የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን

11 መጋቢት 2024, 15:49 EAT

ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ምርጫ አሸንፈው ፕሬዝደንት ከሆኑ ለዩክሬን ምንም ድጋፍ አይሰጡም ሲሉ የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን ተናገሩ።

ወግ አጥባቂው ጠቅላይ ሚኒስትር በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ከትራምፕ ጋር ከተወያዩ በኋላ “ለዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት አምስት ሳንቲም እርዳታ አያደርጉም። ለዚህ ነው ጦርነቱ ያበቃል የምንለው” ብለዋል።

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ከተመረጡ ጦርነቱን “በ24 ሰዓታት” እንደሚቋጩት ቢናገሩም እንዴት የሚለውን አላስረዱም።

የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር በሚቀጥለው ምርጫ ወዳጃቸው ትራምፕ እንዲያሸንፉ በግልፅ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

“ዩክሬን በእግሯ መቆም እንደማትችል ግልፅ ነው” ይላሉ እሑድ ዕለት ኤም1 ለተሰኘው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቃላቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር።

“አሜሪካ እና አውሮፓውያን ተባብረው ገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ካቆሙ ጦርነቱ ይቋጫል። አሜሪካዊያን ገንዘብ መለገስ ካቆሙ አውሮፓውያን ብቻቸውን ይህን ማድረግ አይችሉም። ይሄኔ ጦርነቱ ይቆማል።”

ኦርባን አክለው ትራምፕ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም “የተሟላ ዕቅድ” አላቸው ቢሉም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ትራምፕ የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ስላሉት ነገር እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጡም።

አርብ ዕለት በተንጣለለው ማር-አ-ላጎ የተሰኘ ግቢያቸው ኦርባንን ያገኙት ትራምፕ ለሀንጋሪው ወዳጃቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጠዋል።

“ከቪክተር ኦርባን የተሻለ ብልህ እና ምርጥ መሪ የትም አይገኝም” ብለዋል።

ትራምፕ እና ኦርባን

ወደ ዩኤስ ለጉብኝት ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርባን የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ሳይገኟቸው ነው የተመለሱት።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ኅዳር በሚካሄደው ምርጫ አንገት ለአንገት እንደሚተናነቁ ይጠበቃል።

የአንድ ሀገር መሪ ወደሌላ ሀገር ለጉብኝት ሄደው ተቀማጩን ፕሬዝደንት ሳያገኙ የቀድሞ መሪ አናግሮ መመለስ የተለመደ ክስተት አይደለም።

የሀንጋሪው ፕሬዝደንት ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ከአውሮፓ መሪዎች በተደጋጋሚ ትችት ይደርሳቸዋል።

ከሌሎች የአውሮፓው ሀገራት መሪዎች በተቃራኒ ለዩክሬን ቤሳቤስቲ ድጋፍ እንደማያደርጉ የሚናገሩት ኦርባን ኪየቭ፤ ኒውክሌር የታጠቀችውን ሩሲያ ልታሸንፍ አትችልም ይላሉ።

የአውሮፓ መሪዎች ዶናልድት ትራምፕ ከተመረጡ ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ይቀንሳል፤ የኔቶ አቅምም ይዳከማል የሚል ስጋት አላቸው።

አሜሪካ ለዩክሬን ልታደርግ ያሰበችው የ95 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባላት ባሰሙት ተቃውሞ ምክንያት እንዳይንቀሳቀስ ሆኗል።

በዶናልድ ትራምፕ የሚመሩት ሪፐብሊካኖች መጀመሪያ የአሜሪካ ድንበርን የሚያጠናክር ገንዘብ እስካልተመደበ ድረስ ለዩክሬን የታሰበው ገንዘብ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንቅንቅ አይልም ብለዋል።

ዩክሬን የጦር መሣሪያ እጦት የገጠማት ሲሆን የሩሲያ ኃይሎች በቅርቡ በምስራቅ ዩክሬን በኩል የሚያደርጉት ግስጋሴ አጠናክረው ቀጥለዋል።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ላለባት ጦርነት የጦር መሣሪያ የምታገኘው ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሲሆን በተቃራኒው ሩሲያ በቂ የጦር መሣሪያ ያላት ሀገር ናት።