የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ

12 መጋቢት 2024, 09:23 EAT

የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ዩክሬን “ነጭ ባንዲራ የማንሳት ድፍረት ሊኖራት ይገባል” ማለታቸውን ተከትሎ ኪዬቭ የቫቲካን ተወካይዋን ጠርታለች።

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሊቀ-ጳጳሱ በሰጡት አስተያየት ኪዬቭ “መከፋቷን” ለተወካዩ ኑንሲዮ ቮሎድሚር ኩልቦካስ ነግረናቸዋል ብሏል።

በተያያዘ ዜና ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዩክሬን ከሰሞኑ ከገጠማት ሽንፈት “አገግማ አሁን መረጋጋት ላይ ትገኛለች” ብለዋል።

ነገር ግን የዩክሬን አጋሮች ለሀገሪቱ የሚያደርጉት እርዳታ “እጅጉን ቀንሷል።”

ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ከስዊትዘርላንዱ አርኤስአይ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ በፅሑፍ ከወጣ በኋላ ነው ጉዳዩ ዩክሬንን ያስቆጣው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የቃለ-ምልልሱን ፅሑፍ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ሊቀ-ጳጳሱ “ጠንካራ የምንለው ሁኔታውን ተመልክቶ፤ ለሕዝብ አስቦ፤ ነጭ ባንዲራ ለማንሳት ድፍረት ያለውንና ለድርድር የሚቀመጠውን ነው” ብለዋል።

በጦርነት አውድማ ነጭ ባንዲራ ማለት እጅ የመስጠት ምልክት ነው።

የቫቲካን ቃል-አቀባይ በሰጡት አስተያየት ሊቀ-ጳጳሱ የተናገሩት ጦርነቱን በድርድር ስለማቆም እንጂ እጅ ስለመስጠት አይደለም።

ነገር ግን ዩክሬን በሊቀ-ጳጳሱ አስተያየት መከፋቷን ከመግለጥ ወደኋላ አላለችም።

የቫቲካኑ ተወካይ ወደ ሀገራቸው መጠራታቸውን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “እነሱ [ሩሲያ] ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲጥሱ ከማበረታታት ይልቅ ሊቀ-ጳጳሱ የዓለም መንግሥታት ተባብረው ጥሩ መጥፎውን እንዲረታ መልዕክት ማስተላለፍ፤ ለአጥቂው ሳይሆን ለተጠቂው ማዘን ነበረባቸው” ብሏል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ከሁለት ዓመታት በላይ ቢሆንም ዩክሬን እጅ መስጠት የሚለውን ሐሳብ በእጅጉ ትቃወማለች።

“መቋቋም እንችላለን፤ ማሸነፍ እንችላለን” ብለዋል ዜሌንስኪ ሰኞ ዕለት ባሰሙት ንግግር።

ፕሬዝደንቱ ለአንድ የፈረንሳይ ሚድያ በሰጡት አስተያየት ዩክሬን “በምስራቅ በኩል የመጣውን የሩሲያ ጦር አስቁማለች” ሲሉ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ አክለው ከሩሲያ የሚመጣውን ስጋት ለመቀነስ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝም የመከላከያ ምሽግ መሥራቷን ጠቁመዋል።

ቢሆንም የአሜሪካ የደኅንነት ሙያተኞች ሰኞ ለሴናተሮች በሰጡት ቃል ጦርነቱ ወደ ሩሲያ እያደላ ነው፤ በቂ እርዳታ ካልተደረገ ዩክሬን በ2024 “ከባድ ክስረት” ይደርስባታል ብለዋል።

ለሴኔቱ የደኅንነት ኮሚቴ ሐሳባቸውን የሰጡት የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ “ዩክሬኖች ድፍረት እና ጥንካሬ አላጡም፤ የጦር መሣሪያ እንጂ” ሲሉ ተናግረዋል።

አሜሪካ ለዩክሬን ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል ቁንጮዋ ብትሆንም በቅርቡ ልታደርግ ያሰበችው እርዳታ እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል።

ለዩክሬን የታሰበው 95 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ኮንግረስ ቀርቦ አብላጫ ድምፅ ባለማግኘቱ ለዩክሬን ሊደርስ አልቻለም።

በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት የሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውጤትም ለዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ነው።

ዜሌንስኪ ከሰሞኑ ለደረሰባቸው ሽንፈት የመሣሪያ ድጋፍ እጥረትን ተወቃሽ አድርገዋል።