ተማሪው የሚማርበት የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ
የምስሉ መግለጫ,ተማሪው የሚማርበት የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ

ከ 7 ሰአት በፊት

አንድ ሩሲያዊ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሚጠቀምበትን የዋይፋይ መለያ ዩክሬንን በሚደግፍ መፈክር በመቀየሩ የአስር ቀናት እስር ተፈረደበት።

በዋና ከተማዋ ሞስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚማረው ተማሪ የዋይፋይ ኔትወርክ መለያውን በሩሲያ ቋንቋ “ስላቫ ዩክሬኒ” ወይም “ክብር ለዩክሬን” ብሎ ቀይሮ በመገኘቱ ነው ለእስር የተዳረገው ተብሏል።

ጉዳዩን ሐሙስ ዕለት የተመለከተው የሞስኮ ፍርድ ቤት “የጽንፈኛ ድርጅቶችን መለያዎችን” በማሳየት በሚል ክስ ጥፋተኛ ሆኖ እንዳገኘው አሳውቋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወረራውን በመቃወም ወይም ዩክሬንን በመደገፍ ተከሰው እስር ወይም ሌላ ዓይነት ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

አሁን እስር የተፈረደበት ተማሪ የተያዘው አንድ የፖሊስ መኮንን የሚጠቀምበትን የኢንተርኔት መስመር ስም ለባለሥልጣናት ካሳወቀ በኋላ ነበር።

የፍርድ ቤት ሰነዶች እንዳመለከቱት የፀጥታ አካላት በዩኒቨርስቲው የተማሪዎች መኖሪያ ውስጥ የሚገኘውን የተማሪውን ክፍል በፈተሹበት ጊዜ የግል ኮምፒውተር እና የዋይፋይ ኢንተርኔት ማገናኛ ራውተር አግኝተዋል።

ፍርድ ቤቱ ተማሪው የዋይፋይ ኔትወርኩ በሚደርስበት ርቀት ውስጥ ለበርካታ ሰዎች “‘ክብር ለዩክሬን’ የሚለውን መፈክር ወደ ሌሎች ለማድረስ” አስቦ ያደረገው ነው ነው ብሏል። አሁን የኢንተርኔት ማገናኛው ራውተር ተወርሶበታል።

“ክብር ለዩክሬን” የሚለው መፈክር ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የዩክሬን ደጋፊዎች የሚያሰሙት መፈክር ነው። ሁለት ዓመት የሆነውን የሩሲያን ወረራ በመቃወም በሚደረጉ ሰልፎች ላይም በተደጋጋሚ የሚሰማ ታዋቂ መፈክር ነው።

ተማሪው በቀረበበት ክስ “የናዚ ምልክትን . . . ወይም የጽንፈኛ ድርጅቶችን ምልክቶች ለሕዝብ በማሳየት” ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ10 ቀናት እስር ተፈርዶበታል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ለከፈቱት ወረራ በተደጋጋሚ እንደምክንያት የሚያቀርቡት በዩክሬን ውስጥ “የኒዮ ናዚ መንግሥት” መኖሩን ነው።

አሁን እስር የተፈረደበት ተማሪ ጦርነቱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት እና በፈጸሙት ድርጊት ቅጣት ከተጣለባቸው በርካታ ሩሲያውን መካከል አንዱ ሆኗል።

ከሳምንታት በፊት እስር ቤት ሳለ በአጠራጣሪ ሁኔታ ሕይወቱ ላለፈው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ ሞት ሐዘናቸውን ለመግለጽ አበባ ያስቀመጡ በመቶወች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ይታወሳል።

ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የምታካሂደውን ጦርነት በአገሪቱ ውስጥ ማንም ሰው “ጦርነት” ተብሎ እንዲጠራ አይፈቀድም። ከዚያ ይልቅ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ተብሎ ነው የሚታወቀው።

በአምነስቲ ኢንትርናሽናል መረጃ መሠረት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት “ፀረ ጦርነት አቋም የሚያንጸባርቁ” ከ21,000 በላይ ሰዎች በሩሲያ “ጨቋኝ ሕጎች” ኢላማ ተደርገዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅቱ አክልሎም “ቀላል የሆኑ ትችቶችን ሳይቀር ለመቆጣጠር ሲባል በጣሙን ፍትሃዊ ባልሆነ የፍርድ ሂደት እስር እና ከፍተኛ ቅጣቶች ይወሰናሉ” ሲል ተችቷል።