ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ

ከ 4 ሰአት በፊት

የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ምርጫ ለመፎካከር የሚያስችላቸውን ድምፅ አገኙ።

የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ከ8 ወራት በኋላ ኅዳር 2017 ዓ.ም. ይካሄዳል።

አራት ግዛቶች፣ አንድ የአሜሪካ ክፍል እና በመላው ዓለም የሚኖሩ ዴሞክራቶች ማክሰኞ ዕለት ዕጯቸውን መርጠዋል።

ይህ ማለት በአውሮፓውያኑ 2020 የተመለከትነው የባይደን እና ትራምፕ ፍጥጫ በ8 ወራት ውስጥ ይደገማል።

ሁለቱ ቁንጮ ፓርቲዎች በቅርቡ በየፊናቸው በሚያደርጉት ስብሰባ ዕጩዎቻቸውን በይፋዊ መንገድ ያስተዋውቃሉ።

የ81 ዓመቱ ፕሬዝንት ማክሰኞ አመሻሹን በሰጡት ቃል ደጋፊዎቻቸው እንደገና እንዲወዳደሩ በሳቸው ላይ እምነት ስለጣሉ የተሰማቸውን “ክብር” ገልጠዋል።

ባይደን “ጊዜው ከትራምፕ የሚመጣው ስጋት እጅግ ላቅ ያለበት ነው” ሲሉ አክለዋል።

የምጣኔ ሀብቱ መነቃቃቱን ዋቢ አድርገው “አሜሪካ ወደ ቀደመ አቋሟ እየተመለሰች ነው” ካሉ በኋላ ነገር ግን አሜሪካ ወደፊት የዴሞክራሲ ደንቃራ ተደግኖባታል፤ አልፎም ውርጃ ማካሄድ የሚፈልጉ ጫና እያደረባቸው ነው ብለዋል።

“አሜሪካዊያን ድምፃቸውን ለኛ በመስጠት ወደፊት እንድንራመድ ይፈቅዱልናል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል ባይደን ባወጡት መግለጫ።

ተንታኞች ባይደን ተቀማጭ ፕሬዝደንት መሆናቸው ከሌሎች ዕጩዎች የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው አድርጓል ይላሉ።

ባይደን ዴሞክራት ፓርቲውን ወክሎ በዋናው ምርጫ ለመሳተፍ በሚደረገው ቅድመ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ፉክክር አልገጠማቸውም።

ምንም እንኳ ዕድሜያቸው መግፋቱ ፕሬዝደንት ሆነው ለመቀጠል እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል የሚል ስጋት ከመራጮች ዘንድ ቢኖርም ፓርቲያቸው በሳቸው ላይ ያለውን እምነት በድጋፍ ገልጧል።

በሌላ በኩል የ77 ዓመቱ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ የሚያስችላቸውን ድምፅ በቅድመ ምጫው ማግኘት ችለዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ሆነው ሀገሪቱን ለመምራት እየተሟገቱ ያሉት ትራምፕ ጠበቅ ያለ የስደተኞች ሕግ በማውጣት “ድንበር እንዘጋለን”፤ አልፎም “ስደተኞችን እናባራለን” በሚሉ መፈክሮች ብቅ ብለዋል።

የዩክሬን ጦርነት መቋጨት እና “ቅድሚያ ለአሜሪካ” የሚሉት ሐሳቦች ደግሞ እንደ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይዘው ተከስተዋል።

ምንም እንኳ ከአሜሪካዊያን የተሰበሰበው ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ከሁለቱ ዕጩዎች መምረጥ አንፈልግም የሚል ቢሆንም ሁለቱ የዕድሜ ባለጠጋዎች ቅድመ ምርጫውን ያለተፎካካሪ በማሸነፋቸው በሚቀጥለው ምርጫ ለመጋፈጥ ተዘጋጅተዋል።

የአሜሪካ ቅድመ ምርጫ በየግዛቱ የሚካሄድ ሲሆን ፓርቲዎች ብዙ የፓርቲ ተወካይ ለማግኘት የሚያደርጉት ምርጫ ነው።

ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች ቅድመ ምርጫውን የሚያደርጉበት መንገድ ይለያይ እንጂ ሂደቱ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው።

ሪፐብሊካን ዕጩ በቅድመ ምርጫው 1215 ተወካዮችን ማግኘት አለበት። የዴሞክራት ዕጩ ደግሞ በፕሬዝደንታዊው ምርጫ ለመሳተፍ 1968 ተወካዮችን መሰብሰብ አለበት።

ከማክሰኞው ቅድመ ምርጫ በፊት የባይደን እና ትራምፕ ተፎካካሪዎች ከምርጫው ራሳቸውን በማግለላቸው የሁለቱ ግለሰቦች መመረጥ ብዙም አስገራሚ ዜና አልነበረም።

የትራምፕ የመጨረሻው ተፎካካሪ የነበሩት በተባበሩት መንግሥት የቀድሞው የአሜሪካ አምባሰደር የነበሩት ኒኪ ሄሊ በ14 ግዛቶች ከተሸነፉ በኋላ ራሳቸውን አግልለዋል።

አንዳንድ ግዛቶች አሁንም ቅድመ ምርጫውን ያላጠናቀቁ ቢሆንም ባይደን እና ትራምፕ የሚበቃቸውን ድምፅ አግኝተዋል።