የቦይንግን ምስጢር በማጋለጥ የሚታወቀው ጆን ባርኔት
የምስሉ መግለጫ,የቦይንግን ምስጢር በማጋለጥ የሚታወቀው ጆን ባርኔት

ከ 5 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ግዙፉ የዘመናዊ አውሮፕላኖች አምራች ኩባንያ ድሪምላይነር አውሮፕላኖች የነበረባቸውን ጉድለቶች በተመለከተ ምሥጢር በማጋለጥ የሚታወቀው ጆን ባርኔት ከሰሞኑ መኪናው ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።

የቀድሞ የቦይንግ ሠራተኛ የነበረው ጆን በዓለም ላይ ግዙፍ የሆነውን የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ሳይፈራ በመጋፈጡ ይፋ ባደረገው መረጃ “ደፋር፣ ታማኝ እና ለመርሁ ሟች ነው” ሲሉ ጠበቆቹ አሟካሽተውታል።

ባለሥልጣናት ባርኔት ሕይወቱን ያጣው ራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ነው ቢሉም ምርመራ መክፈታቸውን አስታውቀዋል።

ጆን ባርኔት በአሜሪካው ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ውስጥ ለሰላሳ ዓመታት አገልግሏል።

ከሦስት አስርት ዓመታት አገልግሎት በኋላም ጡረታ የወጣው በአውሮፓውያኑ 2017 ነው።

ባርኔት ህይወቱ ከማለፉ በፊትም በኩባንያው ላይ በቀረበበት ክስ ላይ ማስረጃ እየሰጠ ነበር።

ሁለቱ ጠበቆቹ የጆን ባርኔት አሟሟት ላይ ፖሊስ ሙሉ ምርመራ እንዲከፍት ጠይቀዋል።

“ጆን በኩባንያው ላይ ባጋለጠው ምሥጢር ላይ የምስክርነት ቃለ መሐላውን በመስጠት፣ የፍርድ ሂደቱም ወደ መጨረሻው ተቃርቦ ነበር” ሲሉ ሮበርት ቱርኪዊትዝ እና ብሪያን ኖውልስ በሰጡት መግለጫ አትተዋል።

“በጣም ጥሩ መንፈስ ውስጥ ነው የነበረው። ይህንንም የሕይወቱን ምዕራፍ ወደ ኋላ ትቶ ቀጣይ ሕይወቱን ለመምራት በጉጉት እየተጠባበቀ ነበር። የራሱን ሕይወት እንደሚያጠፋ ምንም ምልክት አላየንም። ይህንን ማመን አይቻልም” ብለዋል ጠበቆቹ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ።

በደቡብ ካሮላይና፣ ቻርልስተን ያሉ ባለሥልጣናትም ስለ ጆን አሟሟት የበለጠ መረጃ እንዲሰጡ በመጠየቅም “ሁሉንም ዝርዝር መረጃዎች ምንም ሳያስቀሩ እንዲሰጡ” ጠይቀዋል።

ሁለቱ ጠበቆች ባርኔት ስለ ቤተሰቦቹ፣ ስለ ጓደኞቹ እንዲሁም ለቦይንግ ከፓይለቶቹ እስከ ደንበኞቹ ድረስ “በጣም የሚጨነቅ ሰው ነበር” ይላሉ።

ባርኔት ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በጤና ምክንያት በጡረታ እስከተገለለበት ጊዜ ድረስ በሰሜን ቻርለስተን በሚገኘው የቦይንግ የ787 ድሪምላይነር የአውሮፕላን ማምረቻ ውስጥ የጥራት ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግሏል።

እነዚህ አውሮፕላኖች ኩባንያው በዘመናዊ መንገድ የሚያመርታቸው እና ለረጅም ርቀት በረራዎች የሚውሉ ናቸው።

በዚያ የኃላፊነት ድርሻውም “ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ከባድ የሆኑ የደኅንነት ችግሮች እንዳለባቸው በመረዳቱ ነበር ምሥጢሩን ያጋለጠው። እናም በአጸፋውም የከፋ የሥራ ሁኔታ ጠበቀው” ብለዋል ጠበቆቹ።

ጡረታ ከወጣ በኋላም ከኩባንያው ጋር ለረጅም ጊዜ በፍርድ ቤት ሂደት እሰጣ እገባ ውስጥ ገብቷል።

ባጋለጠው የደኅንነት ስጋት ምክንያት ቦይንግ ስሜን አጠልሽቷል፣ ማንነቴን አንቋሿል እንዲሁም ሥራዬንም አደናቅፏል ሲል ከሷል። በተጨማሪም ይፋ የወጡትን መረጃዎችንም አስተባብሏል።

በሞተበት ወቅትም ባርኔት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ምስክርነቶችን ለመስጠት በቻርልስተን ተገኝቶ ነበር።

ባለፈው ሳምንት በራሱ ጠበቆች የማመሳከሪያ ጥያቄዎች ከመቅረቡ በፊትም የቦይንግ ጠበቆች መደበኛ የቃለ መሐላ ምስክርነት እንዲሰጥ አድርገውት ነበር። ባለፈው ሳምንት ቅሜ ዕለትም ተጨማሪ ጥያቄዎች እንዲቀርቡለት ቀጠሮ ተይዞም ነበር።

የቦይንግ ኩባንያ

ነገር ግን በቀጠሮው ቀን ባለመቅረቡ ምን እንዳጋጠመው ለማወቅ ወዳረፈበት ሆቴል ሰው ተልኮ በተደረገ ማጣራት ባርኔት በሆቴሉ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በመኪናው ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።

ለረዥም ዓመታት ያገለገለበት መሥሪያ ቤቱ ቦይንግ፣ የማይወጣው ጭንቀት ውስጥ ስላስገባው ጤንነቱ እያሽቆለቆለ እንደነበር ወንድሙ ለአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

“በቦይንግ ውስጥ በተፈጠረበት የከፋ የሥራ ሁኔታ ምክንያት በከፍተኛ ጭንቀት እና መረበሽ ይሰቃይ ነበር። ይህም ለሞት እንደዳረገው እናምናለን” ሲል ወንድሙ ሮድኒ ባርኔት ተናግሯል።

ወንድምየው አክሎም ባርኔት “የፍርድ ሂደቱን መጨረሻ ለማየት በጉገት ይጠባበቅ ነበር፤ ይህም ቦይንግ የሥራ ባህሉን እንዲቀይር ያስገድደዋል የሚል ተስፋ ነበረው” ብሏል።

የጥራት ተቆጣጣሪው በአሜሪካዊው ግዙፍ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ላይ ያሉ ስጋቶችን በማንሳት ይታወቃል።

ባርኔት በፋብሪካው ውስጥ ሠራተኞች በከፋ ጫና ውስጥ በመግባታቸው ጥራታቸው የወረዱ ቁሳቁሶችን በአውሮፕላኖቹ ላይ እየገጠሙ መሆኑንም በአውሮፓውያኑ 2019 ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ባርኔት አክሎም ለቢቢሲ እንደተናገረው ሠራተኞች መመሪያዎችን እና አሠራሮችን ባለመከታተላቸው ጉድለት ያለባቸው አካላት የት እንደገቡ ሳይታወቁ ጠፍተዋል ብሏል።

በተለይም በአውሮፕላኖቹ ላይ የሚገጠሙ የኦክስጅን መሳሪያዎች ላይ የከፋ ችግር መኖሩን ጠቁሞ፣ በድንገተኛ አደጋ ወቅትም ከአራቱ የኦክስጅን ጭምብሎች አንዱ ላይሠራ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።

በተለይም በደቡብ ካሮላይና ባለው ፋብሪካ መሥራት ከጀመረ በኋላ አዳዲስ አውሮፕላኖች እንዲመረቱ በነበረው ጫና መገጣጣሙ በተጣደፈ ሂደት ይከናወን እንደነበር ገልጾ፤ ይህም ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ እንደጣለው አስረድቷል። ቦይንግ ይህንን ምስክርነት አልተቀበለውም።

ባርኔት የሚታዩ የደኅንነት ስጋቶችን ለአስተዳዳሪዎች ማሳወቁን ቢናገርም ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም ብሏል።

ቦይንግ ይህንንም የባርኔት አስተያየት አልተቀበለውም። ነገር ግን የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አካል የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር በአውሮፓውያኑ 2017 ባደረገው ግምገማ ባርኔት ያነሳቸውን አንዳንድ ስጋቶች አረጋግጧል።

በፋብሪካው ውስጥ ቢያንስ 53 “ደረጃቸው ያልተረጋገጡ [የአውሮፕላኖች] አካላት” ያሉበት ቦታ እንደማይታወቅ እና መጥፋታቸው ተረጋግጧል።

በኦክስጂን መሳሪያዎች ዙሪያ ኩባንያው በአውሮፓውያኑ 2017 “ከአቅራቢው የተቀበላቸው አንዳንድ የኦክስጂን መሳሪያዎችን በትክክል መዘርጋት አልተቻለም” ብሏል። ነገር ግን እነዚህን የኦክስጂን መሳሪያዎች በአውሮፕላኖቹ ላይ መገጠማቸውን በተመለከተ ውድቅ አድርጓል።

የባርኔት ሞት የተሰማው አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ እና ዋነኛ አቅራቢው ኤሮ ሲስተምስ ኩባንያዎች የምርት ደረጃቸው ላይ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ባለበት ወቅት ነው።

ባለፈው ሳምንት የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር በኩባንያው ላይ ለስድስት ሳምንታት ባደረገው ኦዲት “ኩባንያው የምርት ጥራት ቁጥጥር መስፈርቶችን ያላሟለበትን በርካታ ሁኔታዎችን ማግኘቱን” ገልጿል።