አምባሳደር ማይክ ሐመር
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት አፈጻፈም ግምገማ ላይ በመሳተፍ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ስላሉ ግጭቶች ሊወያዩ ነው።

በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም በተደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አምባሳደር ሐመር፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሂደትን በተመለከተ በሚካሄደው ግምገማ ላይ መሳተፍ ዋነኛ የአዲስ አበባ ጉዟቸው ዓላማ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መግለጫ አመልክቷል።

በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በተባባሰው የአማራ ክልል ግጭት እና ዓመታትን ባስቆጠረው የኦሮሚያ ክልሉ አለመረጋጋት ዙሪያ ሰላም ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በቆይታቸው ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር በተለይም ደም አፋሳሹን የሰሜን ኢትዮጵያን የእስር በርስ ጦርትነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አስተናጋጅነት ከየካቲት 28 አስከ መጋቢት 4/2016 ዓ.ም. በሚካሄድ ግምገማ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

ከተፈረመ አንድ ዓመት ያለፈውን የፕሪቶሪያው ስምምነት የአፈጻጸም ሂደትን በተመለከተ የስምምነቱ አሸማጋዮች እና ታዛቢዎች የሚሳተፉበት ግምገማ እንደሚካሄድ ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአምባሳደር ሐመርን ጉዞ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ “የጥይት ድምጽ ባይሰማም፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልል” ብሏል።

ለዚህም ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ማሰናበት እና ወደ መደበኛ ኑሯቸው በመመለስ ማቋቋምን ጨምሮ ተዓማኒነት ያለው የሽግግር ፍትህ ሂደት እና ተፈናቃዮች በፍጥነት ወደ ቀያቸው የመመለስ ተግባር መከናወን እንዳለበት ገልጿል።

ሐመር ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚገናኙ እና በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ያለውን ግጭት ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማፋጠን በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ይወያያሉ።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ አለመረጋጋት ውስጥ በገባው የአማራ ክልል ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ክልሉ በአሁኑ ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ይገኛል።

አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል አሁንም ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ሰላም ለማውረድ የተደረጉ ሙከራዎች ውጤት ሳያስገኙ መቅረታቸው ይታወሳል።

ማይክ ሐመር ለሁለት ሳምንታት በሚያደርጉት ጉዞ ወደ አዲስ አበባ፣ ለንደን እና ሮም በመጓዝ በተለያዩ መረሃ ግብሮች ላይ እንደሚሳተፉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

ልዩ መልዕክተኛው ከየካቲት 28 አስከ መጋቢት 11/2016 ዓ.ም. ድረስ ወደ ተለያዩ አገራት በሚያደርጓቸው ጉዞዎች በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።