
11 መጋቢት 2024, 14:53 EAT
የዌልሷ ንግሥት ለእናቶች ቀን የለቀቀችው ፎቶ በዜና ወኪሎች ውድቅ መደረጉን ተከትሎ “ለተፈጠረ ግራ መጋባት” ይቅርታ ጠይቃለች።
ካትሪን በኬኒስንግተን ቤተ-መንግሥት የማሕበራዊ ገፅ በኩል በወጣ መግለጫ ነው ይቅርታ የጠየቀችው።
“እንደ ማንኛውም ጀማሪ ፎቶ አንሺ አንዳንድ ጊዜ እኔም ፎቶዎችን ለመሟሸት እሞክራለሁ” ብላለች።
የዌልሷ ንግሥት ኬት ሚድልተን ባለፈው ጥር ቀዶ ጥገና ካደረገች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የዌልሱ ንጉሥ ባነሱት ፎቶ ላይ የታየችው።
ፒኤ፣ ጌቲ ኢሜጅስ፣ ኤኤፍፒ፣ ሮይተርስ እና አሶሲየትድ ፕረስ ፎቶውን ከገፃቸው አስወግደዋል።
በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ መግለጫ የለቀቀችው ኬት “ትላንት ባጋራነው ፎቶ ምክንያት ለተፈጠረው ግራ መጋባት ይቅርታ እጠይቃለሁ። በዓሉን ያከበሩ መልካም የእናቶች ቀን እንዳሳለፉ አምናለሁ” ብላለች።
የንጉሣዊው ቤተሰብ የወሬ ምንጮች የኬንሲንግተን ቤተ-መንግሥት በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ ያጋራው ፎቶ “በመጠኑ ተነካክቷል” ይላሉ።
ፎቶው የዌልሷ ንግሥት በሁለት ወንዶች ልጇቿ እና በአንዲት ሴት ልጇ ተከባ በፈገግታ ተቀምጣ ያሳያል።
- የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም መዘግየትን በተመለከተ በዝግ ንግግር ተጀመረ11 መጋቢት 2024
- በ60 ዓመታት ውስጥ ያልተመለሰው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ ከትላንት እስከ ዛሬ11 መጋቢት 2024
- የአሜሪካ የጦር መርከብ በጋዛ ወደብ ለመገንባት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ጉዞ ጀመረች11 መጋቢት 2024

ንግሥቷ ከሁለት ወራት በፊት የሆድ ሕመም ቀዶ ሕክምና ካደረገች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀ ኦፊሴላዊ ፎቶ ነው። ኬት ከቀዶ ጥገናው በኋላ ከሕዝብ ዕይታ ርቃለች።
ፎቶው ሲለጠፍ “ባለፉት ሁለት ወራት ላሳያችሁኝ ድጋፍ እና መልካም ምኞች አመሰግናለሁ” የሚል መልዕክት ታክሎበት ነበር።
ቀጥሎ ደግሞ “ለሁላችሁም መልካም የእናቶች ቀን እመኛለሁ” ይላል።
የንጉሣዊው ቤተሰብ ምንጮች ፎቶው የእናቶች ቀንን ለማሰብ የተነሳ “ቀለል ያለ የቤተሰብ ፎቶግራፍ” ነው ይላሉ።
ምንጮቹ አክለው ፎቶው በፕሮፌሽናል መንገድ የተነካካ ሳይሆን እንዲሁ ከመለጠፉ በፊት ማስተካከያ የተረገበት ነው።
የዌልሷ ንግሥት ካትሪን የቀዶ ጥገና ካደረገች በኋላ ከሕዝብ ዓይን በመጥፋቷ ምክንያት የተለያዩ የሤራ ትንታኔዎች እየተነዙ ይገኛሉ።
ለእናቶች ቀን የተለቀቀው ፎቶ ግን የሤራ ትንታኔውን በማክሸፍ ፈንታ የበለጥ እንዲጋጋል ምክንያት ሆኗል።
አምስት የፎቶ የሚያሰራጩ የዜና ወኪሎች ፎቶው “ተነካክቷል” በሚል ከገፃቸው ላይ እንዲወገድ አድርገዋል።
አሶሲየትድ ፕረስ እሑድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ፎቶውን ከቋቱ ማስወገዱን አስታወቋል።
ሮይተርስም እንዲሁ ፎቶው “ከተለጠፈ በኋላ በተደረገ ማጣራት” እንዲወገድ ማድረጉን ሲገልጥ ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪልም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል።
ጌቲ ኢሜጅስ እና ፒኤ የተሰኙት ወኪሎችም ሰኞ ዕለት ፎቶውን ከድረ-ገፃቸው ማስወገዳቸውን ገልጠዋል።