ከጥቂት ዓመታት በፊት በህንድ የተነሳው ተቃውሞ

12 መጋቢት 2024, 07:49 EAT

የሕንድ መንግሥት ፀረ ሙስሊም ተብሎ የተተቸውን አወዛጋቢ የዜግነት ማሻሻያ ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ።

የዜግነት ማሻሻያ ሕግ (ሲኤኤ) የተባለው ሕግ ከፓኪስታን፣ ከባንግላዴሽ እና ከአፍጋኒስታን የሚመጡ ሙስሊም ያልሆኑ የሌላ አናሳ ሃይማኖቶች ተከታዮች ዜግነት እንዲጠይቁ የሚያስችል ነው።

ይህም ለግዞት የተዳረጉ ሰዎችን እንደሚረዳ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ሕጉ በአውሮፓውያኑ 2019 ሲጸድቅ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈበት እና የታሰሩበት ሕዝባዊ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር።

የሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሚት ሻህ እንዳሉት በብጥብጡ ምክንያት ሕጉ ተግባራዊ ለመደረግ ቢዘገይም በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ይውላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ “የሕገ መንግሥታችን አዘጋጆች በሌሎች አገራት ለሚኖሩ ሒንዱዎች፣ ሲኮች፣ ቡድሂስቶች፣ ጃይንስ፣ ፋርሲስ እና ክርስቲያኖች የገቡትን ቃል እውን አድርገዋል” ሲሉም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የ“ሲኤኤ 2019” መስፈርቶችን የሚያሟሉ ብቁ የሆኑ የሌላ አገር ዜጎች የሕንድ ዜግነታቸውን ለማግኘት በበይነ መረብ ላይ ማመልከት እንደሚችሉም አስታውቋል። ማመልከቻዎችንም ለመቀበል ድረ ገጽ እንደተዘጋጀ ተገልጿል።

አዲሱ የዜግነት ማሻሻያ ሕግ ትግበራ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገዥ ፓርቲ የሒንዱ ብሔረተኛው ባህራቲያ ጃናታ በምርጫ ቅስቀሳ ቃል ከገባቸው ጉዳዮች አንድ ነው።

በአሁን ወቅት እየተተገበረ ያለውን ሕገወጥ ስደተኞች የሕንድ ዜግነት እንዳይኖራቸው የሚከለክለውን 64 ዓመት ያስቆጠረውን የሕንድ ዜግነት ሕግንም አሻሽሏል።

በአዲሱ ሕግ ዜግነት የሚጠይቁ ከፓኪስታን፣ ከባንግላዴሽ ወይም ከአፍጋኒስታን የመጡ ስደተኞች በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 31/2014 ጀምሮ ሕንድ መግባታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።

የሕንድ መንግሥት የተሻሻለው ሕግ ተግባራዊ የሚሆንበትን ትክክለኛ ቀን አልሰጠም።

ከሕግ ማሻሻሻያው ጋር ተያይዞ በተለያዩ ግዛቶች ተቃውሞ ተጀምሯል። በተለይም አሳም በተባለችው ግዛት በአውሮፓውያኑ 2019 በከፍተኛ ሁኔታ መዛመት የቻለውን ተቃውሞ የመራው የአሳም የተማሪዎች ኅብረት ሁሉንም እንቅስቃሴዎች የመዝጋት የተቃውሞ ጥሪ አቅርቧል።

በደቡባዊቷ ኬራላ ግዛት ገዢ የሆነው የኮሚኒስት ፓርቲ፣ አገራዊ ተቃውሞ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል። “ሕጉ ሕዝቦችን ለመከፋፈል እንዲሁም የማይሆኑ ስሜቶችን ለማነሰሳት እና የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆችን ለማፍረስ ያለመ ነው” ሲሉ ዋና ኃላፊው ፒናራይ ቪራያን ተናግረው በግዛታቸው ተግባራዊ እንደማይሆን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።