የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር
የምስሉ መግለጫ,የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር

14 መጋቢት 2024, 15:08 EAT

ደቡብ አፍሪካ በጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ ከእስራኤል ጦር ሠራዊት ጉን ተሰልፈው የሚዋጉ ዜጎቿ እስር እንደሚጠብቃቸው አስጠነቀቀች።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ከእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች ጋር በመሆን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተሳተፉ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ወደ አገራቸው በሚመለሱ ጊዜ በቁጥጥር ስር ይውላሉ ማለታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

“የደቡብ አፍሪካ ዜጋ ሆነው በጦርነቱ ውስጥ በመሳተፍ እየተዋጉ ላሉት ተዘጋጅተን እየተበቅናቸው መሆናችንን እና እንደምናስራቸው ቀደም ብለን ባወጣነው መግለጫ አሳውቀናል” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ለመግለጽ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተደረገ ዝግጅት ላይ ነው።

ስድስት ወራት ሊያስቆጥር በተቃረበው የእስራኤል ሐማስ ጦርነት ውስጥ ምን ያህል ደቡብ አፍሪካውያን ከእስራኤል ሠራዊት ጋር ተሰልፈው እየተዋጉ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ደቡብ አፍሪካ በጋዛ ጦርነቱ መቀስቀሱን ተከትሎ ዜጎቿ ከእስራኤል ጦር ጋር በመሆን ከተሳተፉ በሕግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ማውጣቷ ይታወሳል።

ሃሬትዝ የተባለው የእስራኤል ጋዜጣ የአገሪቱን ሠራዊት ጠቅሶ እንደዘገበው “ጦሩ ወታደሮቹ ወደ ውጭ አገራት በሚጓዙበት ጊዜ የደኅንነት እና የሕግ ከለላ ለመስጠት እየሠራ” መሆኑን አምልክቶ፣ ጉዳዩን ከሌሎች የእስራኤል መንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በቅርበት እየተከታተለው ነው ብሏል።

ባለፈው መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ 1,200 ሰዎችን በመግደል ከ200 በላይ የሚሆኑትን አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል። የአስራኤል ጦርም ለዚህ አጸፋ እያካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አሳውቋል።

በዚህም ምክንያት እስራኤል ጋዛ ውስጥ እያካሄደች ያለውን ጥቃት ካወገዙ አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ ግንባር ቀደሟ ስትሆን፣ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥም ገብታለች።

በተጨማሪም በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ እየወሰደች መሆኑን እንዲወስን ደቡብ አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት አቤቱታ ያረበች ሲሆን፣ እስራኤልም ክሱን ተቃውማለች።

ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት መውሰዷን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ላይ የሚደርሰውን የዘር ማጥፋት ለመከላከል እርምጃ እንድትወስድ ውሳኔ ተላልፏል።

አሁን ከእስራኤል ሠራዊት ጋር በጋዛ ውስጥ የተሰለፉ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች እስር እንደሚጠብቃቸው ያስጠነቀቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ፣ አገራቸው በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የክስ ፍርድ ሂደት አጥብቃ እንደሚከታተለው ተናግረው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሚኒስትሯ ደቡብ አፍሪካ ከእስራኤል አንጻር በያዘችው አቋም ምክንያት ከእስራኤል ደኅንነት ማስፈራሪያዎች እየተሰነዘሩባቸው እንደሆነ በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተናግረው ነበር።

የደቡብ አፍሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ‘ሜይል ኤንድ ጋርዲያን’ ከተሰኘው ድረ ገጽ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ኢላማ መደረጋቸውን አመልክተው፣ የቤተሰባቸው ደኅንነትም እንዳሳሰባቸው ገልጸው ነበር።