አቶ ክርስቲያን ታደለ

13 መጋቢት 2024

ተሻሽሏል 14 መጋቢት 2024

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 5/2016 ዓ.ም.ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑትን የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት አነሳ።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ የአቶ ክርስቲያን ያለመከሰስ መብት መነሳት አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ማቅረባቸው ተዘግቧል።

“አቶ ክርስቲያን በአማራ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር አብረው ሲሰሩ እንደነበር” የፌደራል ፖሊስ መርምሮ ለአቃቤ ሕግ መላኩንም ዶ/ር ጌዲዮን ገልጸዋል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ ፓርላማ የገቡት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ምርጫ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ን ወክለው ተወዳድረው ነው።

አቶ ክርስቲያን ፓርላማ ከገቡ በኋላ በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነዋል።

ሆኖም በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ ባለፈው ሐምሌ ወር በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ላላፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ ይገኛሉ።

አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከሰባት ወራት በኋላ ነው ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን በዛሬው ዕለት ያነሳው።

ቢቢሲ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተመለከተው እና ለፓርላማ አባላት የተላከው አጀንዳ የአንድ የምክር ቤት ያለመከሰስ መብት እንደሚነሳ ያትታል።

“የአንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ማንሳት አስመልክቶ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ማጽደቅ” አንደኛው አጀንዳ እንደሆነም ተጠቅሷል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የቢቢሲ ምንጮች ያለመከሰስ መብታቸው የሚነሳው የምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።

ከአቶ ክርስቲያን በተጨማሪ ሌላኛው የአብን ተወካይ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔም ባለፈው ጥር መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ሆኖም ግን ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት ያለመከሰስ መብት ያነሳው የአቶ ክርስቲያን ታደለን ብቻ ነው።

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት፤ “ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።

የአቶ ክርስቲያን ያለመከሰስ መብት በአባላት አብላጫ ድምጽ አግኝቶ መነሳቱን ተከትሎ በሥራ ላይ ባለው ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳ ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል።

ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ዶ/ር ጫላ ዋላ ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሦስት የክልል ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት መነሳቱ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት የአማራ ክልል ምክር ቤት የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት ባለፈው የካቲት ወር ላይ አንስቷል። የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ደግሞ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ የአቶ ታዬ ደንደኣን ያለመከሰስ መብት ያነሳው የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ነበር።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገርም ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው በተመሳሳይ ወቅት ነበር።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ሦስቱ የክልል ምክር ቤት አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉት ያለመከሰስ መብታቸው ከመነሳቱ ከወራት ቀደም ብሎ መሆኑ ይታወቃል።