March 12, 2024 – Konjit Sitotaw 

ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት በሚሞክሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሞት አደጋ ተባብሷል

ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት በሚሞክሩ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ላይ የሚደርሰው የሞት አደጋ እየተባባሰ መምጣቱን ከኬኒያ እና ታንዛኒያ እሥር ቤቶች ተለቀው ዛሬ በኢትዮጵያ ሞያሌ በኩል ወደ አገራቸው የገቡ ተመላሽ የአይን እማኝ ፍልሰተኞች መመልከታቸውን ዶይቼ ቬለ ዘግቧል።

በስደት ጉዞና በእሥር ቆይታቸው አስቸጋሪ ፈተናዎችን ማለፋቸውን የተናጉሩት ከፍልሰት ተመላሾቹ ” ዜጎች በጉዞ ላይና በበረሃና በእሥር ቤቶች ለሞት ሲዳረጉ በርካቶች ሕይወታቸው ሲያጡ ተመልክተናል። አብዛኞቹ የሞት አደጋ የሚጋጥማቸው በጉዞ ላይ ሲሆን በበረሃ፣ እስር ቤቶች ውስጥ በረሃብና በበሽታ የሞቱ ሰዎችንም አይተናል” ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ነዋሪ የሆኑት ወጣት ታደሰ ተመስገን እና ብሩክ ግርማ  በሞያሌ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ከዓመት በፊት ጉዞ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ እነ ታደሰ የተስፋይቱ ምድር ብለው ጉዞ የጀመሩባት ደቡብ አፍሪካ እንዳሰቡት መድረስ አልቻሉም። ይልቁንም በተሽከርካሪ ኮንቴይነር ውስጥ ተደብቀው ከኬኒያ ሞምባሳ ወደ ታንዛኒያ በበረሃ በመጓዝ ላይ ሳሉ  አየር ለመውሰድ በወጡበት በአገሬው ፖሊሶች ተይዘው ለእሥር መዳረጋቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ሞያሌ በኩል ዛሬ ወደ አገራቸው የተመለሱት ከሦስት መቶ በላይ ፍልሰተኞች ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት በእሥር መቆየታቸው ሲገለፅ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት የሃድያና የከምባታ ዞኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው ፍልሰት በመነሻነት የሚጠቀሱ መሆኑም ነው የተገለፀው።