"በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነን" የሚል ጽሁፍ የያዘ ታዳጊ
የምስሉ መግለጫ,ከቀናት በፊት 300 የሚደርሱ ተማሪዎች ተጠልፈው ከተወሰዱ በኋላ ከተሰማው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ “በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነን” የሚል ጽሁፍ የያዘ ታዳጊ

ከ 9 ሰአት በፊት

በናይጄሪያ ከቀናት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በታጣቂዎች ከታገቱ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ተጨማሪ በርካታ ተማሪዎች ተጠልፈው መወሰዳቸው ተዘገበ።

በአገሪቱ በተባባሰው የእገታ ድርጊት ሶኮቶ በተባለው ግዛት ውስጥ ከሚገኝ ጋዳ ከተባለ ትምህርት ቤት ወደ 20 የሚጠጉ ተማሪዎች እና ሴቶች ታግተው ተወስደዋል።

የአካባቢው ምክር ቤት አባል የሆኑት ኡስማን ጎራው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከታገቱት ውስጥ 15ቱ ቅዳሜ ጠዋት በታጣቂዎቹ የተወሰዱ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የናይጄሪያ ሠራዊት ሐመስ ዕለት ከምዕራባዊቷ ኩሪጋ ከተማ በተመሳሳይ ታግተው የተወሰዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎችን ለማግኘት ፍለጋ እያካሄደ ነው።

ከእነዚህም መካከል እስካሁን ቢያንስ 28ቱ ከእገታው ማምለጣቸውን የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ኡባ ሳኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሐሙስ ዕለት በተፈጸመው ጠለፋ 280 ተማሪዎች በታጣቂዎቹ ተይዘው የተወሰዱ ሲሆን፣ ይህም ከአውሮፓውያኑ 2021 ወዲህ በናይጄሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተጠለፉበት ድርጊት ነው ተብሏል።

በሞተር ሳይክሎች የመጡ የታጠቁ ወንበዴዎች በትምህርት ቤቱ ላይ ከበበባ በመፈጸም ዕድሜያቸው ከስምንት አስከ 15 የሚሆኑ ተማሪዎችን አፍነው መውሰዳቸውን የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች እና ወላጆች ተናግረዋል።

የናይጄሪያ መንግሥት ወታደሮች ከፖሊስ እና ከአካባቢው የፍለጋ ቡድን ጋር በመሆን በካዱና ግዛት ውስጥ ከሚገኘው ኩሪጋ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ያሉ ጫካዎችን እና በአጎራባች ግዛቶች ውስጥ ጭምር ተማሪዎቹን ለማግኘት አሰሳ እያካሄዱ ነው።

በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም እያንዳንዳቸው ቤተሰቦች በሚባል ደረጃ አንድ ልጃቸው በጠላፊዎቹ ሳይወስዱባቸው እንደማይቀር ይታሰባል።

ከተጠለፉት ተማሪዎች መካከል በታጣቂዎቹ በጥይት ተመትቶ በህክምና ላይ የነበረ የ14 ዓመት ልጅ መሞቱም ታውቋል።

ይህ ጠለፋ የተከሰተው በቦርኖ ግዛት ውስጥ በምትገኝ በአንዲት ራቅ ያለች ከተማ ውስጥ ሴቶች እና ህጻናት ተጠልፈው ከተወሰዱ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ጠለፋው እየተስፋፋ የሄደው የመንግሥት ሠራዊት አባላት በአካባቢው በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው መሆኑን የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

ልጆቻቸው የተጠለፉባቸው ቤተሰቦች የራሳቸውን ቡድን አቋቁመው ልጆቻቸው ያሉበትን ለማወቅ እና ለማስመለስ በሚያደርጉት ጥረት በአጎራባች ግዛቶች የሚገኙ ማኅበረሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው እየጠየቁ ነው።

የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ካሺም ሼቲማ የካዱና ግዛትን እየጎበኙ ሲሆን፣ ከግዛቲቱ አስተዳዳሪ ጋር እንደሚገናኙ ተነግሯል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ የተጠለፉት ተማሪዎች እንደሚመለሱ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከተማሪዎቹ ከመለቀቅ ውጪ “እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቻቸው ሌላ የምንጠበቀው ነገር የለም። ፍትህ ያለማወላወል ይሰፍናል” ሲሉ በኤክስ ገጽ ላይ አስፍረዋል።

ይህ በካዱና ግዛት የተፈጸመው የተማሪዎች የጅምላ ጠለፋ ከ10 ዓመታት በፊት በሰሜን ምሥራቃዊቷ ቺቦክ ከተማ የተጠለፉትን ወደ 300 የሚጠጉ ተማሪዎችን ትውስታ ቀስቅሷል።

በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ወላጆች ልጆቻቸው በታጣቂዎች ይጠለፋሉ የሚል ስጋት ስላላቸው ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ይፈራሉ። በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም።

በካዱና ግዛት የመጨረሻው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጆች የተጠለፉበት ሁኔታ የተከሰተው ከሦስት ዓመት በፊት ከ150 በላይ ተማሪዎች በታጣቂዎች በተወሰዱበት ጊዜ ነበር።

ከጠለፋው ከወራት በኋላም የተማሪዎቹ ወላጆች የማስለቀቂያ ገንዘብ ለጠላፊወቹ ከከፈሉ በኋላ ተለቀዋል።

ከዚህ ክስተት በኋላ የናይጄሪያ መንግሥት ጠለፋዎችን ለማስቀረት በሚል ለማስለቀቂያ ገንዘብ እንዳይከፈል የሚያግድ ሕግ አውጥቶ ነበር።

ሕጉ የተጠለፈን ሰው ለማስለቀቅ ገንዘብ የከፈለ ሰው የ15 ዓመት እስር እንዲቀጣ ያዛል፤ በተጨማሪም ጠላፊዎች ላይ ደግሞ ጠንካራ ቅጣት የሚጥል ሲሆን፣ የተጠለፈው ሰው ከሞተ ደግሞ ቅጣቱ አስከ ሞት ይደርሳል።