
ዜና አሜሪካ አልሸባብን በመደገፍ በተጠረጠሩ በተባበሩት ኤምሬትስና በሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ቀን: March 13, 2024
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የውጭ ሀብት ቁጥጥር ቢሮ (OFAC) ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ላለውና በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የሽብር ቡድን ገንዘብ በሚያሰባስቡና በሚያንቀሳቅሱ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኬንያና ኡጋንዳ 16 ኩባንያዎችና ግለሰቦች ላይ፣ ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ማዕቀብ ጣለ።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የውጭ ሀብት ቁጥጥር ቢሮ (OFAC) ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ማዕቀቡ የተጣለባቸው የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ (UAE) እና ቆጵሮስን የሚሸፍን ሰፊ የንግድ መረብ በመፍጠር ለአልሸባብ የገንዘብ ድጋፍ ያሰባስቡ እንደነበር ገልጿል።
ማዕቀቡ ይህንን የንግድ መረብ በመጠቀም ለአልሸባብ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ነጋዴዎችንም እንደሚያጠቃልል መግለጫው አመልክቷል።
አልሸባብ የአገር ውስጥ ንግዶችንና ግለሰቦችን በመዝረፍ እንዲሁም በተባባሪ ነጋዴዎች የገንዘብ ድጋፍ በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ፣ ከዚህ ውስጥም የተወሰነውን ገንዘብ ለአልቃይዳ የሽብር ቡድን እንደሚያጋራ ታውቋል።
ማዕቀብ የተጣለባቸው የግለሰቦችና አካላት የመሠረቱትን የንግድ መረብ በመጠቀም በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለአልሸባብ በማሰባሰብና በማሸሽ እንደ ተሳተፉ መግለጫው ያመለክታል። መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው ኩባንያ ሃሊል ኮሞዲቲስ ኤልሲ (Haleel Commodities L.L.C.)፣ ወይም በሌላ መጠሪያው ሃሊል ግሩፕ (Haleel Group) ለአልሸባብ ቁልፍ የፋይናንስ ድጋፍ አስተባባሪ መሆኑንም አስታውቋል።
የአልሸባብ የግንዘብ ምንጭ ሃሌል ግሩፕ በተባለው ኩባንያ መሪዎች፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በቆጵሮስ ባሉ የዚህ ኩባንያ ቅርንጫፎች ላይ የተመሠረተ መሆኑንም መግለጫው ያመለክታል። በቆጵሮስ ውስጥ ያሉ የሃሊል ግሩፕ ቅርንጫፎች ሃሊል ፋይናንስ ሊሚትድ፣ ሃሊል ሆልዲንግስና ሃሊል ሊሚትድ ሲሆኑ፣ በኬንያና ኡጋንዳ የሚገኙት እህት ኩባንያዎቹ ሃሊል ኮሞዲቲስ ሊሚትድ መሆናቸውን፣ በሶማሊያ የሚገኘው ደግሞ ሃሊል ኤሌክትሮኒክስ በመባል እንደሚጠራ መግለጫው ያብራራል፡፡
ማዕቀቡ የተጣለበት ሌላው ኩባንያ መቀመጫውን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያደረገው ቂማት አል ናጃህ አጠቃላይ ትሬዲንግ (Qemat Al Najah General Trading) ሲሆን፣ ይህ ኩባንያ ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በተመሠረተው በዚህ የንግድ መረብ ውስጥ ገንዘብ በማሸሽና ከሃሊል ቡድን ጋር በመተባበር የአልሸባብን ገንዘብ በማስተዳደርና በማስተላለፍ ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑን መግለጫው ያመለክታል።
መቀመጫውን ኬንያ ያደረገው ፋይሰል ዩሱፍ ዲኒ (ዲኒ) የተባለው ግለሰብ ደግሞ የአልሸባብ የፋይናንስ አስተባባሪ በመሆን፣ የሃሊል ቡድንንና አንዳንድ የኩባንያውን አመራሮች በአልሸባብ ስም ገንዘብ እንዲያስተላልፉ ከማስተባበር በተጨማሪ፣ መቀመጫውን ኬንያ ካደረገው መሐመድ ጁማሌ ዓሊ አዋሌ (አዋሌ) ጋር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችንና የገንዘብ ዝውውርን በመወጠንና በመተግበር በቅርበት እንደሚሠራ መግለጫው አመልክቷል።
ለአብነትም ይህ ግለሰብ መቀመጫውን በኬንያ ባደረገው ክሩውን አውቶቡስ አገልግሎትን ጨምሮ በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና ኩባንያዎች የአልሸባብን ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ይመራ እንደነበረ፣ ክራውን አውቶቡስ አገልግሎት ደግሞ የአልሸባብን የሎጂስቲክስ ሥራዎችን ሲደግፍ መቆየቱን መረጃው ያስረዳል።
በአጠቃላይ ስማቸው ከላይ የተገለጸው ኩባንያዎችና ከኩባንያዎቹ ጋር የተገናኙ ግለሰቦችን፣ እንዲሁም የተጠቀሱት ኩባንያዎችና ግለሰቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ 50 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ድርሻ የያዙባቸው ሌሎች በአሜሪካ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የንግድ አካላት ገንዘብና ንብረቶቻቸው መታገዱን አስታውቋል።