March 12, 2024 – Konjit Sitotaw
የሱዳን ወታደራዊ መሪ በረመዳን የጾም ወር የቀረበውን የተኩስ አቁም ጥሪ ውድቅ አደረጉ
የሱዳን ጦር ሰራዊት ምክትል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ያሲር አል አታ፣ በረመዳን የጾም ወር ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (RSF) ጋር የሚያደርጉትን ግጭት እንዲያቆሙ የተኩስ አቁም ጥሪ ቢቀርብም የቀረበውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸው ተነግሯል።
በሱዳን ካርቱም፣ ዳርፉር፣ ኮርዶፋን እና አልጃዚራ ለ11 ወራት በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉና በጦር ሰራዊቱ መሃከል የተደረገው እንዲሁም በሀገሪቱ በርካታ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለውን ጦርነት እንዲቆም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው አርብ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
የሱዳን ጦር ሰራዊት ምክትል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ያሲር አል አታ በቅዳሜ እለት በሀገሪቱ የፍትህ እና የእኩልነት ንቅናቄ (JEM) ሃይሎችን የማስመረቅ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የተኩስ አቁም ጥያቄን እንደማይቀበሉ እና ወታደሩ እና ህዝቡ በሶስተኛ ወገን የሚቀርብን የእርቅ ሰላም ስምምነት ጥያቄ እንደማይቀበሉ ማሳወቃቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረነበውን የእርቅ ጥሪ ተከትሎ፣ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ (RSF) ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ፣ ” ለማድረግ የታቀደውን ሰብዓዊ የተኩስ አቁም በመቀበል፣ በጋራ ስምምነት ላይ ተመስርቶ የተደረሱ እርምጃዎችን ለመውሰድ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን ” ማለታቸውን አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል።
የጦር ሰራዊቱ ምክትል አዛዥ አል አታ በሁለቱ ሀይሎች መሃከል ድርድር ሊደረግ የሚችለው ፥ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ወታደሮች በዳርፉርና በኮርዶፋን የያዙትን ከተሞች በመልቀቅ ከካርቱም መውጣታቸው ሲረጋገጥና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ሲያስረክቡ እንደሆነ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል ነው የተባለው።