የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ያወጣው ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ መስል
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ያወጣው ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ መስል

ከ 6 ሰአት በፊት

የሁቲ አማጺያን በአንዲት የጭነት መርከብ ላይ ረቡዕ ዕለት በፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃት ሦስት የመርከቧ ሠራተኞች መገደላቸውን እና ሌሎች መቁሰላቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የየመን ታጣቂ ቡድኖች በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ ወዲህ በመርከበኞች ላይ የሞት አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው ነው።

ጥቃት የተፈጸመባት የባርቤዶስ ሰንደቅ ዓላማን የምታውለበልበው ‘ትሩ ኮንፊደንስ’ የተባለችው የጭነት መርከብ በሚሳኤል ከተመታች በኋላ ሠራተኞቿ ከመርከቧ ወርደው የሸሹ ሲሆን፣ መርከቧም በእሳት ተያይዛ በባሕሩ ላይ ቆማለች።

በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ እንዳለው በጥቃቱ ሦስት የመርከቧ ሠራተኞች ሲገደሉ፣ ቢያንስ አራት ደግሞ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ሦስቱ ክፉኛ ጉዳት ደርሶባዋል ብሏል።

በጋዛ በሚካሄደው ጦርነት ለፍልስጤማውያን ድጋፋቸውን ለመግለጽ ጥቃት መክፈታቸውን የሚገልጹት ሁቲዎች፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ በመርከቧ ላይ የተኮሱት የባሕር ኃይላቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለቷ መሆኑን ገልጸዋል።

በየመን የብሪታኒያ ኤምባሲ የመርከበኞቹን ሞት በተመለከተ “የሚያሳዝን እና ሁቲዎች በግዴለሽነት ሚሳኤል በመተኮሳቸው የማየቀር ጉዳይ ነው” በማለት ጥቃቱን እንዲያቆሙ ጠይቋል።

ጥቃቱን ተከትሎ በሁቲዎች የሚሠራጨው አል-ኑስራህ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ረቡዕ ምሽት እንደዘገበው፣ በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ስር ባለችው የቀይ ባሕሯ የቀደብ ከተማ ሁዴይዳህ ውስጥ በሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ በአሜሪካ የሚመራ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል።

መርከቧ “የየመን ባሕር ኃይል” ነን ካሉ ቡድኖች በተላለፈላት የሬዲዮ መልዕክት መስመሯን እንድትይር ታዛ እንደነበረ የብሪታኒያ የባሕር ንግድ ተቋም አስታውቋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ ከባድ ፍንዳታ መስማታቸውን እና ግዙፍ ጭስ መመልከታቸውን በአቅራቢያው የነበሩ መርከቦች አሳውቀዋል።

መርከቧ በተተኮሰባት ሚሳኤል ጉዳት የደረሰባት ሲሆን፣ በአካባቢው በነበሩ በአሜሪካ የሚመሩ አገራት የባሕር ኃይል ጥምር ቡድኖች ለመርከቧ ሠራተኞች ድጋፍ ማስጠታቸው ተነግሯል።

በሁቲ ኃይሎች ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ (ፎቶ ፋይል)
የምስሉ መግለጫ,በሁቲ ኃይሎች ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ (ፎቶ ፋይል)

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ሁቲዎች በሚፈጽሙት ጥቃት አሜሪካ ተጠያቂ እንደምትደርጋቸው እና ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ እቅርበዋል።

ቃል አቀባዩ ማቲው ሚለር “ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ ንጹሃን ሰዎች ሰዎች ደኅንነት ግድ ሳይሰጣቸው የሚፈጽሙትን ጥቃት ቀጥለዋል። አሁን ደግሞ በሚያሳዝን ሁኔታ በንጹሃን ላይ ግድያ ፈጽመዋል” በማለት ከሰዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ካሜሮን “በዓለም አቀፍ የመርከቦች መተላላፊያ መስመር ላይ ሁቲዎች የሚፈጽሙትን ጭፍን ጥቃት እናወግዛለን፤ እንዲቆምም እንፈልጋለን። ለዚህም ተግባራዊ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

ሁቲዎች ባወጡት መግለጫ ጥቃት የፈጸሙባት መርከብ “የአሜሪካ ንብረት ናት” ቢሉም የመርከቧ አስተዳዳሪ ድርጅት ቃል አቀባይ ግን መርከቧ “ከየትኛው የአሜሪካ ተቋም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላትም” በማለት አስተባብሏል።

መርከቧ በደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ባለቤትነት ስር ሆና፣ በላይቤሪያ ተመዝግባ በግሪክ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት ሥር የምትነቀሰቀስ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ግን የአንድ የአሜሪካ ድርጅት ንብረት እንደነበረች አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የጭነት መርከቧ ከቻይናዋ ሊያንዩንጋንግ የብረት ምርቶችን እና ከባድ መኪናዎችን ይዛ ወደ ሳዑዲ አረቢያዋ የወደብ ከተማ ጄዳ በማቅናት ሳለች ነበር በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ በሁቲዎች ሚሳኤል የተመታችው።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው ሁቲዎች በአሜሪካ ከሚመሩት የባሕር ኃይሎች ጋር በርካታ የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ነው። ማክሰኞ ዕለት የሁቲ ኃይሎች በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈጽመው እንደነበር ተነግሯል።

ሰኞ ዕለት ደግሞ አንዲት የኮንቴይነር መጫኛ መርከብ በሚሳኤል ተመትታ እሳት ቢነሳባትም የሕንድ ባሕር ኃይል አባላት ደርሰው እሳቱን አጥፍተዋል፤ በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም።

ከሁለት ሳምንት በፊት በሁቲዎች ሚሳኤል ተመትታ ውሃ ወደ ውስጧ ሲገባ የቆየችው መርከብ ባለፈው እሁድ ከሰመጠች በኋላ በየመን አማጺያን ጥቃት የሰመጠች የመጀመሪያዋ መርከብ ሆናለች።

በብሪታኒያ ተመዝግባ በአንድ የሊባኖስ ተቋም አማካይነት ስትንቀሳቀስ የቆየችው የሰመጠችው መርከብ፣ ጥቃቱ በተፈጸመባት ጊዜም 21 ቶን አሞኒየም ናይትሬት የተባለውን ማዳበሪያ ጭና እንደነበር ተነግሯል።

አሁን ደግሞ ረቡዕ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ሦስት መርከበኞች በመገደላቸው በሁቲዎች እርምጃ የተገደሉ የመጀመሪያዎቹ ባሕረተኞች ሆነዋል።

ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል በሚያቋርጡ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም አሜሪካ እና ብሪታኒያ በሌሎች አገራት የባሕር እና አየር ኃይሎች ተደግፈው በየመን ውስጥ ባሉ የቡድኑ ይዞታዎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ቢሆንም በመርከቦች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አልተቋረጠም።