ውይይት

11 መጋቢት 2024, 12:25 EAT

የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ባሉበት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም መዘግየት ዙሪያ ውይይት ጀመሩ።

ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት ከአራት ወራትን አስቆጥሯል።

ምንም እንኳ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የተኩስ አቁም ተደርጎ ጦርነቱ ቢቆምም የስምምነቱ አካል የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ተፈጻሚነት መዘግየቶች እንደገጠሙት በሁለቱም ወገን ሲገልጽ ቆይቷል።

በስምምነቱ የተካተቱ በተለይም ከአገር መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት፣ በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ነበሩበት መመለስ የሚሉ ነጥቦች ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ አልሆኑም።

በዚህም ምክንያት ከህወሓት እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲነሱ ቆይተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የካቲት 21/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም በአፍሪካ ኅብረት ፓኔል በኩል እንዲካሄድ ጠይቆ ነበር።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ እና የፌደራል መንግሥት ችግሮቻቸውን ለመፍታት እና መተማመንን ለመፍጠር እየሠሩ መሆናቸውን ካቢኔው ጠቆሟል። በተጨማሪም ካቢኔው፤ “የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ ለመመለስ የሰላም ድርድሩን አካሄድ ከሁለትዮሽ ማዕቀፍ ወጥቶ ወደ አፍሪካ ኅብረት ፓናል እንዲገባ” ወስኗል ብሏል።

ዛሬ ሰኞ መጋቢት 02/2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ዝግ ስብሰባ ላይ የፌደራል መንግሥቱን ወክለው በቅርቡ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ተገኝተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪው ጌታቸው ረዳ፣ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤልን (ዶ/ር) ጨምሮ በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ኃይሎችን ሲመሩ የነበሩት ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ተሳታፊ ሆነዋል።

የ Twitter ይዘትን ይለፉት

ይዘቱን Twitter ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በTwitter. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የTwitter ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።Accept and continue

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ Twitter ይዘት መጨረሻ

ከሁለቱ ወገኖች ተወካዮች በተጨማሪ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ሰላም ያወረደውን ድርድር የአፍሪካ ኅብረትን ወክለው የመሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንዲሁም የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያ በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም በድርድሩ ላይ ታዛቢ እንደነበሩ የተነገረላቸው የአውሮፓ ኅብረት፣ የኬንያ እና የደቡብ አፍሪካ ተወካዮች የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።

ባለ 12 አንቀፁ የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ከማስቆም ባለፈ የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ መልሶ ግንባታ እንዲካሄድ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና በጦርነት እና በረሃብ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ያለመ ነው።

ምንም እንኳ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባይሆንም ከስምምነቱ መፈረም በኋላ በትግራይ ክልል ተቋርጠው የነበሩት ጀረታዊ አገልግሎቶች እንጂምሩ ተደርገው ክልሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ የተመለሰ ቢሆንም፣ በርካታ ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ከሽብርተኛ መዝገብ ውስጥ ስሙ የተፋቀ ሲሆን፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መደበኛ ግንኙነት ተጀምሮ በህወሓት መሪነት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ይታወቃል።