ጂሚ ሼሪዢዬር (ባርቢኪዩ)
የምስሉ መግለጫ,ጂሚ ሼሪዢዬር (ባርቢኪዩ) ሄይቲን እያመሷት ያሉት የወሮበሎች ቡድኖች መሪ

ከ 6 ሰአት በፊት

በአገሪቱ የሚገኙ ዋነኛ እስር ቤቶች በወሮበላ ቡድኖች ተወሮ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ካመለጡ በኋላ የሄይቲ መንግሥት በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

የካሬቢያን ደሴቶች አካል የሆነችው አገር በአመፅ እየታመሰች ነው። የወሮበላ ቡድኖች የዋና ከተማዋ ፖርት-አው-ፕሪንስን 80 በመቶ ክፍል ተቆጣጥረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪዬል ሄንሪ መንግሥት ሥልጣን ይልቀቅ እያሉ ነው። ያ ካልሆነ በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ይቀሰቀሳል በማለታቸው መንግሥት ጨንቆታል።

በቅፅል ስሙ ባርቢኪው ይሰኛል። ዋነኛው የወሮበሎቹ አለቃ ጂሚ ሼሪዢዬር። በዋና ከተማዋ የሚገኙ አመፀኛ ቡድኖች ጥምረት መሪ ነው።

የቡድኑ ስም ጂ-9 ፋሚሊ ኤንድ አላይስ ይሰኛል። የሚመራው ደግሞ ባርቢኪው ነው።

ባርቢኪው በማኅበራዊ ሚድያ ገጹ መልዕክት አስተላልፏል። እንዲህ ይነበባል፡

“የሄይቲ ብሔራዊ ፖሊስ እና ጦር ሠራዊት ኤሪዬል ሄንሪን በማሠር ኃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ እጠይቃለሁ። አሁንም እደግመዋለሁ፤ ሕዝቡ ጠላታችን አይደለም፤ ታጣቂ ቡድኖቹም ጠላቶቻችሁ አይደሉም።”

የቀድሞው የፖሊስ መኮንን ዘንድሮ እጅግ የሚፈራ ወንበዴ ሆኗል። ለመሆኑ ባርቢኪው መንግሥት እገለብጣለሁ የሚያስብል ኃይል ከየት አመጣ?

ጎዳናውን መቆጣጠር

ሼሪዢዬር በተለይ በቅርብ ዓመታት ነው የወንጀለኛ ቡድኖች አለቃ ሆኖ ብቅ ያለው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዦቬኔል ሞይስ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2021 ሲገደሉ ሸሪዢዬር አብዮት ቀስቅሶ “ሙሰኛ” ያላቸውን ፖለቲከኞች ማሳደድ ያዘ።

ፕሬዝዳንት ሞይስ በሰው እጅ ከመሞታቸው በፊት ነው ለጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ሹመት የሰጡት። ለዚህ ነው አንዳንዶች ሄንሪ አልተመረጡም ሲሉ ዕውቅና የሚነሷቸው።

ፕሬዝዳንት ሞይስ በይፋ አልተተኩም። ሄይቲ ለመጨረሻ ጊዜ ምርጫ ያካሄደችው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር።

ባርቢኪው ጉልበት እያዳበረ ሲመጣ በማኅበራዊ ሚድያ መድረክ በሚያሰራጫቸው መልዕክቶች ተከታዮችን ማፍራት ያዘ፤ ለታጣቂ የወሮበላ ቡድኑ አባላትን በመመልመል ጎበዘ።

በዩቲዩብ ቻነሉ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ የማኅበራዊ ሚድያን ጥቅም ሲተነትን ይደመጣል።

“ይህንን ቴክኖሎጂ የፈጠሩትን ሰዎች ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ዘንድሮ ቴክኖሎጂ ራሳችንን ለሕዝቡ እንድንሸጥ ትልቅ መሣሪያ ሆኖናል። የምሬን ነው የምላችሁ” ይላል።

“እኔ ይኸው የምታውቁኝ ነኝ። ከሚነግራችሁ መካከል 99 በመቶው ሐሰት ነው። ቴክኖሎጂ ራሴን እንድከላከል ዕድል ሰጥቶኛል” ሲል ያክላል።

የታጠቁ ወሮበላ ቡድን አባላት
የምስሉ መግለጫ,የዋና ከተመዋ ፖርት-አው-ፕሪንስ 80 በመቶ ክፍል በታጣቁ ወሮበሎች ቁጥጥር ስር ነው

ሼሪዢዬር ‘ባርቢኪው’ የሚለውን ስም እንዴት እንዳገኘ ይናገራል።

በ2019 አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ለተሰኘው የዜና ወኪል በሰጠው ቃለ ምልልስ የዚህ ቅፅል ስም ባለቤት የሆነው ልጅ እያለ እናቱ መንገድ ዳር ዶሮ እየጠበሱ ይሸጡ ስለነበር ነው ይላል።

እንጂ ሰዎችን ያቃጥላል ከሚለው ነው ስያሜው የመጣው የሚለውን ሐሳብ አይቀበለውም።

ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባርቢኪው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል ይላሉ። ይህን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት እና አሜሪካ በግለሰቡ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።

ሼሪዢዬር፤ በዓለማችን ሕግ አልባ በምትባለው ሄይቲ ዋና ከተማ ያሉ የዘጠኝ ወንጀለኛ ቡድኖች ጥምረት መሪ ነው።

አብዛኞቹ የኤይቲ ዜጎች ባርቢኪው እጅግ የተፈራ የወንጀለኞች ቡድን መሪ እንደሆነ አይክዱም።

ባርቢኪው ዛሬ የሚፈራ ወንበዴ ከመሆኑ በፊት የወንበዴዎችን አዳኝ የፖሊስ መኮንን ነበር።

የሄይቲ ብሔራዊ ፖሊስ አድማ በታኝ ክፍል አባል የነበረው ባርቢኪው ታኅሣሥ 2018 (እአአ) ነው ከሥራው የተባረረው።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት ባርቢኪው በተወለደባት ሎወር ዴልማስ አካባቢ አመፀኛ ቡድን አቋቁሟል ሲሉ ይከሱታል።

ይሄ ብቻ አይደለም በአውሮፓውያኑ 2017 ግራንድ ራቪን፣ በ2018 ላ ሳሊን፣ በ2019 ደግሞ ቤል-አይር በሚሰኙ አካባቢዎች ሰዎች በጅምላ እንዲገደሉ አስተባብሯል በሚል ስሙ ይነሳል።

እሱ ግን እኒህን ውንጀላዎች በፍፁም አይቀበላቸውም።

ጂሚ ሼሪዢዬር (ባርቢኪዩ) ከጠባቂዎቹ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ጂሚ ሼሪዢዬር (ባርቢኪዩ) ከጠባቂዎቹ ጋር

በግራንድ ራቪን አካባቢ አመፀኞችን ለመቆጣጠር በተደረገ እርምጃ ቢያንስ 9 ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።

በወቅቱ የሄይቲ ፖሊስ አባል የነበረው ባርቢኪው ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የአንድ ትምህርት ቤት ግቢን ሰብረው ገብተዋል ሲል መንግሥት ይወቅሳቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በሄይቲ የተሰማራ ተልዕኮ አለው። ሚሽን ፎር ጀስቲስት ሰፖርት ኢን ሄይቲ ይባላል።

ይህ ተልዕኮ ከሄይቲ ፖሊስ ጋር በመተባበር በወቅቱ የተለያዩ ፀረ-ወንበዴ እርምጃ ይወስድ ነበር።

በወቅቱ ላ ሳሊን በተባለ መንደር ላይ በተፈጸመ ጥቃት 71 ሰዎች ሲገደሉ፣ 11 ሴቶች ተደፍረው፣ 150 ቤቶች ወደሙ። በቤል-ኤይር ደግሞ 24 ሰዎች መገደላቸውን የሀርቫርድ የሕግ ትምህርት ቤት ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ሰኔ 2020 ሼሪዢዬር “ጂ9 ፋሚሊስ ኤንድ አላይስ” የተባለ ጥምረት ማዋቀሩን በዩቲዩብ ገፁ ይፋ አደረገ።

ሲቋቋም ዘጠኝ ወንጀለኛ ቡድኖችን አዋቅሮ ነበር። ዘንድሮ ግን ጥምረቱ ከ12 በላይ ቡድኖች እንዳሉት የተባበሩት መንገሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ዘገባ ያመለክታል።

የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው በ2020 አጋማሽ የባርቢኪው ጥምረት 145 ሰዎችን ገድሎ በርካታ ሴቶችን ደፍሯል።

“ነዋሪዎች ዒላማ እየተደረጉ ያሉት ካላቸው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እና ቁርኝት የተነሳ ነው። ይህ የሆነው የሞይስ ፓርቲ ድጋፍ እንዲያገኝ ነው” ይላል የሀርቫርድ ሪፖርት።

የሄይቲ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት የአገሪቱ ፖሊስ ለባርቢኪው ጥበቃ ያደርጋል ሲል ይወቅሳል።

አሜሪካ በባርቢኪው እና በሌሎች ወንበዴዎች ላይ ማዕቀብ የጣላችው ታኅሣሥ 2020 ነው።

ቡድኖቹ ሕፃናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል “አልፎም ሬሳቸውን መንገድ ላይ ጎትተዋል እንዲሁም አቃጥለዋል” ስትል አሜሪካ ትከሳለች።

ባርቢኪው በተደጋጋሚ በእነዚህ ወንጀሎች ላይ አልተሳተፍኩም ሲል ያስተባብላል።

እኔ የማኅበረሰቡ መሪ ነኝ የሚለው ባርቢኪው “የትጥቅ ትግል” ነው የያዝኩት፤ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ሥርዓትን ለመቃወም “አስፈላጊ ከሆነ በእያንዳንዱ ሕፃናት እጅ ላይ የጦር መሣሪያ እናስቀምጣለን” ሲል ይመልሳል።

“እኔን የመሰሉ ሰዎችን ፍፁም ልገድል አልችልም፤ እኔ ደሀ ሰፈር ነው ያደግኩት። ድህነትን አውቀዋለሁ” ሲል ለኤፒ ተናግሯል።

ባርቢኪው እንደሚለው የትጥቅ ትግሉ የደሀ ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚደረግ ነው – ቤት፣ ምግብ እና ንፁህ ውሀ ለማቅረብ ነው። ይህ ለማድረግ ደግሞ የታጠቀ ቡድን ያስፈልገኛል ብሎ ያስባል።

ለባርቢኪው ሁኔታዎች የተቀያየሩት በ2021 ፕሬዝዳንት ሞይስ ሲገደሉ ነው። ይህ ማለት ከፖሊስ የሚያገኘውን ጥበቃ አጣ ማለት ነው ይላሉ ተንታኞች።

በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በታጣቂዎች እንዲያመልጡ ከተደረገ በኋላ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል
የምስሉ መግለጫ,በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በታጣቂዎች እንዲያመልጡ ከተደረገ በኋላ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል

ጉልበት ማሳያ

ባርቢኪው ራሱን የፖለቲካ መሪ አድርጎ ነው የሚያስበው። መግለጫ ይሰጣል፤ የተቃውሞ ሰልፍ ያካሂዳል፤ ሳያጓድል በማኅበራዊ ሚድያ ገጹ ላይ መልዕክት ያስተላልፋል።

በተለይ በዩቲዩብ ገጹ በተደጋጋሚ ጂ-9 የተባለውን ቡድኑን ያስተዋውቃል። ፖሊስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቁጥጥር ሥር እንዲያውል ጥሪ ያቀርባል።

በትዊተር (አሁን ኤክስ በተባለው) ገጹ ላይ ደግሞ አገሪቱ በሌላ ኃይል ቁጥጥር ስር እንድትሆን እና ገዥው መደብ እንዲፈርስ ጥሪ አቅርቦ ያውቃል።

ሌሎች የአመፀኛ ቡድን መሪዎች እና ራፐሮች ደግሞ ቲክቶክን ተጠቅመው ሐሳባቸውን ማስተላለፍ ጀምረዋል።

ማኅበራዊ ሚድያ በሄይቲ የአመፀኛ ቡድኖች ተፅዕኖ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረጉትን በርካታ ተንታኞች ይስማሙበታል።

ባርቢኪው በማኅራዊ ሚድያ ገጾቹ ከሚያስተላልፋቸው ጠንካራ መልዕክቶች ባልተናነሰ የሄይቲን አውራ ጎዳናዎች ተቆጣጥሯል።

ጥቅምት 2021 ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪዬል ሄንሪ በሟች ፕሬዝዳንት የቀብር ስፍራ የመታሰቢ ጉንጉን አበባ ለማኖር ሲያመሩ የባርቢኪው ቡድን አባላት የማስጠንቀቂያ ተኩስ በማሰማት ሐሳባቸውን አስቀይረዋቸዋል።

ይሄኔ ነው በነጭ ሱፍ ያጌጠው ባርቢኪው በጠባቂዎቹ ታጅቦ ወደ ሥፍራው በማምራት የአበባ ጉንጉን አኑሮ የተመለሰው። ይሄን የተመለከቱ ብዙዎች ሰውዬው ጉልበተኛ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል።

በጥቅምት 2021 ከአል-ጀዚራ ጋር በነበረው ቃለ-ምልልስ “ሄንሪ ጠዋት 2 ሰዓት ሥልጣን ቢለቁ 2፡05 ላይ እኛ መንገዶችን እንከፍታለን፤ ከባድ መኪኖች ነዳጅ እንዲቀዱ እንፈቅዳለን፤ ብጥብጡ በአንድ ጊዜ ይቆማል” ሲል ተናግሮ ነበር።

በ2022 የባርቢኪው ጥምረት አባላት መኪናዎች ነዳጅ እንዳይቀዱ በማገድ አገሪቱን ለሁለት ወራት ያክል ጊዜ ወጥረው ይዘዋት ነበር።

ይህንን ተከትሎ በሄይቲ ያለው የከፋ የኑሮ ሁኔታ እጅጉን ተባብሷል።

ባርቢኪው በራሱ ጊዜ ኅዳር 2022 በማኅበራዊ ሚድያ ገጹ ላይ “አሁን ሹፌሮች መጥተው ነዳጅ መቅዳት ይችላሉ” ሲል ማወጁ አይዘነጋም።

የባርቢኪው ጂ-9 ቡድን ጂ-ፔፕ ከተባለው ተቀናቃኝ ቡድን ጋር በተደጋጋሚ በከተመዋ ውስጥ ቅልጥ ኣለ ፍልሚያ ያደጋል። ጂ-ፔፕ የፕሬዝዳንት ሞይስ ተቃዋሚ ነው ይባልለታል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች የተለመዱ ሲሆኑ ከዋና ከተማዋ ጫፍ ተነስተው አሁን አሁን መሐል ከተማ ውስጥ ይዋጉ ይዘዋል።

ባለፈው ሐምሌ ሁለቱ ቡድኖች እርቅ ፈጽመዋል የሚል ወሬ ቢናፈስም፣ አሁንም ባገኙት አጋጣሚ የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ላይ ናቸው።

በሄይቲ በወሮበላ ቡድኖች መካከል በሚደረግ በጦር መሣሪያ የታገዘ ፍልሚያ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመፈናቀል ተገደዋል።

ሄይቲ ሰላም ካጣች የቆየች ቢሆንም ከሁለት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንቷ ከተገደሉ በኋላ ቀውሱ ተባብሷል
የምስሉ መግለጫ,ሄይቲ ሰላም ካጣች የቆየች ቢሆንም ከሁለት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንቷ ከተገደሉ በኋላ ቀውሱ ተባብሷል

ተያያዥ ርዕሶች