የእርዳታ ማዕከሉ ሰራተኛ

ከ 4 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ራፋህ የሚገኘው የዕርዳታ ማዕከሉ ላይ ጥቃት እንዳደረሰበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

በዚህም ጥቃት አንድ የማዕከሉ ሰራተኛ መገደሉን እንዲሁም 22 ሰዎች መቁሰላቸውን የተመድ የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ አክሎ አስታውቋል።

በተመድ ተቋማት ላይ የሚደርሰው ጥቃት “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋትን ግልጽ በሆነ መንገድ በጣሰ መልኩ” ተደጋጋሚ እየሆነ እንደመጣ የኤጀንሲው ኃላፊ ፊሊፕ ላዛራኒ ገልጸዋል።

በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ እስራኤል በማዕከሉ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት አምስት ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ አነጣጥሮ በፈጸመው ጥቃት የሐማስ አዛዥን መግደሉን ተናግሯል።

ግለሰቡ መሀመድ አቡ ሃስና እንደሚባልና በራፋህ አካባቢም የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ውስጥ ድጋፍ ሰጭ ነው ብሏል።

የጤና ሚኒስቴሩ በጥቃቱ ከተገደሉት ውስጥ መሀመድ አቡ ሃስና የሚል ስምም ሰፍሯል።

እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ እየፈጸመችው ያለችውን መጠነ ሰፊ የምድር ጥቃትም የሸሹ 1.5 ሚሊዮን የሚገመቱ ፍልስጤማውያን ዜጎች የራፋህን ግዛት አጨናንቀዋታል።

እስራኤል በራፋህ ግዛት ላይ ልትፈጽመው ያሰበችው ጥቃት ፍልስጤማውያኑን ወደ ከፋ ገሃነም ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አስጠንቅቀዋል።

መስከረም መጨረሻ ላይ ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት ሰንዝሮ 1200 ሰዎች ሲገደሉ፤ 253 ታጋቾች ደግሞ ወደ ጋዛ ተወስደዋል።

እስራኤል ምላሽ ባለችው በተቀናጀ የማያባራ ጥቃት ከ31 ሺህ 200 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ከሚገኘው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ የተከሰተ ሲሆን፣ የረሃብ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት አሳስቧል። 300 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በምግብ እጦት እየተሰቃዩ እንደሆነም ተገልጿል።

እስራኤል ረቡዕ ዕለት በፈጸመችው ጥቃት የተመድን የዕርዳታ ማዕከሉን ምስራቃዊ ክፍል መምታቷ ተዘግቧል። የኤጀንሲው ቃለ አቀባይ ሰብለ ቱማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማዕከሉ ምግብ እና መሰረታዊ ቁሳቁሶችን የያዘ ሲሆን እስከ 60 ሰራተኞችም አሉ ብለዋል።