
12 መጋቢት 2024, 08:02 EAT
ቦይንግ የተሰኘው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ የቀድሞ ሠራተኛ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።
የቀድሞው ሠራተኛው የድርጅቱን ምስጢር በማጋለጥ ይታወቅ ነበር።
ጆን ባርኔት ለቦይንግ ፋብሪካ ለ32 ዓመታት የሠራ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር ጡረታ የወጣው።
ከመሞቱ በፊት ባሉት ቀናት ቦይንግ በተመሠረተበት ክስ ላይ ምስጢር አሾላኪ ሆኖ ቀርቦ ምስክርነቱን እየሰጠ ነበር።
ቦይንግ በቀድሞው ሠራተኛው ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጧል።
የቻርልስተን ክፍለ-ግዛት ባለሥልጣናት የግለሰቡን መሞት ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ባለሥልጣናቱ ግለሰቡ የሞተው ቅዳሜ ዕለት “ራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት” ነው ብለው ፖሊስ ምርመራ መክፈቱን አሳውቀዋል።
ባርኔት ለ32 ዓመታት ከሠራበት ድርጅት ጡረታ የወጣው በጤናው ምክንያት እንደሆነ ተገልጦ ነበር።
ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ኖርዝ ቻርልስተን በሚገኘው የድርጅቱ ማምረቻ ጣቢያ 787 ድሪምላይነር የተሰኘው ውድ አውሮፕላን ጥራት ተቆጣጣሪ ሆኖ ሲያገለግለግ ቆይቷል።
በ2019 ባርኔት፤ ሠራተኞች ጫና እያደረባቸው ጥራታቸው የወረዱ ቁሳቁሶችን አውሮፕላኖች ላይ እየገጠሙ ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
ግለሰቡ አክሎ በተለይ በኦክስጅን መሣሪያዎቹ ላይ ችግር መኖሩን ጠቁሞ በአደጋ ጊዜ ከአራት የኦክስጅን ጭምብሎች አንዱ ላይሠራ ይችላል ሲል መረጃ አሾልኳል።
- የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም መዘግየትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዝግ ንግግር ተጀመረ11 መጋቢት 2024
- ፆም በሰውነታችን ውስጥ የሚያስከትለው ለውጥ እና የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው?12 መጋቢት 2024
- የዌልሷ ንግሥት ለእናቶች ቀን ‘የተነካካ’ ፎቶ በመልቀቋ ይቅርታ ጠየቀች11 መጋቢት 2024

ጆን ባርኔት እንደሚለው ወደ ሳውዝ ካሮላይና የድርጅቱ ጣቢያ ከተዛወረ በኋላ አውሮፕላኖች ቶሎ እንዲደርሱ በሚል በፍጥነት ይመረቱ ነበር፤ ይህ ደግሞ ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ ይጥለዋል።
ቦይንግ ይህን ወቀሳ ፍፁም ሐሰት ነው ሲል ያስተባብላል።
ግለሰቡ ለቢቢሲ ጨምሮ እንደተናገረው ኩባንያው የሚገባውን መመሪያ እየተከተለ ስላልሆነ አንዳንድ ቁሳቁሶች ሳይገጠሙ እየተረሱ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ቁሳቁሶች ከቆሻሻ መጣያ እየተነሱ ተገጥመው አውሮፕላኑ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ሲልም ተናግሮ ያውቃል።
ባርኔት ይህንን በተለመከተ ያለውን ስጋት ለአለቆቹ ቢያሳውቅም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ይናገራል።
የግለሰቡን ቅሬታ ቦይንግ ቢያስተባብለውም በ2017 የአሜሪካው አቪዬሽን ባለሥልጣን [ኤፍኤኤ] ባደረገው ምርመራ አንዳንድ የባርኔት ቅሬታዎች ውሀ ያነሳሉ ብሎ ነበር።
በተለይ የአንዳንድ ቁሳቁሶች ጥራት ማነስ እና የኦክስጅን ጭምብሎች ችግር ማስተዋሉን ያሳወቀው ባለሥልጣኑ ቦይንግ ይህን በፍጥነት እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ባርኔት ጡረታ ከወጣ በኋላ ከድርጅቱ ጋር ለረዥም ጊዜ የቆየ እሰጥ-አገባ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ባወጣሁት የደኅንነት ስጋት ምክንያት የሥራ ሕይወቴ እንዲበላሽ እንዲሁም ያልሆንኩትን እንደሆንኩ አድርጎኛል ሲል ድርጅቱን ቢከስም ቦይንግ ይህን ያስተባብላል።
ባርኔት በሞተበት ወቅት ወደ ቻርልሰተን ክፍለ ግዛት የመጣው ከዚህ ጋር በተያያዘ ላለበት የሕግ ሂደት ቃለ-ምልልስ ለመስጠት ነበር።
ቅዳሜ ዕለት ለነበረው ቀጠሮ ሳይገኝ በመቅረቱ የት እንዳለ ሲጣራ ያረፈበት ሆቴል የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ላይ መኪናው ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።
ቦይንግ እና የድርጅቱ አስፈላጊ ቁሳቁሶች አምራች የሆነው ስፒሪት ኤሮሲስተምስ በጥራት ምክንያት በርካታ ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል።
ባለፈው ጥር አንድ አዲስ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከፖርትላንድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ በሩ ተገንጥሎ መውደቁ ይታወሳል።
የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት ጉዳዩን አጣርቶ አራት አስፈላጊ ብሎኖች በሥርዓቱ አልተገጠሙም ብሏል።