March 13, 2024 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ሐሙስ መጋቢት 5/2016 ዓ.ም. በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑትን የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው።

አቶ ክርስቲያን ታደለ ፓርላማ የገቡት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ምርጫ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ን ወክለው ተወዳድረው ነው።

አቶ ክርስቲያን ፓርላማ ከገቡ በኋላ በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነዋል።

ሆኖም በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ ባለፈው ሐምሌ ወር በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ላላፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ ይገኛሉ።

አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከሰባት ወራት በኋላ ነው ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን ነገ የሚያነሳው።

ቢቢሲ የተመለከተው እና ለፓርላማ አባላት የተላከው አጀንዳ የአንድ የምክር ቤት ያለመከሰስ መብት እንደሚነሳ ያትታል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የቢቢሲ ምንጮች ያለመከሰስ መብታቸው የሚነሳው የምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአቶ ክርስቲያን በተጨማሪ ሌላኛው የአብን ተወካይ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔም ባለፈው ጥር መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ሆኖም ግን ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት ያለመከሰስ መብት የሚያነሳው የአንድ የምክር ቤት አባልን ብቻ ነው።

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት፤ “ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።

ነገ የአቶ ክርስቲያን ያለመከሰስ መብት የአባላትን አብላጫ ድምጽ አግኝቶ የሚነሳ ከሆነ በሥራ ላይ ባለው ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳ ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ይሆናሉ።

ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ዶ/ር ጫላ ዋላ ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሦስት የክልል ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት መነሳቱ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት የአማራ ክልል ምክር ቤት የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት ባለፈው የካቲት ወር ላይ አንስቷል። የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ደግሞ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ የአቶ ታዬ ደንደኣን ያለመከሰስ መብት ያነሳው የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ነበር።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገርም ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው በተመሳሳይ ወቅት ነበር።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ሦስቱ የክልል ምክር ቤት አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉት ያለመከሰስ መብታቸው ከመነሳቱ ከወራት ቀደም ብሎ መሆኑ ይታወቃል።