
10 መጋቢት 2024
በኢራን ወንድ እና ሴቶች በአንድነት የሚታደሙባቸው ማናቸውም ዓይንት የሙዚቃ ዝግጅቶች ሕገወጥ ናቸው።
በተለይማ የምሽት ክበቦች የሚታሰቡ አይደለም።
ነገር ግን ኢራን የሕዝቡን በተለይም የሴቶችን የአደባባይ ውሎ እቆጣጠራለሁ በሚል ካቋቋመችው የሥነ ምግባር ፖሊሶች ዕይታ በራቀ መልኩ ምሥጢራዊ የዳንስ የምሽት ክበቦች ተበራክተዋል።
በእነዚህም ፓርቲዎች ላይ መንግሥት የጣለባቸውን ዕገዳ እና በማኅበረሰቡ ነውር ተብሎ የሚታየውን ልማድ በመጣስ ሴት ዲጄዎች ታዳሚዎቻችን ያስጨፍራሉ፤ መድረኩንም ያደምቃሉ።
የኢራንን ባህል የገለባበጠው የ1979 እስላማዊ አብዮት
በኢራን የተከሰተውን የአውሮፓውያኑ 1979 እስላማዊ አብዮትን ተከትሎ አብዮታዊ አይደለም ተብሎ የተፈረጀው የፖፕ ሙዚቃ ዓይነት እንዲታገድ ተደርጓል።
በዚህም ሳቢያ በርካታ ሙዚቀኞች አገሪቷን ጥለው ሸሹ።
በተጨማሪም ሴቶች ዘፋኝ መሆን ሐጢያት ወይም ሐራም ነው ተብሎ ታወጀ።
ከአብዮቱ በፊት ታዋቂ የነበረው የኢራን ፖፕ ሙዚቃ እንዲሁም ካባሬት ተብሎ የሚጠራው ሙዚቃዊ ትዕይንትም ሞተ።
ነገር ግን አንዳንድ ትዕይንቶችን መንግሥታዊ እግድ ወይም አዋጅ ሊያስቆማቸው አልቻለም።
በኢራን መንግሥት “አግባብነት የሌላቸው” የተባሉ የሙዚቃ ካሴቶች እና ሲዲዎች ከውጭ አገራት በድብቅ ወደ አገር ውስጥ ገብተው በየቤቱ መድረስ ጀመሩ።
የአደባባይ የሙዚቃ ፓርቲዎች ቢታገዱም ኢራናውያን መላ በመዘየድ ቤቶቻቸውን ወደ ምሽት ክበቦች መቀየር ጀመሩ። እራት ተበልቶ ከተጠናቀቀ በኋላ መብራቶች ይደበዝዛሉ፣ ሳሎኖችም ወደ ዳንስ ወለልነት ይቀየራሉ።
ልክ በደርግ ዘመነ መንግሥት ወቅት የሰዓት እላፊ አዋጅ በመጣሉ ምክንያት የሙዚቃ ታዳሚዎቻቸውን ከውስጥ ቆልፈው እስከ ጥዋት ድረስ የሚያስጨፍሩት “ዝጉብኝ” እንደተባሉት የምሽት ክበቦች። በኢራን በቤት ውስጥ የሚደረጉት ፓርቶዎች “ሜህሞኒ” ይሰኛሉ።
“በእያንዳንዱ የሜህሞኒ (የቤተሰብ ፓርቲ) መድረኩን በዳንስ የማደምቀው እኔ ነበርኩ” ትላለች በበርሊን መቀመጫዋን ያደረገችው ዲጄ እና የሙዚቃ ፕሮዲውሰር ፓራሚዳ።

- “መኪናችሁን እንወርሳለን” – የኢራን መንግሥት ማስፈራሪያ ሂጃብ ለማይለብሱ ሴቶች10 ሰኔ 2023
- ኢራን ሂጃብ ያላደረጉ ሴቶችን ለመከታተል ካሜራዎችን ገጠመች9 ሚያዚያ 2023
- እስር ላይ የምትገኘው ኢራናዊቷ የኖቤል ሎሬት ናርገስ ሞሐመዲ የረሃብ አድማ መታች7 ህዳር 2023
የፓራሚዳ እናት መጀመሪያ ኢራንን ለቀው ከወጡት መካከል አንዷ ናቸው። ልጃቸው “ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ በሚንገላቱባት” አገር እንዳትኖርም በመፈለጋቸው ነበር ከአገር የተሰደዱት። ከተቃወሟቸው እገዳዎች መካከል አስገዳጅ የሆነውን ሂጃብ መጠምጠምን ነበር።
ጀርመን ኑሯቸውን አድርገው የነበረ ቢሆንም በቤተሰብ ምክንያት ወደ ኢራን በአውሮፓውያኑ 2002 ተመለሱ። በወቅቱ የአራት ዓመት ህጻን የነበረችው ፓራሚዳም በዋና ከተማዋ ቴህራን ትምህርት ጀመረች።
ፓራሚዳ በኢራን ስታድግ በቤት ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎችን እየያየች ነበር። ከፍ ስትልም በድብቅ ይዘጋጁ በነበሩ የሙዚቃ ድግሶች ላይ መገኘት ጀመረች።
“ወንዶች እና ሴቶች በተለያዩ መኪናዎች ተከፋፍለን ከከተማ በመውጣት ነበር ፓርቲውን የምናዘጋጀው። መዚቃ እና መብራቶችን እናዘጋጅና ሁሉም ሰው መጨፈር ይጀምራል” ስትል ፓራሚዳ ታወሳለች።
ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹም ጀምሮ በኢራን ውስጥ አዲስ ዓይነት የፓርቲ ባህል ማበብ ጀመረ።
እንዲሁም ሕገወጥ ሳተላይቶች በየቤቱ መተከላቸውንም ተከትሎ እንደ ኤምቲቪ ያሉ የሙዚቃ ቻናሎች መጡ።

ብዙም ሳይቆይ ሬቭ የተሰኙት ፓርቲዎች በድብቅ መዘጋጀት ጀመሩ። ሬቭ የሚባሉት ፓርቲዎች ፈጠን ያሉ ሙዚቃዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃን ከተጓዳኝ የብርሃን ትዕይንት ጋር የሚያጣምሩ የዳንስ ፓርቲዎች ናቸው።
“ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ፓርቲ ላይ ሄጄ አንድ ዲጄ ሃውስ የተሰኘውን የሙዚቃ ዓይነት ሲያጫውት ሰማሁ” ትላለች ቴህራን ውስጥ ተወልዳ ያደገችው የ40 ዓመቷ ዲጄ ኔሳ አዛዲካህ።
“ዲጄውን ዝም ብዬ እያየሁ ለራሴ የማስበው ነገር ይህንን ሥራ መሥራት እፈልጋለሁ የሚል ነበር” ትላለች።
እንዳሰበችው አልቀረም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኔሳ በድብቅ በሚዘጋኙ “ነጻ ፓርቲዎች” ላይ ዲጄ ሆነች።
በእነዚህ ፓርቲዎች ላይ የሚጫወቱት የሙዚቃ ዓይነቶች ሃውስ እና ቴክኖ የተሰኙት ሲሆኑ፣ ለመታደምም ግብዣ ያስፈልጋል።
በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ፓርቲዎች ይካሄዱ የነበሩት በሼምሻክ የበረዶ መንሸራተቻ መንደር ውስጥ ነው። ስፍራው በዓለም በምሽት ክበቦች የምትታወቀውን የስፔኗ ደሴትን በመውሰድ በቅጽል ስሙ ሺቢዛ ይሰኛል።
በኢራን የሙዚቃ ፓርቲዎች ወንጀል ናቸው። በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ውስጥ ባይጠቀስም፣ በእነዚህ ድብቅ ፓርቲዎች ውስጥ ታድመው የተገኙ ሰዎች በተደጋጋሚ ሲታሰሩ ይሰማል።
የሚቀርባቸውም ክሶች የአልኮች መጠጥ በመጠጣት ከተቃራኒ ጾታ ጋር በአንድ ላይ መገኘት የሚሉ ሲሆኑ፣ እነዚህም ወንጀሎች በእስር ወይም በግርፋት የሚያስቀጡ ናቸው።

ምን ያህል ሰዎች በየዓመቱ እንደሚታሰሩ ባይታወቅም ባለፈው ኅዳር 300 በአንድ የድብቅ ፓርቲ ላይ የታደሙ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን የኢራን መገናና ብዙኃን ዘግበዋል።
እንዲሁም ከቀናት በፊት ከአንድ ዩኒቨርስቲ ወንድ እና ሴቶች ተቀላቅለው ከታደሙበት ፓርቲ 11 ተማሪዎች ተይዘው እስከ ሦስት ሴሚስተር ድረስ ከትምህርት እንዲታገዱ ተደርገዋል።
“ወላጆቼ ሁልጊዜም ፖሊስ እነዚህ ፓርቲዎች ላይ ካገኘኝ ችግር ላይ እንደሚጥለኝ ይነግሩኝ ነበር። ይህም ሁኔታ በጣም ጠንቃቃ አድርጎኛል” ትላለች ኔሳ።
ኔሳም ሆነ ፓራሚዳ ሬቭስ በተሰኙት ፓርቲዎች ላይ በመገኘታቸው እንደ ዕድል ሆኖ ተይዘው አያውቁም። ነገር ግን ሁልጊዜም አደጋ ውስጥ ነኝ በሚለው ስሜት ውስጥ ማደግ የኢራን ሙዚቀኞችን ሕይወት በተለየ መልኩ ሊቀርጸው እንደሚችል ጥያቄ የለውም።
ሁለቱም ዲጄዎች ላለፉት 45 ዓመታት በኢራን ውስጥ እየተካሄደ ያለው የሴቶች እንቅስቃሴ አካል አንደሆኑ ነው የሚሰማቸው።
በኢራን ሴቶችን አስረው የያዟቸው ፖሊሲዎች እና አዋጆች ላይ ለውጥ ይምጣ የሚለው እንቅስቃሴ እየጎላ ሲሆን፣ በተለይም ሂጃቧን በትክክል አልለበሽም በሚል የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀጣጥሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት በመላው ኢራን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች “ሴት፣ ሕይወት፣ ነጻነት” እያሉ ሲዘምሩ ፓራሚዳ ልቧ እንደተነካ ትናገራለች።
“ያ እንቅስቃሴ በሁላችንም ሴቶች መካከል ጥብቅ ቁርኝት እና ትስስር እንዳለ ስላሳየኝ ተስፋ ሰጥቶኛል” ትላለች።
ፓራሚዳ ከሌሎች ኢራናውያን ዲጄዎች አይዳ እና ኔሳ ጋር በመጣመር የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ቅንብሮች ስብስብ የሆነውን “ሴት፣ ሕይወት፣ ነጻነት” ፕሮጀክት ጀምራለች።
በተጨማሪም በኢራን በድብቅ የኤሌክትሮኒስ ሙዚቃ የሚያዘጋጁ ኢራናውያንን ሥራዎችን የሚያሳይ ‘ዲፕ ሃውስ ቴህራን’ የተባለ ሌላ መድረክም አላት።

ለኔሳም ሆነ ለፓራሚዳ እንደ ኢራን ባለች ወግ አጥባቂ እና ሃይማኖታዊ አገር ውስጥ አንዲት ሴት በድብቅ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ፓርቲዎች መሄድ “ፓለቲካዊ” እንደሆነ ይሰማቸዋል።
“የምንፈልጋቸው አብዛኛዎቹ ነገሮች በነውርነት የሚፈረጁ ወይም የተከለከሉ በመሆናቸው ይህንን ስንተላለፍ ሕጎቹን እየጣስን ነው። እነዚህን ድርጊቶችን መፈጸም ወደ እምቢተኝነት እና ተቃውሞ ይቀየራሉ” ስትል ኔሳ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“በኢራን ውስጥ ለበርካታ ሴቶች የተከለከለውን ማድረግ መቻሌ በእውነቱ የተቃውሞ ምልክት ያደርገኛል” ስትል ፓራሚዳ ታስረዳለች።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ የዳንስ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ በወንዶች የተሞላ ቢሆንም፣ በተለይ ፓራሚዳ እና ኔሳ ዲጄነት በጀመሩበት በአውሮፓውያኑ 2010 የበለጠ የጠበበ ነበር።
“ፆተኝነት አሁንም አለ ነገር ግን ትንሽ ይለያል” ትላለች ኢራን ውስጥ የመጀመሪያ ሴት ዲጄ ሆና የሠራችው ኔሳ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሬቭ በተሰኙት ፓርቲዎች ሙዚቃ የሚያጫውቱ ቢያንስ 10 ሴት ዲጄዎች አሉ ትላለች።
“በሕይወቴ ሁሉ ሴት ስለሆንሽ ይህንን ማድረግ አትችይም እየተባልኩ እየተነገረኝ ነው የኖርኩት። እናም እችላለሁ፣ አሳያችኋለሁ እል ነበር” በማለት ፓራሚዳ ታስረዳለች።
ፓራሚዳ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር በሆነው የበርሊኑ የቴክኖ ሙዚቃ ክለብ በርጌይን ዲጄ ናት።
ኔሳም ብትሆን በአውሮፓ ውስጥ ሙዚቃ የማጫወት ህልም አላት።
ሆኖም ለበርካታ ዓመታት የቪዛ ማመልከቻዎቿ ውድቅ ተደርገዋል። ይህ ሁኔታ በኔሳ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ የኢራን አርቲስቶች ላይ የሚያጋጥም ነው።
ፓራሚዳ በአሁኑ ወቅት ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ከጃፓን ብራዚል ድረስ ባሉ ክለቦች እና ፌስቲቫሎች ላይ ሙዚቃዋን ታጫውታለች።
ቢቢሲም ሲያገኛት በስፔኗ ኢቢዛ በሚገኝ ክለብ ሙዚቃ ልታጫውት በዝግጅት ላይ ነበረች። ሆኖም ፓራሚዳ ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ ወደ ኢራን አልተመለሰችም።
“አንደኛው ትልቁ ህልሜ ወደ ቴህራን ተመልሼ ፓርቲ ማዘጋጀት ነው። ያ ምን ያህል አስደናቂ ሊሆን ይችል ነበር?” ስትልም ፓራሚዳ ትጠይቃለች።
ኔሳም ይህንን ስሜት ታስተጋባለች።
ከኢራን ውጭ መጫወት ነጻነት የሚሰማ ቢሆንም፣ ለኔሳ እንደ የኢራን የድብቅ ፓርቲዎችን የሚወዳደር የለም።