ጋይ ፊሊፕ [ግራ]፤ ባርቢኪው [መሐል]፤ ኢዞ [ቀኝ]
የምስሉ መግለጫ,ጋይ ፊሊፕ፣ ባርቢኪው፣ ኢዞ

ከ 5 ሰአት በፊት

ጠመንጃውን እየነቀነቀ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት የሚወደው የቀድሞው የፖሊስ መኮንን፣ በሜሪካ ውስጥ ታስሮ የቀየው ታራሚ እና የራፕ ሙዚቃ ክሊፖች ላይ የሚታየው ወጣቱ ወንበዴ ሄይቲ ውስጥ ለሥልጣን ፉክክር ላይ ናቸው።

እነዚህ በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-አው-ፕሪንስ ለተነሳው ነውጥ ተጠያቂ ናቸው የሚባሉትን ዋነኞቹ ሁለት የወሮበላ ቡድኖችን የሚመሩ ናቸው።

ለወራት በወሮበሎች ጥቃት ሥር የቆየችው ሄይቲ፣ ባለፉት ሳምንታት ነውጡ ተባብሶ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ለመልቀቅ ተስማምተዋል።

እዚህ ላይ በአሜሪካ እስር ላይ የነበረ፣ ዘንድሮ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን ያለመ የቀድሞው የወሮበሎች ቡድን መሪ ሲጨመርበት ምን ያህል ሄይቲ ጭንቀት ላይ እንዳለች መረዳት አይከብድም።

የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ጥረት ላይ የምትገኘው ሄይቲ ቀጣዩ መሪ መሆን በሚሹ ወንበዴዎች ልቧ ጠፍቷል።

ለመሆኑ ለሥልጣን እየተፎካከሩ ያሉት ወንበዴዎች የትኞቹ ናቸው?

ጂሚ ሼሪዢዬር – ባርቢኪው

የ47 ዓመቱ የቀድሞው የፖሊስ መኮንን ሄይቲ ውስጥ ከሚገኙ የወንጀለኛ ቡድን መሪዎች እጅግ አደገኛው ላይሆን ይችላል።

ነገር ግን ጂሚ ሼሪዢዬር አሊያም ባርቢኪው በቅርብ ዓመታት ብቅ ብለው ጡንቻ ካወጡ ወንበዴዎች መካከል አንደኛው ነው።

በሚታወቅበት ጥይት መከላከያ ጃኬቱ እና በጠባቂዎቹ ታጅቦ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠት የሚወደው ባርቢኪው፣ ጂ9 የተሰኘው የወሮበላ ቡድኖች ጥምረት መሪ ነው።

ባርቢኪው ጠቅላይ ሚኒስትር አሪዬል ሄንሪን በግላጭ በመቃወም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ ሲጠይቅ ቆይቷል።

የጂ9 መሪው ባርቢኪው ራሱን ለተራው ማኅበረሰብ እንደሚታገል፤ ሥልጣን ላይ ያሉ ኃያላንን የሚጠየፍ አድርጎ ነው የሚቆጥረው።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2018 በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጅምላ ጭፍጨፋ በማቀናበር ከመከሰሱ በላይ በ2021 ለተከሰተው የነዳጅ እጥረትም ተጠያቂ ነው።

የጂ9 አባላት የመጠጥ እና ምግብት አቅራቢዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት የሄይቲን ደሀ ማኅበረሰብ ከደቆሱ ምክንያቶች አንዱ ነው።

ወንጀለኛ ቡድኖቹ ነዳጅ እንዳይተላለፍ ማገዳቸውን ተከትሎ ሆስፒታሎች ጄኔሬተር የሚያንቀሳቅሱበት ኃይል አጥተው ከርመዋል።

“ባርቢኪው ፍትሕ የሰፈነበት እና እኩልነት ያለበት ማኅበረሰብ ይፈጠር ይላል፤ የሚገርመው ነገር ግን ሕዝቡ እዚህ ማጥ ውስጥ የገባው በዋና ከተማዋ እና በሌሎች ቦታዎች ያሉ ታጣቂዎች በፈጠሩት ግርግር ምክንያት ነው” ይላሉ ማይክል ዴይበርት።

ባርቢኪው በዋና ከተማዋ ያሉ አስፈሪ የሚባሉ ወንጀለኛ ቡድኖችን በማጣመር ‘ቪቭ አንሳንም’ [አብሮ መኖር] የተባለ ኅብረት ፈጥሪያለሁ ይላል።

ባርቢኪው

ይህ እውነት ስለመሆኑ ማጣራት ግን ቀላል አይደለም። ነገር ግን እስካሁን የትኛውም የወሮበሎች ቡድን መሪ ወጥቶ ሐሰት ነው አላለም።

የትኛውም ኅብረት ዕድሜው በጣም አጭር መሆኑን በሄይቲ ጉዳይ ብዙ ምርምር ያደረጉት ዴይበርት ይገልጻሉ።

“አነዚህ ቡድኖች ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ይጣላሉ” ይላሉ ጋዜጠኛው እና የሊዝበን ኢንስቲትዩት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው።

ባርቢኪው ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ወደ ሄይቲ የሚመለሱ ከሆነ በአገሪቱ “የእርስ በርስ ጦርነት” ይነሳል ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

የጂ9 መሪው ባርቢኪው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽግግር ምክር ቤት ሲቋቋም ሥልጣኔን እለቃለሁ ካሉ በኋላ በይፋ የሰጠው አስተያየት የለም።

ቢሆንም ከዚህ ቀደም የሄይቲ ዜጎች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ይወስናሉ ሲል አስተያየት መስጠቱ ይታወሳል። ይህ ማለት ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ወታደሮች ወደ ሄይቲ ሊሰማሩ መሆኑ ለእሱ መልካም ዜና አይደለም ማለት ነው።

ባርቢኪው በዋና ከተማዋ የሚገኘውን የባሕር በር እና የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር መቆጣጠሩ ጉልበት ሰጥቶታል።

ዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል ወደ ሄይቲ የሚሰማራ ከሆነ የባርቢኪው ተፅዕኖ እያነሰ ሊመጣ እንደሚችል ተንታኞች ይስማማሉ።

ተንታኞች አክለው እንደሚሉት ባርቢኪው ሄይቲ ውስጥ ከሚገኙ የወንጀለኞች ቡድን መሪዎች ይህን ያህል ጉልበት ያለው አይደለም፤ ነገር ግን ወጥቶ መገናኛ ብዙኃን ላይ ወጥቶ በመናገር ዝናን ተጎናፅፏል።

“አብዛኞቹ የወሮበላ ቡድኖች በፍፁም መገናኛ ብዙኃን ላይ ወጥተው መታየት አይፈልጉም” ይላሉ ዴይበርት።

ኢዞ

ጆንሰን አንድሬ – ኢዞ

የ26 ዓመቱ ጆንሰን አንድሬ አሊያም ኢዞ ከባርቢኪው በላይ ጉልበተኛ እንደሆነ ይታመናል።

ኢዞ ከቀድሞው የፖሊስ መኮንን ባርበኪው የሚለየው በሚመራው የወሮበላ ቡድን ውስጥ ከታች ተነስቶ ‘ቪላይ ዲ ዳይ’ የተሰኘው ቡድን መሪ ለመሆን መቻሉ ነው።

ሁለቱ የሚያመሳስላቸው ነገር መታየት መውደዳቸው ነው። ነገር ግን ኢዞ በማኅበራዊ ሚድያ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮች ከማሰራጨት ይልቅ የሙዚቃ ክሊፕ መልቀቅ ይቀናዋል።

ወጣቱ ወንበዴ በርካታ የራፕ ሙዚቃዎችን የለለቀ ሲሆን፣ ዩቲዩብ ላይ 100 ሺህ ተከታዮች በማፍራቱ ከድርጅቱ ሽልማት ማግኘት ችሏል።

በሙዚቃ ቪድዮዎቹ ከሚታየው ማንነቱ ጀርባ ግን በመድፈር፣ አፈና፣ ዕፅ እና መሣሪያ ዝውውር በተባበሩት መንግሥታት የሚወቀስ ግለሰብ ነው።

ወጣቱ የወሮበላ ቡድን መሪ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ እክል በመፍጠርም ወቀሳ ይደርስበታል።

የሄይቲን የወሮበላ ቡድኖችን ያጠኑ ተንታኞች ኢዞ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በመዲናዋ ፖርት-አው-ፕሪንስ የሚገኙ የባሕር ኃይል መተላፊያዎችን መቆጣጠሩ ነው ይላሉ።

ይህ ማለት ከሌሎች ቡድኖች ቀድሞ የጦር መሣሪያ ለማመላለስ ዕድሉን ይሰጠዋል ማለት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ኢዞ የአገሪቱን “ደካማ የፀጥታ ሁኔታ” ተጠቅሞ ከደቡብ አሜሪካ ቀጥታ ከሚገባ የዕፅ ንግድ ገንዘብም እያተረፈ ነው።

ኢዞ ከዋና ከተማዋ ባሻገር 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሚሬባላይ ከተማን ለመቆጣጠር ባደረገው ሙከራ 5 አባላቱን ያጣ ሲሆን፣ 30 ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል።

ጋይ ፊሊፕ

ጋይ ፊሊፕ

ሄይቲን ከሚያስጨንቁ የወሮበላ ቡድኖች መሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ጋይ ፊሊፕ ልክ እንደ ባርቢኪው የቀድሞው ሥራው የፖሊስ መኮንንነት ነበር።

የ56 ዓመቱ ፊሊፕ በአውሮፓውያኑ 2004 ፕሬዝዳንት በርትራንድ አሪስቲድን ከሥልጣናቸው ለመገልበጥ መፈንቅለ መንግሥት ካካሄዱ ሰዎች መካከል ነው።

በ2016 (እአአ) በሄይቲ የሕዝብ ተወካይ ሆኖ ተመርጧል። ነገር ግን ቃለ-መሐላ ሊፈፅም ቀናት ሲቀሩት ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ተከሶ ወደ አሜሪካ ለእስር እንዲሄድ ተደረገ።

ፊሊፕ በወቅቱ ቃለ-መሐላ ፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ያለመከሰስ መብት ይኖረው ነበር።

ነባር የፖሊስ መኮንን ሳለ አደገኛ ዕፆች ወደ አሜሪካ እንዲጓጓዙ ክፍያ መቀበሉንም አምኗል።

የቀድሞው አማፂ ባለፈው ኅዳር ነበር ከአሜሪካ እስሩን አጠናቆ ወደ ሄይቲ የተመለሰው። ማይክል ዴይበርት፤ ይህንን ሁኔታ “ነዳጅ ላይ እሣት እንደመጫር ነው” ይለዋል።

ፊሊፕ ወደ ሄይቲ ተመልሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ላይ “አመፅ” የሚቀሰቅስ ቪድዮ ቀርፆ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ለማሰራጨት ጊዜ አልወሰደበትም።

ሰውዬው ቀጣዩ የሄይቲ ፕሬዝዳንት ለመሆን ያለውን ምኞት በግልፅ ነው የሚናገረው።

ምናልባት አሜሪካ ውስጥ እሥር ላይ መቆየቱ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሆኖ እንዳይመረጥ እክል ይሆንበት እንደሁ የተጠየቀው ፊሊፕ “ማንዴላ እስር ቤት ነበር። ኡጎ ቻቬዝ እሥር ቤት ነበር። ሉላ ዳ ሲልቫ እሥር ቤት ነበር። ስለዚህ ሕዝቤ ካመነብኝ መሪ የማልሆንበት ምክንያት የለም። ወሳኙ ሕዝቡ እንጂ ማንም አይደለም” ይላል።

ጋይ ፊሊፕ እና ሌሎች የወሮበላ ቡድን መሪዎች ሄይቲን ለመምራት ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

“በዚህ ግርግር መሐል የተረሳው የሄይቲ ሕዝብ ነው” ይላል ዴይበርት።

ከአገሪቱ 11 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 5 ሚሊዮን ገደማው የሚሆኑት የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ሰብዓዊ እርዳታው በወንበዴዎች ግርግር መካከል የተረሳ ይመስላል።