

የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ (ከመሀል) ለዩክሬን ረዥም ርቀት ተተኳሽ ሚሳኤል አልሰጥም ማለታቸው አስተችቷቸዋል (አሶሺየት ፕሬስ)
ዓለም ሩሲያን ከጀርመን ያወዛገበው የጦር ምስጢር
ቀን: March 6, 2024
ከዓመት በፊት በሩሲያና በዩክሬን መካከል የተጀመረውን ጦርነት በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት ጥረት ቢደረግም፣ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ለዩክሬን የወገኑት አሜሪካና አውሮፓውያኑ የውክልና ጦርነታቸውን ከሚያካሂዱበት ዩክሬን ምድር ከ31 ሺሕ በላይ ዩክሬናውያን፣ ከሩሲያ ወገንም ከ20 ሺሕ በላይ መሞታቸውን አንዳንድ ግምታዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ይህም ሆኖ ጦርነቱ ዛሬም አላባራም፡፡ ይልቁንም የሚያባብሱና የውክልና ጦርነቱን ወደ ቀጥታ የሚቀይሩ ሁኔታዎች መኖራቸውን፣ ከወደ ጀርመን አፈትልኮ ወጥቷል የተባለው ወታደራዊ ውይይት ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለዩክሬን የመሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ሲያቀርቡ ከነበሩት ምዕራባውያን፣ የጀርመን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ረዥም ርቀት የሚጓዝ ታውረስ ክሩዝ ሚሳኤል ለዩክሬን ለመስጠት የመከሩበት መረጃ፣ በሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥንና ማኅበራዊ ትስስር ገጾች መለቀቅም ጀርመንን ከሩሲያ አወዛግቧል፡፡
የ38 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው የጀመርን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የመከሩበት ቅጅ፣ ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመቋቋም እንድትችል፣ ጀርመን ታውረስ የተባለውን የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤልን ለዩክሬን እንድትሰጥ መወያየታቸውን ያጋለጠ መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ መረጃውን ከለቀቀች በኋላ፣ ‹‹ጀርመን በሩሲያ ላይ የቀጥታ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀች ነው፤›› ማለቷን የጀርመን መንግሥት ያጣጣለው ቢሆንም፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ ያደረጉት ውይይት እንዴት አፈትልኮ እንደወጣ ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡
የመረጃውን ማፈትለክ ተከትሎ ከጀርመናውያን የመጣውን ጫና ለማርገብም፣ ‹‹ጀርመን በሩሲያ ላይ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀች ነው ተብሎ በሩሲያ የተለቀቀው መረጃ የሩሲያ ፕሮፖጋንዳ ነው፤›› ሲሉም፣ የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ዎልፍ ጋንግ ቡችነር በበኩላቸው፣ ‹‹የመረጃው መለቀቅ ሩሲያ በምዕራባውያን ላይ የከፈተችው የመረጃ ጦርነት አካል ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ዓላማውም በጀርመን ውስጥ አለመግባት ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጀርመን ባለሥልጣናት መረጃውን ሐሰት ነው ብለው አልተከራከሩም፡፡ ይህ መረጃ ከማፈትለኩ ከሦስት ሳምንታት በፊትም፣ ሾልዝ ታውረስ የረዥም ርቀት ክሩዝ ሚሳይልን ለዩክሬን በመስጠት አገራቸውን ቀጥተኛ የጦርነቱ ተሳታፊ ማድረግ እንደማይፈልጉ መግለጻቸው፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተዘግቦ ነበር፡፡
ከአሜሪካ ቀጥሎ ለዩክሬን ከፍተኛውን የጦር መሣሪያ እያቀረበች የምትገኘው ጀርመን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ እስክ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ ዒላማ ለመምታት፣ ለዕይታና ለማክሸፍ ሳይመችም ድልድዮችን ለማፈራረስ የሚችለውን ታውረስ ሚሳኤል ለዩክሬን ለመስጠት ቢመክሩም፣ ሾልዝ ቀድሞም እሽታቸውን አለመግለጻቸው ‹‹ግድ የለሽ›› አስብሏቸው ነበር፡፡
መረጃው ከተለቀቀ በኋላ በደቡብ ምዕራብ ጀመርን የሚገኝ ትምህርት ቤትን የጎበኙት ሾልዝ፣ ‹‹እኔ መራሄ መንግሥት ነኝ፣ ቃሌም ተገቢነት አለው፤›› ሲሉም ረዥም ርቀት የሚጓዘውንና ጀርመን ሠራሹን ታውረስ ሚሳኤል አገራቸው ለዩክሬን የማትሰጥበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡
በጀርመን በኩል በመከላከያ ባለሥልጣናቱ የተደረገው ውይይት እንደ አማራጭ የቀረበ ነው የሚል ማለሳለሻ ቢሰጥም፣ ሩሲያ ጉዳዩን፣ ‹‹መጥፎ ከስተት የሚያስከትል›› ስትል ገልጻዋለች፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ‹‹የጀርመን ሕዝብ ይህንን ካላስቆመ ለጀርመን ጭምር መጥፎ ዕዳ ይዞ ይመጣል፤›› ብሏል፡፡
የተለቀወው ድምፅ የጀርመን አየር ኃይል ኃላፊን ጨምሮ የአራት ባለሥልጣናትን ውይይት ያካተተ ነው፡፡ በውይይቱም የታውረስ ሚሳይልን በፍጥነት ወደ ዩክሬን መላክ ዕውን ሊሆን የሚችለው፣ በጀርመን ወታደሮች ተሳትፎ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በውይይቱ ስለሚሳይሉ አጠቃቀም ለዩክሬን ወታደሮች ሥልጠና መስጠት ስለሚቻልበት የተነሳ ቢሆንም፣ ሥልጠናው ወራትን ሊወስድ ስለሚችል በጀርመናውያን ቢሆን የሚል ሐሳብም ተነስቷል፡፡ የጀርመን መንግሥት ሚሳኤሉ ለዩክሬን መሰጠት የለበትም በሚል መቃወሙም የውይይታቸው አካል ነበር፡፡
ከጀርመን ወገን፣ ሩሲያ ምዕራባውያንን ለመከፋፈል ያደረገችው የመረጃ ጦርነት ቢባልም፣ ምዕራባውያን በዩክሬን ጦርነት መሣሪያ ከመርዳት አልፈው የሰው ኃይል ማሠለፋቸው በውይይቱ መነሳቱም፣ ሩሲያ ‹‹ምዕራባውያን በጦርነቱ እየተሳተፉ ነው፤›› እንድትል አስችሏታል፡፡
የእንግሊዝ የሰው ኃይል በዩክሬን መኖሩ በውይይቱ መነሳቱም ‹‹አውሮፓውያን ተባብረው በጦርነቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ›› ለሚለው የሩሲያ ውንጀላ ማስተማመኛ ሆኗል፡፡
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ረሺ ሱናክ፣ የእንግሊዝ ወታደሮች በእንግሊዝ መኖራቸውን በተመለከተ ‹‹ጥቂት ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በዩክሬን አለን፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለዲፕሎማቶች የደኅንነት አገልግሎት ለመስጠትና ሕክምናን ጨምሮ የዩክሬን ወታደሮችን ለመደገፍ መሰማራታቸውን አክለዋል፡፡ ዘ ጆርናል እንዳሠፈረውም፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስለመሳተፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት ነገር የለም፡፡
ከጀርመን መከላከያ ወጣ በተባለው ውይይትና በመራሄ መንግሥቱ በኩል ይሁንታን የተነገፈው ታውረስ ሚሳይልን ለዩክሬን የመላክ ዕቅድ፣ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ መምታት የሚችሉ ስካልፕ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ባስታጠቁት ፈረንሣይና ብሪታንያ መንደር ቅሬታን አስነስቷል፡፡
የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባሎቹና በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ለዩክሬን የመሣሪያና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርጉ የቆዩት አገሮች ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡም አድርጓል፡፡
‹‹ሩሲያ የምዕራባውያንን አንድነት ልታፈርስ ነው፤›› የሚል አስተያየት ከየቦታው ሲሰጥም ይሰማል፡፡ እንግሊዝም፣ የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ሾልዝ፣ ‹ፈረንሣይና እንግሊዝ ዒላማ በሚመቱ ሚሳኤሎች ዙሪያ ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ ነው› ብለው መናገራቸውንም ተቃውመዋል፡፡
ሾልዝ፣ የፈረንሣይና የእንግሊዝ የሰው ኃይል ለዩክሬን የተለገሱ ሚሳኤሎችን ያንቀሳቅሳሉ (ይተኩሳሉ) ማለታቸው ‹‹ስህተት፣ ኃላፊነት ያልተሞላበትና አብረው የሚሠሩ አገሮችን በጥፊ እንደመምታት ነው፤›› ሲሉም በእንግሊዝ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ላይ ጀርመን ለዩክሬን ረዥም ርቀት ተተኳሽ ሚሳኤል ለመስጠትም ሆነ ወታደር ለመላክ ፈቃደኝነቷን አለመስጠቷ ሲገለጽ፣ ከዚህ ቀደም ፈረንሣይ ‹‹ኔቶ በቅርቡ ወታደሮቹን ወደ ዩክሬን መላክ ይጀምራል›› በማለቷ በርካታ አገሮች ሐሳቧን አጣጥለውባት ነበር፡፡