የሞሪሺየስ ዋና ከተማ ፖርት ሉዊስ
የምስሉ መግለጫ,በጎብኚዎች የተመራጭ የሆነችው ትንሿ የደሴት አገር ሞሪሺየስ ቀዳሚዋ ሀብታም አገር ናት

5 መጋቢት 2024

አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ቢሆንም ባሉባት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች እንዲሁም የደኅንነት እጦት፣ ሙስና፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች እና በሽብር እንቅስቃሴዎች ምክንያት በድህነት ውስጥ ትገኛለች።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሀብታም እና ድሃ አገራትን ዝርዝር አውጥቷል።

በዚህም የአገራቱን ሀብት ወይም ድህነት ለመመዘን የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲሁም በአገራቱ ውስጥ ያሉ ምርቶች እና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ በማካፈል አስልቷል።

ኢትዮጵያ ከአህጉሪቱ ቀዳሚ አምስት ሀብታም እና ደሃ አገራት መካከል ባትገኝም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት ካላቸው መካከል እንደሆነች ያመለክታል።

በአውሮፓውያኑ 2024 አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርቷ በ6.2 በመቶ እንደሚያድግ የሚጠበቀው ኢትዮጵያ፤ የዋጋ ግሽበቷ እየጨመረ እንደመጣ እና ነገር ግን ይህ ግሽበት በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት ይቀንሳል ይላል።

ኢትዮጵያ፣ አይቮሪ ኮስት እና ሩዋንዳ በ2024 ከ6 በመቶ በላይ ዕድገት ያስመዘግባሉ ይላል የተቋሙ ትንበያ።

በአይኤምኤፍ ደረጃ መሠረት ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት መካከል አምስቱን ሀብታም እና አምስቱን ደሃ አገራት እነሆ።

የአፍሪካ 5 ሀብታም አገራት

1. ሞሪሺየስ

በዚህ ዓመት በአፍሪካ ሀብታሟ አገር የሆነችው ሞሪሺየስ ስትሆን፣ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርቷ ከከሕዝቧ የመግዛት አቅም አንጻር 31,157 ዶላር ነው። ሞሪሺየስ ከምትታወቅበት የስኳር እና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ባሻገር ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ አላት።

2. ሊቢያ

ባለፉት ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመሆን ከባድ ምጣኔ ሀብታዊ ፈተና ቢገጥማትም፣ ሊቢያ በ26,527 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀብታም አገር ሆናለች።

የአገሪቱ ሀብት ምንጭ በዋናነት መሠረት ያደረገው ባላት ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ሀብት ነው። ባለፈው ዓመት አገሪቱ እንድትረጋጋ የተደረገው ጥረት በአፍሪካ ያላትን የምጣኔ ሀብት ደረጃ እንድትጠብቅ አስችሏታል።

3. ቦትስዋና

ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ቦትስዋና 20,311 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ቦትስዋና ያላት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት አቅም ለዕድገቷ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

ቦትስዋና ያላትን የአልማዝ ሀብት በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም ቱሪዝምን እና የግብርና ልማትን ለማስፋፋት ስላዋለችው ምጣኔ ሀብቷን ጠንካራ አድርጎታል።

4. ጋቦን

ጋቦን 19,865 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ በማዝመዝገብ አራተኛ ደረጃ ሀብታም አገር ሆናለች። በነዳጅ ዘይት እና በማዕድናት የታደለችው ጋቦን ለምጣኔ ሀብቷ መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የአገሪቱ መንግሥት የተከተለው ዘላቂ የልማት ዕቅድ እና ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ጋቦን በአፍሪካ ሀብታም ከሆኑ አገራት ተርታ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

5. ግብፅ

ግብፅ በ17,786 የነፍስ ወከፍ ገቢ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ግብፅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ካላቸው የአህጉሪቱ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ ምጣኔ ሀብቷ በቱሪዝም፣ በግብርና እና በፋብሪካ ምርት ዘርፍ ላይ መሠረት ያደረገ ነው።

የአፍሪካ 5 እጅግ ድሃ አገራት

በጦርነት እና ባለመረጋጋት ውስጥ ያለችው ደቡብ ሱዳን ከአፍሪካ በድህነት ቀዳሚ ናት
የምስሉ መግለጫ,በጦርነት እና ባለመረጋጋት ውስጥ ያለችው ደቡብ ሱዳን ከአፍሪካ በድህነት ቀዳሚ ናት

1. ደቡብ ሱዳን

በአውሮፓውያኑ 2011 ነጿነቷን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን የዓለማችን ወጣቷ አገር ናት። የምጣኔ ሀብት ችግር ተብትቧታል።

ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና ያልተሟላ መሠረተ-ልማት ደቡብ ሱዳን ወደፊት እንዳትራመድ ካደረጓት ችግሮች መካከል ናቸው።

አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ ኋላ ቀር ግብርና ላይ የተሠማራ ነው። ግጭት እና ተፈጥሯዊ አደጋ ደግሞ ግብርናውን እያሰናከለው ይገኛል።

11 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ባሕር በር አልባዋ ደቡብ ሱዳን በድህነት አረንቋ ውስጥ ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ናት።

2. ቡሩንዲ

ቡሩንዲ በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ ትንሽ ባሕር አልባ አገር ናት። በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ፈተናዎች የተሞላቸው ቡሩንዲ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና የተዳከመ መሠረተ-ልማት ወጥሮ ይዟታል።

ምጣኔ ሀብታዊ ተግዳሮቶች ዜጎች ሕይወታቸው እንዲከብድ ምክንያት ሲሆን፣ የሕዝብ ቁጥሯ በፍጥት እያደገ መምጣቱ ደግሞ ሌላ ደንቃራ ነው።

80 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ባሕላዊ ግብርና ላይ ጥገኛ የሆነው ቡሩንዲ፣ ከሌሎች የአፍሪካ የሰሀራ በታች አገራት ሲነፃፀር በምግብ ዋስትና ግርጌ ላይ ትገኛለች።

3. ማዕከላዊት አፍሪካ ሪፐብሊክ

ማዕከላዊት አፍሪካ ሪፐብሊክ ስሟ እንደሚጠቁመው በአፍሪካ ማዕከላዊ ክፍል ላይ ነው የምትገኘው።

እንደሌሎች ደሀ የአፍሪካ አገራት በፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ በታጣቂዎች ግጭት እና በተዳከመ መሠረተ-ልማት ምክንያት ምጣኔ ሀብቷ ሊንቀሳቀስ አልቻለም።

በወርቅ፣ ነዳጅ፣ ዩራኒየም እና አልማዝን በመሳሰሉ ማዕድናት የበለፀገች ብትሆንም ዜጎች አሁንም በድህነት አረንቋ ውስጥ ናቸው።

የዋጋ መናር፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት እና ከባድ ጎርፍ ተደማምረው ማዕከላዊት አፍሪካ ሪፐብሊክ ከአፍሪካ ደሀ አገራት መካከል እንድትሆን አድርገዋታል።

4. ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ

በቅፅል ስሟ ዲአርሲ የምትሰኘው ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከሰሀራ በስተደቡብ በኩል ካሉ አገራት ግዙፏ ናት።

ኮባልት እና ኮፐር በመሳሰሉ ተፈጥሯ ሀብቶች የበለፀገችው ዲአርሲ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ወጥረው ይዘዋታል።

አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ ደሀ ሲሆን 62 በመቶ ገደማ የሚሆኑ ዜጎቿ በቀን ከ2.15 ዶላር በታች በሆነ ገቢ ነው የሚተዳደሩት።

የሰውነት መቀንጨር፣ የትምህርት አለመስፋፋት እና የጤና ማዕከላት እጥረት፤ ከከፍተኛ የውልደት መጠን ጋር ተደማምረው ዕድገቷን አንቀራፈውታል።

5. ሞዛምቢክ

የፖርቹጋል የቀድሞ ቅኝ ግዛት የሆነችው ሞዛምቢክ ሕዝቧ ተበታትኖ የሚኖርባት አገር ናት።

በተፈጥሯዊ አደጋ፣ በበሽታ እና በፈጣን የሕዝብ ዕድገት ምክንያት ድህነት የተንሰራፋባት ሞዛምቢክ፣ የግብርና ምርቷ አነስተኛ፤ የሀብት ክፍፍሏ ደግሞ ኢ-ፍትሐዊ ነው።

ተፈጥሯዊ ሀብት ቢኖራትም፣ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ገቢዋም ጠንካራ ቢሆንም ከዓለማችን ደሀ አገራት ተርታ ከመሰለፍ አልጠበቃትም።

ይህ የሆነው የነዳጅ ሀብታም በሆነችው ሞዛምቢክ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች በሚፈጥሩት አለመረጋጋት ምክንያት ነው።