ትሪስታን ቴት (ግራ) እና አንድሩ ቴት
የምስሉ መግለጫ,ትሪስታን ቴት (ግራ) እና አንድሩ ቴት

ከ 3 ሰአት በፊት

አወዛጋቢው ተጽዕኖ ፈጣሪ አንድሩ ቴት እና ታናሽ ወንድሙ ትሪስታን ቴት ለዩናይትድ ኪንግደም ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ ሲል የሮሜኒያ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ፍርድ ቤት ይህን ያለው ሁለቱ ወንድማማቾች በዩናይትድ ኪንግድም የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነው።

ትናንት የዋለው ፍርድ ቤት አንድሩ እና ትሪስታን ቴት በሮሜኒያ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የቀረበባቸውን የክስ ሂደት ካጠናቀቁ በኋላ ለዩኬ ተላልፈው እንደሚሰጡ ነው የወሰነው።

ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ወንድማማቾቹ ከእስር ተለቀዋል።

ከችሎቱ በኋላ አንድሩ ቴት ለጋዜጠኞች “እኛ ነጹህ ሰዎች ነን በጊዜ ሂደት ሁሉም የሚረዳው ይሆናል። የፍርድ ሂደቱን አጠናቀን ስማችንን ነጻ ማድረግ እንፈልጋለን” ብሏል።

ሁለቱ ወንድማማቾች በዩኬ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ብሪታኒያ ውስጥ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ፈጽመዋል የሚል ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ነው።

የ37 ዓመቱ አንድሩ ቴት እና የ35 ዓመቱ ወንድሙ የቀረቡባቸውን ክሶች “ሙሉ በሙሉ ውድቅ” እንደሚያደርጉ ተወካያቸው ገልጸዋል።

የብሪታኒያ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያለው አወዛጋቢው አንድሩ ቴት በሰዎች የሕገ-ወጥ ዝውውር እና ከመድፈር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ሮሜኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ሲሆን ከእስር ቤት ወጥቶ ከወንድሙ ጋር በቁም እስር ለረዥም ጊዜ ቆይቷል።

ወንድማማቾቹ ተጥሎባቸው የነበረው የቁም እስር ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተነሳላቸው ቢሆንም ሮሜኒያን ለቀቀው እንዲወጡ አልተፈቀደላቸውም።

ራሱን “ሴቶችን አናሳ አድርጎ የሚመለከት ሰው” አድርጎ የሚገልጸው ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚያጸባርቃቸው አመለካከቶች ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ባለፉት ዓመታት እጅጉን ጨምሯል።

ከዚህ ቀደም በነበረው የስፖርት ሕይወቱ አራት ግዜ የኪክቦክስ የዓለም ሻምፒዮና መሆን የቻለው ቴት በተለይ በቲክቶክ አማካይነት ሴቶችን በተመለከተ የሚሰጣቸው “አጸያፊ እና አስነዋሪ” የተባሉት አስተያየቶቹ ዝነኛ አድርገውታል።

አንድሩ ቴት ሴቶችን በተመለከተ በሚሰጣቸው አስተያየቶች ምክንያት ከፌስቡክ፣ ከኢንስታግራም እና ከዩቲዩብ ታግዷል።

ቴት ሴቶችን ከኮምፒዩተር ፊትለፊት አስቀምጦ በኢንተርኔት አማካይነት ወንዶችን እንዲያማልሉ በማድረግ ከወንዶች በሚቀበለው ገንዘብ ሃብት እንዳፈራ ይነገራል