
ከ 3 ሰአት በፊት
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቲክቶክን በመላ ሀገሪቱ ለማገድ የሚያስችል ረቂቅ ይፋ አደረጉ።
ይህ ማለት የቻይናው ግዙፉ ኩባንያ ባይትዳንስ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያለውን የአክሲዮን ድርሻ መሸጥ አለበት፤ አሊያም መተግበሪያው አሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል ይደረጋል።
ምንም እንኳ ረቂቅ አዋጁ በአብላጫ ድምፅ በእንደራሴዎቹ ድጋፍ ቢያገኝም ሕግ ለመሆን ሴኔቱ ይሁንታ ሰጥቶ ፕሬዝደንቱ ሊፈርሙበት ይገባል።
ሕግ አውጭዎቹ ቻይና ቲክቶክን ተጠቅማ ጫና እያሳደረች ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።
ቲክቶክ የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 2012 ሲሆን ባለቤቱ ደግሞ ባይትዳንስ የተባለው የቻይና ኩባንያ ነው።
መቀመጫውን ቤዢንግ ያደረገው ኩባንያ ኬይመንድ አይላንድ በተባለችው የተመዘገበ ሆኖ በአውሮፓ እና አሜሪካ ቢሮዎች አሉት።
ረቂቅ አዋጁ የሴኔቱን ይሁንታ ካገኘ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጠረጴዛቸው ላይ እንደተቀመጠ ፈርመው ሊያፀድቁት ቃል ገብተዋል። ይህ ከሆነ በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው ውጥረት ሊባባስ እንደሚችል ግምት አለ።
ባይትዳንስ ድርሻውን ለመሸጥ ከቻይና ባለሥልጣናት ፈቃድ ማግኘት የሚገባው ቢሆንም ቤዢንግ ይህን ትቃወማለች።
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዌንቢን ቲክቶክን ለማገድ እየተደረገ ያለው ነገር “አደጋው ለአሜሪካ ነው” ብለዋል።
የቻይና ኩባንያዎች የሚሰበስቡትን መረጃ ለመንግሥት ማጋራት እንዳለባቸው የሀገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ ያስገድዳል።
ቲክቶክ 150 ሚሊዮን የሚሆኑ የአሜሪካ ደንበኞቹን መረጃ ለመጠበቅ እርምጃ መውሰዱን ይገልጣል። የቲክቶክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሹ ዚ ቺው ኩባንያቸው መረጃውን በደንብ እንደሚጠብቅና “ከውጭ ተፅዕኖ የፀዳ” እንዲሆን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ሥራ አስኪያጁ፤ ሪቂቅ አዋጁ ከፀደቀ “ሌሎች ጥቂት የማሕበራዊ ሚድያ ኩባንያዎች ኃይል ይኖራቸዋል”፤ በርካታ አሜሪካዊያንም ሥራ ያጣሉ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
- ዴንማርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶችን ለወታደራዊ ግዳጅ መመዝገብ ጀመረችከ 4 ሰአት በፊት
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነውከ 2 ሰአት በፊት
- የቦይንግን ምሥጢር በማጋለጡ በጀግንነት የሚወደሰው ግለሰብ ሞቶ መገኘት ያስከተለው ጥያቄከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው ጥር ዎል ስትሪት ጆርናል ያወጣው የምርመራ ዘገባ እንደሚጠቁመው አሜሪካ ባለው ቲክቶክ እና ቻይና ባለው ባይትዳንስ መካከል መረጃ ኦፊሴላዊ ባልሆነ መንገድ እየተሰራጨ ነው።
ለምሳሌ ቻይና ያሉ የባይትዳንስ ሠራተኞች የአንድ ጋዜጠኛን ግላዊ መረጃ አግኝተው የዜና ምንጩ/ ምንጯ ምን እንደሆነ ማጣራታቸው ተሰምቷል።
ሪብሊካኖች እና ዲሞክራት የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት ቲክቶክ በመላው አሜሪካ ይታገድ በሚለው ሐሳብ የተስማሙ ቢመስሉም አንዳንዶች እየተቃወሙት ነው።
የሴኔቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ፖለቲከኞች መሪ የሆኑት ቻክ ሹመር ኮሚቴያቸው አዲሱን ሪቂቅ እየመረመረ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ምርጫ ድጋሚ ወደ ዋይት ኃውስ ለመግባት ጥረት እያደረጉ ያሉ ዶናልድ ትራምፕ አዋጁን ተቃውመውታል።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ሥልጣን ላይ ሳሉ ቲክቶክን ለማገድ ተነስተው ነበር። ሐሳባቸውን የቀየሩ የባይትዳንስ አክሲዮን ባለቤት ከሆኑት ገንዘብ ለጋሹ ጄፍ ያስ ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው።
ሌላኛዋ ሪፐብሊካን ማርጆሪ ቴይለር ግሪን ሴኔቱ የአሜሪካን መረጃ ከውጭ ኃይሎች መጠበቅ በሚል ስም ሌሎችንም ኩባንያዎች ሊዘጋ ነው ይላሉ።
አንዳንድ ዲሞክራቶች ደግሞ ለምርጫ ቅስቀሳቸው በአብዛኛው ታዳጊዎችና ወጣቶች የሚጠቀሙት ቲክቶክ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ።
ቲክቶክ አሜሪካ ለሚገኙ ደንበኞቹ በላከው መልዕክት [ኖቲፊኬሽን] ተጠቃሚዎች ተወካዮቻቸውን በማሳመን መተግበሪያው እንዳይዘጋ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የተወሰኑ ሰዎች ረቡዕ ዕለት ዋይት ኃውስ ደጃፍ ተገኝተው ቲክቶክ እንዳይዘጋ ድምፃቸውን በሰልፍ ሲገልጡ ውለዋል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “ቲክቶክ የአሜሪካን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ እየወሰደ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ባታገኝም ቲክቶክን ማስፈራራቷን ቀጥላለች። እንዲህ ዓይነቱ ማስፈራራት ለማንም አይጠቅምም” ብለዋል።
ባይትዳንስ ያለውን የአክሲዮን ድርሻ ለመሸጥ ከቻይና መንግሥት ፈቃድ ቢያገኝ እንኳ ቲክቶክን ለመግዛት አቅም ያላቸው ኩባንያዎች አሉ ወይ የሚለው ሌላኛው ጥያቄ ነው።
ኩባንያው የቲክቶክ ዋጋ 268 ቢሊዮን ዶላር ነው ይላል። ይህ ዋጋ ከፍተኛ ቢመስልም የቴክኖሎጂ ልሂቃን ገዢዎች ሞልተዋል ይላሉ።
ቲክቶክ ከአሜሪካ ገበያው ብቻ ከማስታወቂያ በዓመት 8.66 ቢሊዮን ዶላር ያስገባል።