
ከ 5 ሰአት በፊት
“በረመዳን ወቅት እኛ እየፆምን ነው፤ እነሱ [በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን] ግን እየተራቡ፣ እየሞቱ ነው” ነው ይላል ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኘው ካሊድ።
በአየርላንድ፣ ቤልፋስት የተወለደው እና ባለቤቱ እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት በጋዛ የተገደሉበት ፍልስጤማዊ በሙስሊሞች ዘንድ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራውን የረመዳንን ወር እንደ ከዚህ ቀደሙ ማክበር እንደሚቸገር ይገልጻል።
ካሊድ ኤል ኤስታል በኅዳር ወር ጋዛን ለቀው ከሸሹት ሁለት ልጆቹ ጋር መገናኘት ችሏል።
ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በጋዛ ሰርጥ ለቀሩት አባቱ፣ ሁለት ወንድሞቹ እና ጓደኞቹ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ነው የሚናገረው።
“ከቀን ወደቀን ሁኔታው እየከፋ ነው” ሲልም የጋዛ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱን ያስረዳል።
“በጋዛ እየሆነ ያለው ነገር የማይታመን ነው። ሁሉም ተስፋ ቆርጧል። ሕዝቡ በልመና እና ተማጽኖ ላይ ነው። ሁሉንም ነገር መለወጥ እንደምችል ይሰማቸዋል። በርካቶች ከጋዛ እንዳስወጣቸው ይደውሉልኛል” ይላል።
መስከረም መጨረሻ ላይ ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት ሰንዝሮ 1200 ሰዎች ሲገደሉ፤ 253 ታጋቾች ደግሞ ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
እስራኤል ምላሽ ባለችው በተቀናጀ የማያባራ ጥቃት ከ30 ሺህ 900 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ከሚገኘው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ የተከሰተ ሲሆን፣ የረሃብ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት አሳስቧል። 300 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በምግብ እጦት እየተሰቃዩ እንደሆነም ተገልጿል።
- ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 103 ዘመዶቹን ያጣው ፍልስጤማዊ አባት27 የካቲት 2024
- ከረመዳን ጾም ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ እሳቤዎች21 ሚያዚያ 2022
- የሳተላይት ምስሎች ግማሽ የሚሆኑት የጋዛ ሕንጻዎች በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መውደማቸውን አሳዩ31 ጥር 2024
“ፍጹም የተለየ ነው”
ካሊድ ጦርነቱ የበርካታ ፍልስጤማውያንን ሕይወት በጋዛ እየቀጠፈ ባለበት በዚህ ወቅት ረመዳንን ለማክበር ማሰብ እንደሚያዳግተው ይናገራል።
“ረመዳን ለእኛ ትልቅ ነው። እኛ ወሯን በልዩ ሁኔታ ነው የምናሳልፈው። በአሁኑ ወቅት በጋዛ ውስጥ ካለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው” ይላል።
ካሊድ ኤል ኢስታል ያሁኑን አያድርገው እና ከዚህ ቀደም ከባለቤቱ ጋር ለረመዳን ከፍተኛ ዝግጅት ያደርጉ ነበር። ከረመዳን በፊት ባሉት ቀናትም ከባለቤቱ ጋር ለዝግጅቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ይሸምታሉ። ቤታቸውንም በመብራት ያስጌጡታል።
በአሁኑ ረመዳን ግን ከቤትም አልወጣም።
“በአሁኑ ወቅት የተለየ ነገር ለማድረግ ማሰብ አልችልም። ዝም ብሎ ነው የሚያልፈው። በጋዛ እየተከሰተ ያለውን ነገር ማሰብ ራሱ ህመም የሚፈጥር ነው” ይላል።

ጥቂት ስለ ረመዳን
ረመዳን በእስልምና የዘመን አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር የአረብኛ ስም ነው። ከጨረቃ ዑደት ጋር ተያይዞ የረመዳን ቀን የሚጀመርበት ዕለት በየዓመቱ ይለያያል። የዘንድሮውም ጾም መጋቢት 2/ 2016 ተጀምሯል።
የረመዳን ወር የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁርዓን ለነብዩ መሐመድ የተገለጠበትን ጊዜ የሚዘክር ነው።
ከእስልምና አምስት አምዶች አንዱ የሆነው የረመዳን ወር፤ በፆም እና በጸሎት የሚታሰብ ሲሆን፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ይህን ወር የእምነቱን ሥርዓት ጠብቆ እንዲያሳልፈው ይጠበቃል።
በረመዳን የፆም ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙ ሁሉም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፤ ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ ከማንኛውም ዓይነት ምግብ እና መጠጥ ይቆጠባሉ።
የፆሙ ዋና አላማ መንፈሳዊነትን ማጎልበት ሲሆን፣ በርካቶች ጸሎት በማድረግ፣ ከተለያዩ ነገሮችን ራስን በመቆጠብ፣ የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት፣ በደግነት፣ በትዕግስት እና በይቅር ባይነት የፆሙን ወቅት እንዲያሳልፉ ይበረታታሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ቤልፋስት የተወለደው ካሊድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አባቱ በመምህርነት ያገለግሉበት ከነበረው ኩዊንስ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ቦታኒክ ከሚባለው ሰፈር አካባቢ ነው የተማረው።
የስምንት ዓመት ልጅ እያለም ነው ቤተሰቡ ወደ ጋዛ የተዘዋወረው፣ ባለቤቱንም የተዋወቃት እዚያው አሽዋክ በተሰኘ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ በነበረበት ወቅት ነው።
ባለቤቱ በጋዛ ስትገደል እሱ በሥራ ምክንያት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ነበር።
ከአራት ዓመት ልጁ አሊ እና ከአንድ ዓመት ሴት ልጁ ሳራ ጋር እንዲያገናኙትም እርዳታ ሲማጸን ነበር።
ህጻናቱ በአየርላንድ መንግሥት እርዳታ በኅዳር ወር ጋዛን ለቀው በግብፅ በኩል እንዲወጡ ተደርገዋል።

“እያንዳንዷ ቀን ትግል ናት”
በጋዛ ጦርነት አሰቃቂ ሁኔታዎችን ለመመልከት የተገደዱት ልጆቹ አብረውት ደብሊን ከተማ ውስጥ ይኖራሉ።
በየቀኑ ሁኔታቸውም እየተሻሻለ እንደሆነም ይናገራል።
ልጁ አሊ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት እንዲሁም እንግሊዝኛ መማር ጀምሯል።
“አሁን በሕይወቴ ውስጥ የምሠራቸውን ተግባራት ሁሉ የማከናውንባቸው ምክንያቶቼ እነሱ ናቸው” ይላል ልጆቹን።
በቅርቡ የተከበረው የእናቶች ቀን ለልጆቹ እንዴት ፈታኝ እንደነበረም ለመናገር ካሊድ ቃላት ያጥሩታል።
“እያንዳንዷ ቀን ትግል ናት። ቀን ላይ በሥራ ስለምጠመድ ብዙም አላስብም። ነገር ግን ማታ ማታ ስለ ሁሉም ነገር፣ ስለ ቤተሰቤ፣ ስለ ባለቤቴ ግድያ ያለማሰለስ አስባለሁ” ሲልም ያስረዳል።
በጋዛ ውስጥ የቀሩት ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ሁኔታ ቀን ከሌት የሚያሳስበው እና የሚያስጨንቀው ጉዳይ ነው። ምንም ነገር አለማድረግ አለመቻል እና የአቅመ ቢስነት ስሜትም ይሰማዋል።
“ስለ ሁሉም ሰው እጨነቃለሁ። አንዳንድ ጊዜ ግን እየሆነባቸው ያለውን ነገር ላለማሰብ እና ለመርሳት እፈልጋለሁ” ይላል።