የሞምባሳው ነጋዴ አዋድ ኦማር

12 መጋቢት 2024, 07:16 EAT

አዋድ ኦማር በሞምባሳ ኦልድ ታውን ገበያ አነስተኛ ሱቅ ዘርግቷል። ከሳዑዲ አረቢያ የሚመጣ ጣፋጭ ቴምር እና ከየመን እና ከጀርመን የሚገባ ማር ይሸጣል።

የአዋድ ትልቁ የገበያ ወቅት አሁን ነው። የረመዳን ወር። ለፆመ ረመዳን ብዙ ሲዘጋጅ ቢከርምም ቀይ ባሕር ላይ ያለው ነገር አሳስቦታል።

ለዚህ ነው ከሌላው ጊዜ ቀደም ብሎ ከውጭ አገር ምርቶች ለሚያመጡለት ደንበኞቹ ትዕዛዝ የሰጠው።

ነገር ግን በዚህ ምክንያት የኬንያ መንግሥት ለረመዳን ያስቀመጠው ከታሪፍ ነፃ ምርት የማስገባት ዕድል አምልጦታል።

የኬንያ መንግሥት ይህን ተግባራዊ ያደረገው ከአውሮፓውያኑ መጋቢት 1 ጀምሮ ለ20 ቀናት ነበር።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባሕር ተሻግረው ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የሚመጡ ዕቃ ጫኝ መርከቦች ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።

ይህ የሆነው የየመን ሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር በኩል ሸቀጥ ጭነው የሚመላለሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ በመሆኑ ነው።

ጥቃቱ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ላይ ጫናውን እያሳደረ ይገኛል። በተለመደው የቀይ ባሕር መንገድ በኩል ማለፍ ያልቻሉ መርከቦች በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገው መጓዝ መጀመራቸው የትራንስፖርት ወጪው ሸማቹ ላይ እንዲያርፍ አድርጓል።

የሞምባሳ ገበያ

ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ “በጣም ጣፋጭ ቴምር ይመረታል። እዚህ በጣም ተወዳጅ ነው። ነገር ግን በዚህ ዓመት ዋጋው ጨምሯል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የትራንስፖርት ዋጋ ማሻቀቡ ነው። በዚያ ላይ የዶላር ምንዛሪም ሌላ የዋጋ ንረት ምክንያት ሆኗል” ይላል አዋድ።

ዘንድሮ 1 የአሜሪካ ዶላር 144 የኬንያ ሺሊንግ ነው። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት የምንዛሪ ዋጋው 127 ነበር።

በያዝነው ዓመት ጣፋጭ ምግቦች ዋጋቸው እጅግ በመናሩ ሸማቹ እንደቀድሞው በቀላሉ ገዝቶ ሊበላቸው አይችልም የሚል ስጋት አለ።

“አንድ የቴምር ካርቶን 17 ዶላር እየተሸጠ ነው። ባለፈው ዓመት በዚሁ ሰዓት 10 ዶላር ነበር። መቼም በውድ ዋጋ ገዝተን በርካሽ ልንሸጠው አንችልም” የሚለው ሌላኛው የሞምባሳ ነጋዴ ፉአድ ኦማር ነው።

ቴምር በመላው ዓለም ለሚገኙ ሙስሊሞች አስፈላጊ ምግብ ነው። ምንም እንኳ ቴምር ዓመቱን ሙሉ ቢበላም በተለይ በረመዳን ፆም ወቅት ኃይል ሰጪ ምግብ ሆነው ይቀርባሉ።

በረመዳን ወቅት በየዕለቱ ፆም ሲያዝ እና ሲፈታ በቴምር ፍሬ ነው።

ተምር

የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር

ወደ ኬንያ የሚገቡ አብዛኞቹ ሸቀጦች መርከብን አማራጭ ያደርጋሉ። በአውሮፕላን እና በመሬት ዕቃዎችን ማጓጓዝ ከመርከብ ጋር ሲነፃፀር በጣም ብዙ ወጪ ያስወጣል።

ለዚህ ነው ብዙውን ጊዜ ጥራጥሬዎች፣ ቴምር፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች በመርከብ የሚጋዙት።

ቢሆንም ቀይ ባሕር ላይ ያለው ሁኔታ መርከቦች አህጉር አቆራርጠው መንገዳቸውን አርዝመው እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል። ይህ ደግሞ ወጪውን ከፍ አድርጎታል።

ይህ የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር በረዥም ጊዜ ምጣኔ ሀብቱን ሊያደቀው እንደሚችል ይገመታል።

የናይሮቢው የምጣኔ ሀብት ምሑር ኬን ጊቺንጋ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ይመጣ የነበረው ስንዴ መስተጓጎል ምን ያህል ነገሮችን እንዳጠላለፈው ያወሳሉ።

“መርከቦች የእህል ምርት ጭነው በቀይ ባሕር በኩል መምጣት ካልቻሉ በአፍሪካ የስንዴ ዋጋ ከፍ ማለቱ አይቀሬ ነው” ይላሉ።

“አቅርቦት ሲቀንስ እና ፍላጎት ሲጨምር የአንድ ምርት ዋጋ ከፍ ይላል። የስንዴ ዋጋ የናረው ለዚህ ነው። ይህንን ወደ ነዳጅ ገበያ ወደ መኪና ብንወስደው የዋጋ ግሽበቱ ከፍ ይላል ማለት ነው።”

የምጣኔ ሀብት ሙያተኛቸው እንደሚሉት ይህ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ባንኮች ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር የወለድ መጠንን መጨመር ነው። ይህ በተራው የመበደር አቅምን እና ንግድን የሚያዳክም ሲሆን ለጠቅላላው ምጣኔ ሀብት አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ነው።

የቅንጦት ዕቃዎች

ሁቲዎች በቀይ ባሕር የንግድ መስመር ላይ የፈጠሩት ስጋት በምግብ ምርቶች ላይ ብቻ የመጣ አይደለም። የቅንጦት ዕቃቆች ተብለው የሚመደቡ እንደ መኪና ያሉ ምርቶችም ችግሩ ነክቷቸዋል።

መኪና አስመጪው ሌናርድ ንጂሩ በሞምባሳ በኩል ከአውሮፓ፣ ከዱባይ፣ ከሲንጋፖር እና ከጃፓን የሚያስመጣቸው መኪኖች በጊዜ ባለመድረሳቸው ሸማቾች ገንዘባቸውን እያጡ ነው።

ሌናርድ እንደሚለው ያገለገሉ መኪኖች እና ሚኒ ባሶች ከተመረቱ ስምንት ዓመት ካለፋቸው ወደ ኬንያ ማስገባት ክልክል ነው።

“ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ መኪኖቹን ማስገባት ካልተቻለ ኪሳራ ነው ማለት ነው” የሚለው የመኪና አስመጪ ብዙ ነጋዴዎች ጉዞው በመጓተቱ የመጨረሻው ቀን እንዳመለጣቸው ይናገራል።

የኬንያ ዓለም አቀፍ ትራንስፖርት እና መጋዘን ማኅበር ቀነ-ገደቡ ያለፈባቸው ነጋዴዎች መኪናዎቻቸውን ማስገባት እንዲችሉ ከመንግሥት ጋር ድርድር ላይ እንደሆነ ለቢቢሲ ይናገራል።

ይህ ካልሆነ እነዚህ መኪኖች ይጨፈለቃሉ፣ አሊያም ከመዝገብ እንዲፋቁ ይደረጋል፤ ካልሆነ ደግሞ በባለቤቱ ወጭ ወደ መጡበት አገር ይመለሳሉ።

ከውጭ ሀገር የሚመጡ ተምሮች

ባለፈው ታኅሣሥ ወደ ኬንያ የመጡ መከርቦች ቁጥር ከያዝነው ወር ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ አሳይቷል። ይህ ለምን ሆነ የሚለውን ለማጣራት ለኬንያ ባሕር በር ባለሥልጣን ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

አስመጪ እና ላኪዎችን የሚወክለው ማኅበር በበኩሉ በተመሳሳይ ወቅት የመጡ መርከቦች ቁጥር ትንሽ ነው ይላል።

“ለአንድ ደንበኛ በወር እስከ 30 ጭነት እቆጣጠር ነበር። ነገር ግን አሁን ቁጥሩ ቀንሷል። አንዳንድ መርከቦች በሳምንት አንድ ጊዜ ይመጣሉ። አሁን አሁን በወር አንድ ጊዜ ነው የሚመጡት” ይላል ከወኪሎቹ አንዱ የሆነው ሳሊም ሙባረክ።

ከአውሮፓ እና እስያ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የሚመጡ መርከቦች ዋነኛ መስመራቸው ቀይ ባሕር ነው።

ነገር ግን አሁን አሁን 5 ሺህ ማይል አቋርጠው በደቡብ አፍሪካው ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል አድርገው ነው የሚመጡት።

የመርከብ ኩባንያዎች በዚህ ጉዞ ምክንያት ተጨማሪ የኢንሹራንስ ገንዘብ እና ለመርከበኞች ከሌላው ጊዜ ላቅ ያለ ደመወዝ መክፈል አለባቸው። ይህ ክፍያ በእንግሊዘኛው ‘ዴንጀር መኒ’ ይባላል።

የአፍሪካ ዲቨሎፕመንት ባንክ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የነዳጅ እና የሸቀጥ ዋጋ መጨመር የእርስ በርስ ግጭትን ሊያባብስ ይችላል ብሏል።

የሞምባሳ ነጋዴዎቹ እነ አዋድ በቀይ ባሕር ያለው ክስተት ተስተካክሎ ንግዱ እንደ ቀድሞው እንዲቀላጠፍ ነው ምኞታቸው።

“ረመዳን ያለ ቴምር ሊሆን አይችልም። በእምነታችን እንደተማርነው ፆም ስንፈታ ቴምር መቅመስ አለብን።”