የእስራኤል ሰፈራ

ከ 5 ሰአት በፊት

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ከ3 ሺህ 400 በላይ አዳዲስ የሰፈራ ቤቶችን ለመገንባት የወጣውን እቅድ አጸቀደች።

ከነዚህ ቤቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት የሚገነቡት በምስራቅ ኢየሩሳሌም በምትገኘው ማሌ አዱሚም ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከቤተልሔም በስተደቡብ በሚገኙት ኬዳር እና ኤፍራት አቅራቢያ ነው ተብሏል።

ግንባታው ከሁለት ሳምንታት በፊት በማሌ አዱሚም አቅራቢያ ለደረሰው የፍልስጤም ጥቃት ምላሽ ነው ሲሉ አንድ ሚኒስትር ተናግረዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር የግንባታውን ዕቅድ አውግዟል። ይህ የግንባታ ዕቅድ ከሰኔ ወር ጀምሮ ሲጸድቅ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች።

አብዛኛው የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል እያደረገችውን ሰፈራ በአለም አቀፉ ህግ መሰረት ህገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በዌስት ባንክ የእስራኤል መንግሥት ፖሊሲን የሚተገብረው የሲቪል አስተዳደር ከፍተኛ እቅድ ኮሚቴ 3 ሺህ 476 የሰፈራ ቤቶችን እንዲገነባ እቅድ እንዳወጣ የእስራኤሉ ኃሬትስ ጋዜጣ ዘግቧል።

የሲቪል አስተዳደሩን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የቀኝ አክራሪው ፖለቲከኛ የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች አገራቸው በኃይል ተቆጣጥራው በምትገኘው ዌስትባንክ ሰፈራዎች በአጠቃላይ የ18 ሺህ 515 ቤቶች ግንባታ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እንደጸደቀ አስታውቀዋል።

እስራኤል በዌስትባንክ እያደረገችው ያለውን ሰፈራ የሚቃመው ፒስ ናው የተባለው ድርጅት በበኩሉ “ የእስራኤል መንግሥት ለወደፊቱ ተስፋን፣ ሰላምን፣ ደህንነትን ከመገንባት ይልቅ ለጥፋት መንገዱን እየዘረጋ ነው” ሲል አስጠንቅቋል።

እስራኤል እያደረገቻቸው ያሉት እነዚህ ፕሮጀክቶች የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭትን ለመቋጨት የሁለት አገራት መፍትሄ ለማምጣት በሚደረገው ጥረትም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል ብሏል።

መቀመጫውን በዌስት ባንክ ያደረገው የፍልስጤም አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ አዲሶቹን የግንባታ እቅዶች እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትሩን አስተያየት አውግዟል።

“ሰፈራው በመሰረቱ ህጋዊ ያልሆነ ነው። የአመጽና የጦርነት አዙሪት እንዲቀጥልም ግልጽ ጥሪ መደረጉን የሚወክል ነው” ሲል መግለጫው አክሏል።