ሦስቱ የኦርቶክስ መነኮሳት
የምስሉ መግለጫ,ሦስቱ የኦርቶክስ መነኮሳት በስለት ተወግተው ስለመገደላቸው ምልክት ማግኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።

13 መጋቢት 2024, 13:17 EAT

ሦስት የግብፅ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መነኮሳት በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ገዳም ውስጥ “ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ” መገደላቸው ተገለጸ።

አባ ታክላ ሙሳ፣ አባ ሚናህ አቫ ማርከስ እና አባ ዮስቶስ አቫ ማርከስ ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 3/2016 ዓ.ም. መገደላቸውን የግብፅ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ የደቡብ አፍሪካ አገረ ስብከት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከሦስቱ መነኮሳት ግድያ ጋር በተያያዘ አንድ የግብፅ ዜግነት ያለው የቤተክስቲያኗ አባል በቁጥጥር ስር መዋሉም ተገልጿል።

የመነኮሳቱ ግድያ በደቡብ አፍሪካ እና በመላው የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።

“ሐዘናችንን እና ህመማችንን የሚገልጽ ቃል አናገኝም። ይሁን እንጂ በአባታችን በአብርሃም፣ ይስሐቅ እና ያዕቆ እቅፍ በአጸደ ገነት እንደሚኖሩ ስናሰብ እረፍት ይሰጠናል” ይላል ከደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የወጣው መግለጫ።

በለንደን የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አንጄሎስ የመነኮሳቱ ግድያን “አሳዛኝ እና አስደንጋጭ” ሲሉ ገልጸውታል።

ሦስቱ የግብፅ መነኮሳት ከደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ኩሊናን በተሰኘች አነስተኛ ከተማ በሚገኝ ገዳም ውስጥ ነው የተገደሉት።

የግዛቱ የፖሊስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዲማካትሶ ቬቭሁሁለዊ ሦስቱ ግለሰቦች በስለት ተወግተው መገደላቸውን የሚያሳይ ምልክት በአስክሬናቸው ላይ ይታያል ስለማለታቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከዚህ ጥቃት ተርፏል የተባለ ግለሰብ በብረት ከተመታ በኋላ አምልጦ መደበቅ በመቻሉ ሕይወቱን ስለማትረፉ ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል ተብሏል።

ፖሊስ ለግድያው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማጣራት ላይ እንደሚገኝ የግዛቷ የፖሊስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ቬቭሁሁለዊ ጨምረው ተናግረዋል።

“ጥቃት አድራሾቹ ወንጀል ከተፈጸመበት ቦታ ምንም ዓይነት ዋጋ ያላቸውን ንብረቶች ሳይወስዱ ሄደዋል” በማለት ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ በዓለማችን ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ነች።