March 12, 2024 – Konjit Sitotaw 

ኦነግ፣ መንግሥት ያቋቋመው ሚስጢራዊ የጸጥታ ኮሚቴ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚፈጽማቸው ግድያዎች እንዲቆሙ ሕዝቡ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የጸጥታ ኮሚቴው አባላት ለፈጸሟቸው ተግባራት ተጠያቂ እንዲኾኑ እነዚኹ አካላት ጥረታቸውን እንዲቀጥሉም ኦነግ ጥሪ አድርጓል። ኦነግ ጨምሮም፣ በአብዛኞቹ የክልሉ ዞኖች ከፍርድ ውጭ የኾኑ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስሮች፣ ስቃይ እና ምዝበራ እንደቀጠለ ነው ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተካተቱበት ሚስጢራዊ የጸጥታ ኮሚቴ የሚያስፈጽማቸውን ከሕግ ውጭ የኾኑ ግድያዎች ሮይተርስ በጥልቅ ምርመራ በቅርቡ አጋልጧል ያለው ኦነግ፣ የሚስጢራዊው ኮሚቴ መዋቅር እስከ ዞን፣ ወረዳ፣ ከተማ እና ቀበሌ አስተዳደሮች ድረስ የተዘረጋ መኾኑን ጠቅሷል።