ጸረ እስላም ፖለቲከኛ ገርት ዋይልደርስ

ከ 2 ሰአት በፊት

ፓርቲያቸው ባለፈው ዓመት ኔዘርላንድስ በተደረገው ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ያሸነፈው ጸረ እስላም ፖለቲከኛ ጌርት ዋይልደርስ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩነት ራሳቸውን አገለሉ።

“ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የምችለው በጥምረቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ፓርቲዎች የሚደግፉት ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ሊሆን አይችልም” ሲሉም ፖለቲከኛው በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ፍሪደም (ፒቪቪ) የተሰኘው ፓርቲያቸው ባለፈው ዓመት በአገሪቱ በተደረገው ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፍ ችሏል።

ነገር ግን መንግሥት ለማቋቋም ጥምረት መመስረት የሚያስፈልግ ሲሆን ለዚህም ሌሎች ፓርቲዎች ተሳትፎ ያስፈልጋል።

አዲሱ መንግሥት ምን ዓይነት ቅርጽ ይኑረው በሚለው ዙሪያ ከሶስት ፓርቲዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

ማክሰኞ የተጠናቀቀውን የዚህ ዙር ድርድር የሚመሩት ተደራዳሪም ሃሙስ ሪፖርቱን ለፓርላማ እንዲያጋሩም ይጠበቃል።

“የቀኝ አክራሪ ካቢኔ እንዲኖር እፈልጋለሁ። የጥገኝነት እና እና ስደተኞችን ጥያቄ የማይቀበል እና ኔዘርላንድስን በቁጥር አንድ የሚያስቀምጥ። ለአገሬ እና ለመረጠኝ ህዝብ ያለኝ ፍቅር ከራሴ አቋም በበለጠ መሰረታዊ እና አስፈላጊ ነው” ሲሉም ፖለቲከኛው ረቡዕ አመሻሽ ላይ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

የ60 ዓመቱ ፖለቲከኛ ለወራትም ያህል ቪቪዲ፣ ኒው ሶሻል ኮንትራክት እና ቢቢቢ ፋርመርስ ከተሰኙት ሶስት ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግሥት የሚመሰርቱበትንም ሁኔታ ለወራት ሲወያዩም ቆይተዋል።

የሶስቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ወደፊት ሁኔታዎች ለመግፋት የሚፈቅዱበት ብቸኛው መንገድ አራቱም የፓርቲ መሪዎች በመንግስት ስልጣን ላይ ካልተቀመጡ ብቻ ነው በሚለው መጽናታቸውን የደች የህዝብ ብሮድካስቲንግ ኤኦኤስ ዘግቧል።

ሁሉንም የሚያስማማ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ስለመደረሱ የተገለጸ ነገር የለም።

በጉዳዩ ላይ የፓርላማ ክርክርም ዛሬ ሐሙስ ይጠበቃል።

ጸረ-እስላም የሆኑት ፖለቲከኛ ፓርቲያቸው ፒቪቪ ማሸነፉ የኔዘርላንድን ፖለቲካ ያናጋ እንዲሁም በርካቶችን ያስደነገጠ ሆኗል። ኔዘርላንድስ ከአውሮፓ ህብረት መስራች አገራት አንዷ ከመሆኗም ጋር ተያይዞ ጦሱ ለነሱም ይተርፋል ተብሏል።