናት ተመክሮ የመነጨና ሲሆን፣ ዕውቀት (ጥበብ) ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ የኑሮ ዘዴ (ብልኃት) ያዘለ ነው፡፡ ለዚህ ነው የጎልማሶች ትምህርት ባህላዊ ዕውቀትን መሠረት አድርጎና ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ተቀናጅቶ መሰጠት ያለበት፡፡ ይህም ማለት ባህላዊ ዕውቀት ለጎልማሶች ትምህርት አንዱ ግብዓት ማድረግ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡
ባህላዊ ዕውቀት የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት፣ ከአካባቢውና ከማኅበረሰቡ ጋር አብሮ ለመኖር ያስቻለ ዕውቀት ነው፡፡ የጥንት አባቶቻችን ከዱር አራዊት ራሳቸውን ለመጠበቅ፣ አድኖ ለመብላት፣ ምግባቸውን ለማዘጋጀት፣ ጤናቸውን ለመጠበቅ፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግና ከሌሎች ጋር አብሮ ለመኖር ዕውቀትና ብልኃት ነበራቸው፡፡ ታዲያ ዛሬ የዓለም ሕዝብ ዘመናዊ ዕውቀት እየገበየ ቴክኖሎጂን ለኑሮው መጠቀም ላይ ባለበት ዘመን ባህላዊ ዕውቀታችን ብቻ ለምንመኘው አገራዊ ዕድገት በቂ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ስለዚህም ማንበብ፣ መጻፍና ሥሌት (አራቱ መደብ ሒሳብ) የማይችሉ ጎልማሳ ዜጎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙና የግብ ተኮር ተግባራዊ ትምህርት ተጠቃሚ አንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ዘርፈ በዙ ችግር ላለባት ኢትዮጵያ የጎልማሶች ትምህርት ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ የተማረ ግለሰብ (ጎልማሳ) በማንኛውም የልማት ሥራዎች በንቃት ለመሳተፍ የበለጠ ዝግጁ ነው፡፡ ስለዚህም የራሱን፣ የቤተሰቡንና የማኅበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የተሻለ ዕድል ይኖረዋል፡፡ የዕለት ከዕለት ተግባሩን (ሥራውን) በተሻለ መንገድ ይመራል፣ ከአንድ የሥራ ዓይነት ወደ ሌላ ለመለወጥም ክህሎትና መተማመን ይኖረዋል፡፡
የሚበዘው በጣቱ የሚፈርመው ሕዝባችን በገጠር የሚገኝ ገበሬው ስለሆነ፣ በግብርና ሥራው ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች የመፍታት ችሎታው በጎልማሶች ትምህርት ይዳብራል፡፡ ከዚህም በላይ ዘመኑ ያመጣቸውን አዳዲስ የአሠራር ዘዴዎች፣ በጽሑፍ የሚያገኛቸውን መመርያዎችና ምክሮች በማንበብ ተግባራዊ ስለሚያደርግ ገበሬው ምርታማነቱን ይጨምርለታል፣ ገቢውም ያድጋል፡፡
በጤና በኩል ሲታይ ደግሞ የተማሩ ወላጆች በተለይም እናቶች ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን፣ የልጆቻቸውንም ደኅንነት (ክትባት፣ የሕፃናት አመጋገብ፣ ወዘተ) በማሻሻል የሕፃናትን ሞትና የመቀንጨር ችግር መቀነስ ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ የተማሩ እናቶች ልጆቻቸውን ለማስተማር የበለጠ የተጉ እንደሚሆኑ ይታወቃል፡፡ ለጥቃቅን ነጋዴዎችም ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ በሸቀጥ ዕቃዎች ላይ የተጻፉ መረጃዎችን በትክክል በመረዳት (በማንበብ) ነጋዴዎች ለደንበኞቻቸው የተሻለ መረጃ ያስተላልፋሉ፡፡ ሥሌት በማወቃቸውም የንግድ ድርጅቱን (ሱቁን) ገቢና ወጪ ጠንቅቆ በማወቅ ሥራውን ቀልጣፋና የበለጠ አትራፊ ያደርገዋል፡፡ ለቤተሰቡ የተሻለ ገቢ ያስገኛል፣ ለንግድ ሴከተሩም (ለመንግሥት) አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡
የጎልማሶች ትምህርት አካባቢን በተሻለ እንዲያውቅ ስለሚረዳ የተፈጥሮ ሀብትን (አፈር/ውኃ ጥበቃ፣ ጫካና ዛፍ ልማት፣ የዱር አራዊት ጥበቃ፣ ፓርኮችን ማልማት፣ ወዘተ) የሚንከባከብና ለአካባቢ ልማት በቂ ክህሎት ያለው ዜጋ ያደርገዋል፡፡ በአየር ጠባይ ለውጥ ዙሪያም ቢሆን የሚከሰተውን ችግር ለመቋቋም በተሻለ የተዘጋጀ ሰው ይሆናል፡፡
ድህነት በተንሰራፋበት አገራችን የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታትና ኑሮውን ለማሻሻል ዕውቀትና ክህሎት ወሳኝ በመሆኑ፣ መንግሥት የጎልማሶችን ትምህርት ዘርፍ ሊቀይስ ይገባል፡፡ የተቀናጀና ተግባራዊነት የሆነ የጎልማሶች ትምህርት ያገኘ ማኅበረሰብ ለአገር ልማትና ዕድገት አስተዋፅኦው ከፍተኛ ስለሆነ፣ መንግሥት ለዚህ ተቋም አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል፡፡
የትምህርት ይዘቱ ምን መሆን አለበት? ትምህርቱን የሚሰጠው ማን ነው? ትምህርቱ የሚሰጠው መቼና የት ነው? ትምህርቱን ለማጠናቀቅስ ምን ያህ ጊዜ ይወስዳል? የጎልማሶች ትምህርት አመራር እንደ አካባቢውና እንደ ሁኔታው ታይቶ የሚቀናጅ ይሆናል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው በሥራ ስዓት፣ በትርፍ ጊዜ ጨምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚቋቋመው ተቋም የጎልማሶች ትምህርት ሽፋኑ፣ ተቀባይነቱና አግባብነቱ እየጨመረ የሚሄድና ማይምነትን ለማጥፋት ዓላማና ብቃት ያለው ተቋም ለማድረግ ከትምህርት ማኅበረሰቡ ብዙ ይጠበቃል፡፡
የጎልማሶች ትምህርት ከማንበብ መጻፍና ሥሌት በተጨማሪ ከሙያ ማሻሻል ጋር የተቆራኙ ለምሳሌ የሕፃናት አያያዝና ጤና አጠባበቅ፣ ስለአመጋገብና የምግብ ዝግጅት፣ የአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ የጓሮ አትከልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የግብርና ምርታማነትና ስለማኅበራዊ ኑሮ ሊያጠቃልል ይገባል፡፡ አገራችን የቋንቋ ብዝኃነት ስላላት የመማር/ማስተማሩ ሥራ በአካባቢው ወይም አብዛኛው ማኅበረሰብ በሚፈልገው ቋንቋ ይሰጣል፡፡ አስተማሪዎች በጎልማሶች ትምህርት ሙያ የሠለጠኑ ወይም አጭር ጊዜ ሥልጠና የተሰጣቸው መምህራን ሲሆን፣ ዝግጅቱም በባለሙያዎች ድገፍ የታቀደ መሆን አለበት፡፡ የመማሪያ/ማስተማሪያና የንባብ መጻሕፍትም ከማኅበረሰቡ ኑሮን ፍላጎት ጋር የተዛመደ ማድረግ ይገባል፡፡ የማንበብ ልምድ እንዲዳብርና ማይምነት ተመልሶ እንዳይመጣ ይረዳል፡፡
የጎልማሶች ትምህርት ለዜጎች ኑሮ መሻሻልና ለአገር ዕድገት መሠረታዊ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ፕሮግራሙን ለማስፈጸም ተቋም ተመሥርቶ የማይማንን ቁጥር በመቀነስና ጭራሽ በማጥፋት የኢትዮጵያን የዕድገት ሒደት ፈጣንና ብሩህ ማድረግ ይቻላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው dawitabatetassew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡